Site icon ETHIO12.COM

የፋሲካ በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር በድምቀት እንዲከበር ኮሚሽኑ በቂ ዝግጅት አድርጓል… ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል

ህብረተሰቡ በመላ ሀገሪቱ የሚከበረውን የፋሲካ በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር በድምቀት እንዲያከብር በቂ ዝግጅት መደረጉን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ገልጸዋል። ኮሚሽነር ጀነራሉ የፋሲካ በዓልን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ፋሲካ የእምነቱ ተከታዮች እርስ በእርስ ግንኙነታቸውን የበለጠ የሚያጠናክሩበት፣ መንፈሳዊ እሴቶቻቸውን የሚያዳብሩበት፣ ተቻችለውና ተከባብረው በጋራ መኖርን ለመላው አለም የሚያሳዩበት ታላቅ በዓል ነው ሲሉም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

በዚህ በዓል ወቅት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ህዝቡን ከጎኑ አሰልፎ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር በርካታ የፀጥታ ስራዎችን በማከናወን ላይ ነው።

ኮሚሽኑ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በንፁሃን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ለማክሰም ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የህግ የበላይነትን የማስከበር ዘመቻ እያካሄደ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በዚህም የጁንታውን ርዝራዦች፣ የኦነግ ሸኔ አባላት እና በመተከል ዞን የመሸጉ ሽፍቶችን ከተደበቁበት ስፍራ ሙሉ በሙሉ አድኖ ለፍትህ ለማቅረብ ሌት ተቀን እየሰራ እንደሚገኝም አስታውሰዋል።

በሌላ በኩል 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ለማድረግ ፖሊስ በብቃትና በገለልተኝነት በማገልገልም ላይ ነው ብለዋል።

ኮሚሽነሩ እንዳሉት ሰራዊቱ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ሌሎች ታላላቅ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን በመጠበቅ ኢትዮጵያን ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች በጀግንነት እየታደጋት ነው።

በትግራይ ክልል በህግ ማስከበር ግዳጅ ላይ ያላችሁ፣ በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን፣ ምዕራብና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች፣ በቤኒንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን፣ በደቡብ ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ጉራ ፈርዳ ወረዳ፣ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና ከሚሴ ዞን እንዲሁም በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በግዳጅና በኦፕሬሽን ላይ ያላችሁ ውድ የሰራዊታችን አባላት በሙሉ እንኳን ለፋሲካ በዓል በሰላም አደረሳችሁ እላለሁ” በማለትም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ በመላ ሀገሪቱ የሚከበረውን የፋሲካ በዓልን ያለምንም የጸጥታ ችግር በድምቀት እንዲያከብር ኮሚሽኑ በቂ ዝግጅት ያደረገና የፖሊስ አባላትም በወትሮ ዝግጁነት ላይ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮችና ለመላው የሀገሪቱ ፖሊስ አባላትም እንኳን ለፋሲካ በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት በዓሉ የሰላም፣ የጤናና የፍቅር እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን መግለጻቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። via OBN

Exit mobile version