Site icon ETHIO12.COM

የመርካቶ ሰባተኛ ቆጥ ቤቶች ገመናና- ጉቦ

ቤት መጠለያም ገመና መሸፈኛ ነው። ቤትና መቃብር ለብቻ የሚባለውም ለዚሁ ነው። ባልና ሚስት፣ልጆች፤ ጎጆው እየደረጀ ሲመጣም የቅርብ ዝምድና ያላቸው የቤት ሠራተኞች አባል ይሆናሉ፡፡ሆኖም የዚህ ዓይነቱ ቤተሰብ የሚመሰረትበት መኖሪያ ጎጆ አቅርቦት ለማሟላት ፈተና የሆነባት ኢትዮጵያ አሁንም ችግሩን አልተሻገረችውም፡፡የቤት አቅርቦት ችግሩ ከመባባሱ የተነሳ በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ምቹነቱም ገመና ከታችነቱም ቀርቶ ብዙዎችን ምሬት ውስጥ ከቷል፡፡መፀዳጃ ቤትና ፍሳሹ ተጎራብቷቸው ይስተዋላል።ሰው በፍፁም ሊኖርባቸው የማይገባ ጽዩፍ እየሆኑ መጥተዋል። ቤት ከሚባለው ይልቅ ንጹ አየር ፍለጋ ደጁ ለውሎና አዳር እየተመረጠ ነው፡፡እንዳንዶችም ይህን ሀሳብ እየሰጡ ነው። እንዲህም ንጽህናቸው ተጓድሏል የሚባሉም ሆኑ የተሻሉ መኖሪያቤቶችን በኪራይ በአዲስ አበባ ከተማ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ውስጥ ማግኘት ከባድ የሆነባቸው ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡በብዙ ድካም ተገኝቶም ተከራዩን ምቾት የሚነሱት ብዙ ነገሮች ያጋጥሙታል፡፡አሁን እየታየ ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ተባብሶ ነዋሪውን የበለጠ አማሮታል፡፡

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በደከሙ የቀበሌ ቤቶች አናት ላይ የቆጥ መኖሪያ ቤት ሰርቶ ማከራየትና ኑሮን መደጎም ተለምዷል። በቤት እጥረት የተጨናነቀውን ቤተሰብ በቤቱ ጣሪያ ላይ ቆጥ ሰርቶ ዘና ኢንዲል ማድረግና ማስተንፈስ ተመራጭ ሆኗል። በወረዳ ስምንት ሰባተኛ፣ከአውቶቡስ ተራ ጀርባ ባለው በቀበሌ 32 እንዲሁም በተለምዶ በሰባተኛ አጎራባችና አጎናፍር ሆቴልና አየለ ሆቴል እየተባሉ በሚጠሩት አካባቢዎች የቆጥ ቤት አከራዮች፣ተከራዮች በብዛት ይገኛሉ፡፡

ወይዘሮ ፍቅር አዲስ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የመርካቶ ሰባተኛ ቆጥ ቤት ተከራይ ናቸው። እንዳጫወቱን የቆጥ ቤቶቹ የሚሰሩት በአብዛኛው በአረጁ የቀበሌ ቤቶች አናት ላይ ነው። ከአናቱ የሚሰሩበት ምክንያት ደግሞ ወደ ጎን ለማስፋት ከግራም ሆነ ከቀኝ ቦታ ባለመኖሩ ነው። በወረዳ ስምንት በዚህ መልኩ የሚሰሩት አብዛኞቹ ቤቶች ለነዋሪዎቹ የገቢ ማስገኛ ናቸው። በተለይ አሁን እየታየ ባለው የኑሮ ውድነት ኑሮውን ለመደጎም ለነዋሪዎቹ ዓይነተኛ መፍትሄ ሆኖላቸዋል።ወይዘሮ ፍቅር በቆጥቤት ኪራይ ለ10 አመታት ኖረዋል፡፡በቅርቡ ግን የቀበሌ ቤት አግኝተው ከቆጥ ላይ ወርደዋል፡፡

