Site icon ETHIO12.COM

የልጅ እንዳልካቸው መኮንን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሹመትና የተማሪዎች አመጽ

አብርሃም ተወልደ

 በአጼ ሀይለስላሴ አገዛዝ መጨረሻ አካባቢ በዛሬው እለት ከተከሰቱ ታሪካዊ ሁነቶች መካከል የልጅ እንዳልካቸው መኮንን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ መሾምና የተማሪዎች አመፅ ይጠቀሳል። ይህ ክስተት በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ሲታወስ የሚኖር በውስጡ በርካታ ጉዳዮችን በጥቅል የያዘ ነው።

“የደሃውን ልጅ በደሃነቱ ለማስቀረት የታለመ ነው” በሚል ፍራቻ የአያሌ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማረዎችን እና ወላጆችን ድጋፍ ያገኘውን ዋና ጥያቄያቸው መንግስት ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅቱ ላይ የነበረው “ኢጁኬሽናል ሴክተር ሪቪው” የተሰኘውንና የትምህርት ማሻሻያ ይሆናል ተብሎ የተነደፈውን ፕሮግራም እንዲታደግ በየካቲት 11 ቀን 1966 ዓ.ም የሀገሪቱ መምህራን ጠቅላላ የስራ ማቆም አድማ መቱ።

በዚህ መልክ ገንፍሎ የወጣው ህዝባዊ ቁጣ መለያ ባህሪው የተቀናጀ መሆኑ ነው።ይሁን አንጂ ግዙፍና ሁለተናዊ በመሆኑ ስርዓቱን አርበደበደው።በጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ በሚመራው ካቢኔ ውስጥ የመገናኛ ሚኒስትር የነበረውን ልጅ እንዳልካቸው መኮንንን ጠቅላይሚኒስትር አድርጎ መሾም አዲስ ካቢኔ እንዲመሰርት አዘዘ፡፡

እንዳልካቸውም ከቀድሞው ሚኒስትሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ዶክተር ምናሴ ኃይሌን ብቻ ሲያስቀር ካቢኔውን በአዲስ መልክ አቋቋመ።አዲሱ ካቢኔ የመሳፍንቱን ወገን ጊዜያዊ የበላይነት ከማንጸባረቁ ባሻገር እንዳልካቸውን ጨምሮ ሶስት የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ምሩቃን ስለነበሩበት (ሌሎች ሁለቱ የአገር ግዛት ሚኒስትሩ ዶክተር ደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ስላሴ እና የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ዶክተር ልጅ ሚካኤል እምሩ ናቸው) የህዝብን ህሊና የሚስብ ይመስል ነበር።ይሁን እንጂ ህዝባዊው አመጽ በዚህ የማስታገሻ ርምጃ ከመብረድ ይልቅ ይበልጥ እየሰፋና እየከረረ ሄደ፡፡

ታላቁ ሠላማዊ ሰልፍ

ለአያሌ ሳምንታት በቆየው ህዝባዊ አመጽ ውስጥ ሌላው ጉልህ ስፍራ የያዘው በሚያዝያ 10 ቀን የተካሄደው ከመቶ ሺህ በላይ የሚገመት ህዝብ የተካፈለበት ግዙፍ ሰላማዊ ሰልፍ ነው።ሙስሊሞች እና ክርስቲያን ደጋፊዎቻቸው የተሳተፉበት ይህ ሰልፍ የሃይማኖት እኩልነት እንዲሰፍን የመንግስት እና የቤተክህነት ቁርኝት እንዲቀርና የሙስሊም በዓላት ብሔራዊ በዓላት እንዲሆኑ አበክሮ ጠየቀ፡፡

በየሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ከፍተኛ ሹማምንት

 ከስራ እንዲባረሩ መጠየቅ የተለመደ ነገር ሆነ፤ አንዳንድ ባለስልጣናት እስከነአካቴው በየቢሯቸው ለተወሰነ ጊዜ እስከመታሰር ደርሰው ነበር።በዋና ከተማ የተጀመረው አንቅስቃሴ ወደ ጠቅላይ ግዛቶችም ተዛመተ።በጅማ በህዝቡ የተመረጠ ኮሚቴ ሙሉ ስልጣን ጨብጦ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ጥላቻ አትርፎ የነበረውን የንጉሰ ነገስቱን እንደራሴ ደጃዝማች ጸሐዩ እንቁስላሴን አባረረ።ይህን ተግባሩን በሩሲያ አብዮት ከታየው ህዝባዊ ልዕልና ጋር በማነጻጸር ግራ ሀይሎች “የጂማ ሶቪየት” ሲሉ አሞካሹት።

የእንዳልካቸው ካቢኔ ይህን ህዝባዊ ማዕበል ለመግታት ከቶም አልቻለም።ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ፋታ ስጡኝ” እያለ ቢማፀንም ሰሚ አላገኘም ።ከግራ ሀይሎች ለዚህ ምልጃ ያገኘው ምላሽ “ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም” የሚል ሆነ።በሌላ አነጋገር በቀድሞና በአዲሱ ካቢኔ መካከል የቅርጽ እንጂ የይዘት ልዩነት የለም እንደማለት ነበር።

አዲሱ ካቢኔ የወሰዳቸው አንዳንድ የማሻሻያ ርምጃዎችም የህዝቡን ቀልብ ከቶም ሊስቡ አልቻሉም።ለምሳሌ፣ ካቢኔው በተሰየመ ጥቂት ቀናት ውስጥ በንጉሰ ነገስቱ ትዕዛዝ ህገ መንግስቱን ለማሻሻል ዕቅድ ነደፈ።በመጋቢት ወር ውስጥ ደግሞ የቀድሞ መንግስት ሸማምንትን አለአግባብ መበልጸግ አጣርቶ ለፍርድ የሚያቀርብ የምርመራ ኮሚሽን ተቋቋመ።ከዚያም በማስከተል አዲሱ ካቢኔ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲውን በዝርዝር የሚያብራራ የእንግሊዝ መንግስትን አሰራር ዘይቤ ተከትሎ “ነጭ ሰነድ” (white paper) የተሰኘ መመሪያ ይፋ አደረገ፡፡

ይህ ሁሉ ግን እንዳልካቸው የፈለገውን ፋታ ሊያስገኝለት አልቻለም።የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋንኛ ችግር ምንም እንኳ ራሱንና ካቢኔውን በአዲስ መልክ ለማቅረብ ቢሞክርም የቀድሞ ታሪኩ እስረኛ መሆኑ ነው።በአንድ ወገን ከመሳፍንት ዘር መወለዱ እና ሌላ ወገን ደግሞ ስርዓቱ ተቀባይነት የሌለው ስብዕና ሰጠው።

ገና ከመሾሙ በየካቲት 22 ተማሪዎች ተቃውመውት ሰልፍ ወጡ።ከሶስት ቀን በኋላ ደግሞ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ማህበር የማያወላዳ ሂስ ሰነዘሩበት።ከዚያ ቀጥሎ በሰራተኞች ማህበር ኮንፌዴሬሽን የተጠራው ጠቅላላ የስራ አድማ በመሰረቱ “የሰራተኛውን መብት ለማስከበር የተደረገ ነበር” ቢባልም አዲሱን ካቢኔ የመቃወም የፖለቲካ ገጽታ ነበረው።በመጨረሻም የአጋሚው ለውጥ ሰላባ ሆኑ።

ምንጭ፦ “የኢትዮጵያ ታሪክ” በባህሩ ዘውዴ፤ “ቀዳማዊ ሃይለስላሴ” መርሴ ሃዘን ወልደ ቂርቆስ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17/2013


Exit mobile version