Site icon ETHIO12.COM

በመዲናዋ ያለአግባብ የተያዘ 13 ሚሊዮን ካሬ ሜትር መሬት ተገኝቷል – ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ

በአዲስ አበባ የመሬት አጠቃቀም ላይ በተደረገ ፍተሻ 13 ሚሊዮን ካሬ ሜትር ያለአግባብ የተያዘ መሬት መለየቱን ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።

ምክትል ከንቲባዋ በመሬት አጠቃቀምና አያያዝ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላትና ከባለሃብቶች ጋር እየተወያዩ ነው።
በውይይቱ በመዲናዋ ዓመታትን ያስቆጠሩ የመሬት ጥያቄዎችን ለመመለስና በዘርፉ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል።

ቀደም ሲል የነበረውን የመሬት አሰጣጥ መፈተሽ፣ በዘርፉ የአቅምና የመልካም አስተዳደር ችግር ያለባቸውን ባለሙያዎች የማረምና በሌላ መተካት ከስራዎቹ መካከል ተጠቅሰዋል።

የመሬት ዘርፉን ከመልካም አስተዳደር ችግር ለማጥራት በተከናወነው ተግባርም 422 ሙያተኞች ከዘርፉ እንዲወጡ መደረጉ ተገልጿል።

በመሬት አሰጣጥ ፍተሻው 13 ሚሊዮን ካሬ ሜትር መሬት ያለአግባብ የተያዘ መሆኑን በማጣራት 10 ሚሊዮን ካሬ ሜትር ወደ መሬት ባንክ እንዲመለስ ተደርጓል ነው የተባለው።

ምክትል ከንቲባዋ ጥያቄ ቀርቦባቸው ለረዥም ጊዜ ውሳኔ ያልተሰጣቸው 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ካሬ ሜትር የመሬት ይዞታዎች በአንድ ጊዜ ውሳኔ እንዲያገኙ መደረጉን ነው የተናገሩት።

ይህን መሰረት በማድረግ የመሬት ጥያቄ ለነበራቸው የሃይማኖት ተቋማት፣ በሆቴልና አገልግሎት ዘርፍ ለተሰማሩ አዳዲስና የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች፣ ለጤና ዘርፍ ተቋማት፣ ለአምራች ኢንዱስትሪዎችና መሰል ፕሮጀክቶች ግልጽ በሆነ አሰራር መሬት ተሰጥቷል ብለዋል።

የተሰሩት ስራዎች በከተማዋ የነበረውን የመሬት ወረራ ከመቀነስ ባሻገር በአገልግሎትና በጤናው ዘርፍ የነበሩ ክፍተቶችን የሚቀንሱና የስራ ዕድል የሚፈጥሩ መሆኑንም ምክትል ከንቲባዋ ተናግረዋል።

“የከተማዋ መሬት ያለ ስራ ታጥሮ መቀመጥ የለበትም” ያሉት ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ መሬቱን ያገኙ ባለሃብቶችም ፈጥነው ወደ ስራ መግባት እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ ባለሃብቶችም የተሰጣቸውን መሬት በተያዘለት ጊዜ ለታለመለት ዓላማ እንደሚያውሉ ተናግረዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ባደረገው የመሬት አጠቃቀም የአሰራር ፍተሻ ለዕምነት ተቋማት ጥያቄ መልስ የሰጠው ፍትሃዊ ምላሽ የሚበረታታ መሆኑንም የሃይማኖት አባቶች ገልፀዋል።

ለረዥም ጊዜ የቆዩ የመሬት ጥያቄዎች በአጭር ጊዜ መመለሳቸውን የጠቀሱት ተሳታፊዎቹ ይህ የመልካም አስተዳደር መስፈን ጅማሮ መኖሩን የሚያመላክት እንደሆነም ገልፀዋል። ኦቢኤንሚያዝያ 15/2013-

Exit mobile version