በሥፍራው ተገኝቼ እንዳየሁት በቆጥ ላይ ለዚያውም በኪራይ በፍፁም አይመከርም። ቆጦቹ የተሰሩት በአጠናና ከምን አለሽ ተራ በተሰበሰቡ አሮጌ ቁርጥራጭ ቆርቆሮ በመሆኑ ለዓይን ማራኪ ውበት የላቸውም። ጣራቸው ለአጠናና ቆርቆሮ ፍጆታ ቁጠባ ሲባል ከወለላቸው ብዙም የራቀ አይደለም ።የአንድ የመካከለኛ ሰው ቁመት ያህል እንኳን አይሆኑም። ተጎንብሶ ተገብቶ ተጎንብሶ የሚወጣባቸው ናቸው። ምግብ አዘጋጅቶ ማዋል አይቻልም። ከሙቀት የተነሳ ምግብ አብስሎ ለምሳና ለእራት ማቆየት አይታሰብም፡፡ተበላሽቶ ይደፋል፡፡ተከራዩ የግል መብቱ አይጠበቅም፡፡ገመናን መሸፈን የሚባል ነገር የለም፡፡በአከራዩ ቤት ነው የሚተላለፈው፡፡ወደ ቆጡ የሚወጣበትና የሚወርድበት መሰላልም አስተማማኝ አይደለም፡፡ጥንካሬ ስሌለው የመውደቅ አደጋ ያጋጥማል፡፡በአጠቃላይ የቆጥ ተከራይ ‹‹ኑሮ ካሉት መቃብርም ይሞቃል›› እንደሚባለው አይነት ህይወት ነው የሚገፋው፡፡

ቆጥ ለመከራየትም ደላላ ጋር መሄድ ያስፈልጋል፡፡በግል ጥረት አይገኝም፡፡የአከራይና ተከራይ አገናኝ(ደላላ) ምን ውየለት ድፋባቸው በዚህ አካባቢ ነው የሚሰራው፡፡ስለስራውም ስለአካባቢውም እንዳጫወተኝ፤ወረዳ አምስት ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ያለበት በመሆኑ ከንግድ ውጪ የመኖሪያ ቤት ኪራይ በፍፁም አይገኝም። ወረዳው ነዋሪ ይበዛበታል ።ቆጥ ቤት ቢኖርም ከቤተሰብ የሚያልፍ አይደለም። በመሆኑም አስፋልቱን ተሻግረን ድሬ ታወር ቁልቁል በመውረድ በርካታ የቆጥ ቤቶችን ቃኝተን ነው በተለምዶ አጎናፍር ሆቴልና አየለ ሆቴል እየተባሉ ወደ ሚጠሩት የቆጥ ቤቶች የሚገኙባቸው አካባቢዎች የተሻገርነው ።

አቶ ሬድዋን አብደላን ያገኘናቸው ደግሞ እነዚሁ የቆጥ ቤቶች በስፋት በሚገኙበትና በተለምዶ አየለ ሆቴል እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው ።እርሳቸውም እንዳጫወቱኝ አራት ልጆች ቢኖራቸውም ልጆቻቸውን በየሰው ቤት እንጀራ በመጋገር የምታስተዳድረውን ባለቤታቸውን ለማገዝ በአካባቢው የሸክም ሥራ ለመሥራትና ለመኖር ከመጡ ሰባት ዓመታቸውን ይዘዋል ። በዚህ ጊዜ ውስጥ በአካባቢው የሚከራዩት ቤት አላገኙም ። ቢያገኙም ከገቢያቸው ጋር የሚመጣጠን አይደለም። ሁለት በሁለት የቆጥ ቤት እስከ አራት ሺህ ብር ይጠየቅበታል። አራት በአራት እያለ ትንሽ ጥራት ያለው ቤት እስከ 10ሺ ብር ነው የሚከራየው። የጥራት ነገር ከተነሳ ብዙ ጥራታቸው የተጓደለ የቆጥ ቤቶች አሉ። መወጣጫ መሰላላቸው እንኳን አያስተማምንም ። የሚሰራው በአጠና በመሆኑ ተከራዮችን ሲጥልና ለአካል ጉዳት ሲዳርግ ያዩበት አጋጣሚም አለ። ከንጽህናና ከጤና አንፃርም ቢሆን ብዙ ጎዶሎ የሆኑ ነገሮች አሏቸው፡፡አኗኗሩ የተፋፈገ በመሆኑ ምቹ አይደለም፡፡ለኮቢድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ መተላለፊያም ዓይነተኛ ምክንያትነት ሆኖ ይጠቀሳል፡

የእነዚህ ቤቶች ዋጋ ከአንድ ሺ 500 እስከ ሁለት ሺ 500 በመሆኑ አቶ ሬውዳን ትንሽ ገንዘብ ጠርቀም አደርገው ተከራይተዋቸው ያውቃሉ። ነገር ግን ምቾት ስላልሰጧቸውና በጤንነት መኖር ስላላስቻሏቸው የሸክም ሥራ የሚሰሩበት ቦታ ላይ ሸራ አንጥፈው ለማደርና ለመኖር ተገድደዋል። ከዚህ ለመውጣት በ2005 ዓ.ም የተመዘገቡትን የ20/80 ቤት ቢጠብቁምና ከዕለት ጉርሳቸው እየከፈሉ ቢቆጥቡም የቤት ዕድለኛ መሆን አልቻሉም። አሁን ላይ ከተጋጋለው ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ ጭራሽ የቤት የቁጠባ ክፍያው ስለከበዳቸው ለማቋረጥ ተገደዋል። አቶ ሬውዳን ያሉበትን ሁኔታ መንግሥት እንዲያይላቸውና መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ወጣት ተሾመ ሚዲቅሳን ያገኘነው ደግሞ ከአውቶቡስ ተራ ጀርባ ባለውና አያሌ የመኖሪያ ቆጥ ቤቶች በሚከራዩበት አካባቢ ነው። ወጣቱ እንዳጫወተን በ2008 ዓ.ም በጂኦሎጂ በዲግሪ ቢመረቅም እስከ አሁን ሥራ ባለማግኘቱ የዕለት ጉርሱን የሚሸፍነው በአካባቢው በሱቅ በደረቴ ሥራ እየሰራ ነው ኑሮውን የሚመራው፡፡ሥራውን የሚሰራው በከተማዋ የደንብ አስከባሪዎች እየተባረረ መሆኑንም ይናገራል፡፡ለሚኖርበት የቆጥ ቤት ኪራይ ለመክፈልም ሆነ የዕለት ጉርሱን ለመሸፈን እንዳልቻለም በምሬት ይገልጻል፡፡ወጣቱ እንዳጫወተኝ በቀበሌ 32 ቀላል የሚባለው የቆጥ ቤት ኪራይ በቀን ከ30 እስከ 50 ብር ተከፍሎ በአንድ አልጋ ላይ ለአራት የሚታደርበት ነው። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የዕለት ከዕለት አዳሩም በዚህ የተወሰነ ነበር። ማደሪያው ለኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ አጋላጭ በመሆኑ ወጣጡ አዳሩንና ውሎውን በጎዳና ላይ ለማድረግ መርጧል። በአካባቢው አግኝተናቸው ያነጋገርናቸው በርካታ የቆጥ ቤት ተከራዮችና አከራዮች እንደነገሩን ብዙዎቹ አከራዮች ሴት ተከራይ አይፈልጉም።ሙሉውን ቀን ቤት ለሚውልም ሰው ቤታቸውን ለማከራየት ፈቃደኛ አይደሉም።ምክንያታቸው ደግሞ ቀን ቀን ለአጭር ጊዜ የሚከራዩ በመኖራቸውና ተጨማሪ ገቢ ስለሚያገኙበት ነው፡፡

ወይዘሮ ፍሬህይወት ፈይሰንን ያገኘናት አየለ ሆቴል እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ባለው ገሊላ ፎቶ ቤት ገባ ብሎ የሚገኘው የመንገድ ቅያስ ባለው የቀበሌ ቤት የቆጥ ቤት እያስገነባች ነው። እንዳጫወተችን የምታስገነባው እሷም እንደሌሎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች እየናረ የመጣውንና መገራት ያልቻለውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም የሚያስችላት ገቢ ለማግኘት ነው። ከአራት ዓመት በፊት በስደት ሄዳ ስትሰራበት የነበረው የሳውዲ መንግሥት ከአገራቸው እንዲወጡ ባለበት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው። ሆኖም በ18 ዓመቷ በሳውዲ 14 ዓመት ብትሰራም፡፡ይህ ነው የሚባል ሀብት አላፈራችም፡፡ባለቤቷም ቢሆን በኮቪድ ምክንያት ሥራ ማግኘት ባለመቻሉ እያገዛት አይደለም። በመጣችበት ወቅት አጋጣሚ እናቷ የጋራመኖሪያቤት ሲደርሳቸው ይኖሩበት የነበረው የቀበሌ ለእርስዋ ተሰጣት።ቤቱ ሁለት ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ አራት በአራት የሆነ ቆጥቤትም አለው፡፡ከሌሎቹ የተሻለ ነው፡፡የምታሰራው በአዲስ ቆርቆሮ ነው። እያንዳንዱን ቆርቆሮ የገዛችው ደግሞ 300 ብር ሲሆን አጠቃላይ የፈጀባት 15 ቆርቆሮ ነው። በጠቅላላው ሁለት ሺ 500 ብር ወጪ አድርጋለች፡፡እንደሌሎቹ ተከራዮች ተጨናንቀው እንዲኖሩ አትፈልግም፡፡ሴቶችንም ለማከራየት ተዘጋጅታለች፡፡ነገር ግን ቅድመሁኔታ አስቀምጣለች ጠዋት ወጥታ፣ማታ የምትገባ ነው የምትፈልገው፡፡ምክንያትዋን ግን ግልጽ አላደረገችም፡፡

በዚሁ አካባቢ ያሉት ሌላዋ የቆጥ ቤት አከራይ ወይዘሮ ማሜ አሰግደው ይባላሉ ።እንዳጫወቱን ባለቤታቸው የዘጠኝ ዓመት ልጅ ጥሎባቸው ከሞተ አርባ ቀኑን ይዟል።የሚያከራዩት የቆጥ ቤት ለተከራይ ደህንነት ሲባል መሰላሉ ብረት ነው ። ዋጋው ደግሞ ከነ ውሃና መብራቱ 1ሺህ 500 ብር ነው። ‹‹ውሀ የሬሳ ማጠቢያ ነው ››የሚሉት ወይዘሮ ማሜ ውሃ መቅዳትና መብራት ማብራትም ገደብ እንደሌለው አጫውተውናል። የመጨረሻው የተከራይ መግቢያ ሰዓት ከምሽቱ ሦስት ሰዓት መሆኑንና በትራንስፖርትና በተለያየ እክል የዘገዩ ተጠብቀው የጊቢው በር (ጊቢ ከተባለ )የሚዘጋው ከምሽቱ ሦስት ተኩል መሆኑንም ነግረውናል ። ወይዘሮ ማሜ ጋር በምሽት ጊዜ በር ሲቆለፍ ለመክፈትም ቢሆን ዋጋውን ለመጋራት የፈለገውን ያህል ሰው መጨመር ለተከራይ ይፈቀድለታል።

በሦስቱም የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አካባቢዎች ያነጋገርናቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች እንደነገሩን የቆጥ ቤቶቹ ግንባታ ዕለት ከዕለት እየጨመረ ነው። የነዋሪዎቹን የዕለት ከዕለት ኑሮ ቢደጉሙና የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም ቢያግዙም መዘዛቸው ብዙ ነው። ከኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ ጋር ተያይዞም አኗኗሩን የከፋ እያደረገው ይገኛል፡፡ ብየቆጥቤት ግንባታዎች የሚከናወኑት ለወረዳና ክፍለ ከተማ አመራሮች ጉቦ እየተሰጠ እንደሆነና በክፍለ ከተማው እርምጃ እየተወሰደ አለመሆኑንም ለመረዳት ችያለሁ፡፡

እኛም የክፍለ ከተማው ጽሕፈት ቤት የነዋሪዎቹን የቤት ችግር ለመፍታትና የቆጥ ቤቶቹ በጤናና በአካል ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን ችግር ለመቅረፍ እንዲሁም የአካባቢውን ፕላን ለማስጠበቅ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ለመቃኘት በተደጋጋሚ ለማነጋገር ሞክረን ነበር።ቢሮ በሄድንበት አጋጣሚ ኃላፊ ነኝ ያሉን ወይዘሮ ውቢት በአንድም በጉዳዩ ላይ ከዚህ ቀደም መረጃ መስጠታቸውን በመግለጽ መረጃ ሊሰጡን አልፈቀዱም።ወደ አቶ ዳንኤልም አሸጋግረውን እርሳቸውም የፍርድ ቤት ቀጠሮ ስላለኝ አልችልም ብለውናል።ስልክም በመደወል እንዲተባበሩን ጠይቀናቸው፡፡ሊተባበሩን አልቻሉም፡፡

ሰላማዊት ውቤ – አዲስ ዘመን ሚያዚያ 16/2013


Exit mobile version