Site icon ETHIO12.COM

“ይህች አገር በዕድል ዛሬ ላይ የደረሰች አይደለችም በጀግኖች እናትና አባቶቻችን መስዋዕትነት እንጂ”፡- ዶ/ር ሂሩት ካሳው


የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ካሳው 80ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች ቀን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልእክት “ይህች አገር በዕድል ዛሬ ላይ የደረሰች አይደለችም በጀግኖች እናትና አባቶቻችን መስዋዕትነት እንጂ” ብለዋል።

ዶ/ር ሂሩት ካሳው ያስተላለፉትን የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ውድ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቼ ፤

ይህች ገናና እና ታሪካዊት አገራችን ለዛሬ ክብሯና ማንነቷ መሰረት የሆናት የኩሩና አገር ወዳድ ልጆቿ አጥንትና ደም ነው።

በየዘመናቱ ያልተነካ ሃብቷንና ያልተገዙ ልጆቿን ሊመዘብር እና ሊበዘብዝ አቅዶና ተደራጅቶ የመጣን ወራሪ ኃይል ግንባራቸውን ሳያጥፉ በመፋለምና አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ሃፍረትን ተከናንቦ እንዲመለስ ሲያደርጉ አገራቸውን ደግሞ የነጻነት ምድር፣ የተገፉት መጠጊያና መመኪያ አድርገውና ኢትዮጵያን በኩራት ማማ ላይ አስቀምጠው አልፈዋል።

ኢትዮጵያውያን ይህን ሲያደርጉ ኢትዮጵያዊነትን በልባቸው ጽፈው፣ ሰንደቃቸውን ከፍ አድርገው፣ እምነታቻውን በፈጣሪ ላይ ጥለው፣ ዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት፣ ፆታ ሳይለያቸው፤ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪ በየጦር አውድማው በጋራ በመትመም የጠላትን ቅስም ሲሰብሩ በአንጻሩ ደግሞ ወገናቸውን ሲያኮሩ ኖረዋል።

ለጠላት ኢትዮጵያን መያዝ ብሎም መግዛት ሃብቷንም መዝረፍ ህልም ሆኖ እንዲቀር አድርገዋል። ለዚህ የወዳጅ ምስክር አያሻንም በየጊዜው የተነሱ ጠላቶቻችን ሳይቀር መስክረው አልፈዋልና።

የኢትዮጵያውያን አርበኞች የአገር ፍቅር ስሜት ይህን ያክላል ይህን ይመስላል ብሎ በአጭር መለኪያ ወይም ቃል ለመግለጽ ይከብዳል። ከልክ በላይ ነውና፡፡

ዛሬ ያለው ትውልድ የተረከባት አገር የእነዚያ ጀግኖች ውድ ህይወት የተገበረባት ናት፡፡ ስለዚህ ዋጋዋም በዚያ ልክ የሚለካ ነው።

ይህች አገር በዕድል ዛሬ ላይ የደረሰች አይደለችም በጀግኖች እናትና አባቶቻችን መስዋዕትነት እንጂ፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያችን በአርበኞቹ ደምና አጥንት የተሰራች ስለሆነ ተረካቢ የሆንን እኛ ይህንን ሀቅ መርምረን ልናውቅና አገራችንን ይበልጥ ተንከባክበንና ጠብቀን ለቀጣይ ትውልድ ልናሸጋግር ይገባል።

ክቡራትና ክቡራን፤
አገራችንን መውደዳችንን የምናውጀው ሁኔታዎች ሲመቻቹልን ብቻ መሆን የለበትም፡፡ አርበኞቻችን በዚያ የ5ዓመት የተጋድሎ ዘመናቸው የአገር መሪ በሌለበት፣ መንግስታዊ አደረጃጀት በፈረሰበት፣ ስንቅና ትጥቅ እንደልብ በማይገኝበት፣ ጠላት ከላይ ቦንብና የመርዝ ጋዝ በሚረጭበት፣ ከታች መትረየስና መድፍን የመሰሉ ከባድ መሳሪያዎችን በወገን ላይ በሚያዘንብበት፣ የንፁህ ወገናችን መኖሪያ በእሳት በሚጋይበትና አብዛኛው ህዝብ ዱር ቤቴ ብሎ በሚኖርበት በዚያ ክፉ ቀን የአገር ፍቅር ያነደዳቸው አርበኞች ይህን ሁሉ መከራ ከምንም ሳይቆጥሩ ጠላትን አሳደው፤ ድል አድርገው ይችን ነፃ አገር አስረክበውናል።

ስለሆነም የዚህ ዘመን አገር ተረካቢዎች በማንኛውም ጊዜ ለአገራችን ልዕልናና ደህንነት ዘብ ልንቆም ይገባል፡፡ ለእነዚያ መከራን ታግሰው በድል ላደመቁን አርበኞች ከፍ ያለ ክብርና ምስጋናየን በዚህ አጋጣሚ ላቀርብ እወዳለሁ፡፡

ውድ የዛሬ ወጣቶች ይች አገር በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ታፍራና ተከብራ የኖረችና ዛሬ ላይ ደግሞ በእኛ መዳፍ መካከል ያለች ናት፡፡ ይህንን ክብር ያስገኙን ቀደምት እናትና አባቶቻችን አደራቸውን ተወጥተው ለዚህ ትውልድ እስከነሙሉ ክበሯ አስረክበዋል።

ስለሆነም ወጣት ኢትዮጵያውያን እንደቀደምቶቹ ጀግኖች፤ በፍቅር ሰንሰለት ተሳስረን፣ ለመጪ ትውልድ ያደገችና ለዜጎቿ የኩራት ምንጭ የሆነች አገርን ለማሸጋገር ከወዲሁ በርትተን መሥራት ይጠበቅብናል።

በተለይ ወጣት እህትና ወንድሞቻችን ታሪካችሁን፣ ባህላችሁን በሚገባ ማወቅና ሳይሸራረፍ ይልቁንም ሌላ አንፀባራቂ ድል ተጨምሮበት ለመጪው ወገን እንዲደርስ ተግታችሁ መሥራት ይኖርባችኋል።

አባቶቻችን “ ከአያያዝ ይቀደዳል ከአነጋገር ይፈረዳል “ እንዲሉ የዛሬዋን ኢትዮጵያ የያዝናት፣ የነገዋን ኢትዮጵያ የምንሰራት እኛ ነንና በብልህ አዕምሮ፣ በጠንካራ ክንድ፣ በፍቅርና በጥበብ ተክነን አገራችንን እንደሙሽራ ልናስውባትና ከፍ ልናደርጋት ይገባል።

ያኔ ጠላት ድንበር ጥሶ ታንክ መትረየስ ተኩሶ፣ መርዝ ነስንሶ ያላፈረሳትን አገር ዛሬ ላይ እኛ በወሬ ናዳና በአሉቧልታ፣ ባለመደማመጥና ባለማስተዋል ልንፈታተናት አይገባም።

ዛሬ ላይ ያለው ጠላት ድምበር ጥሶ ሳይሆን ባለንበት ቦታ ሁሉ በእጃችን በያዝነው የቴክኖሎጂ ውጤት የልቡናችንን በር ከፍቶ፣ ማንነታችንን አኮስሶ፣ መኩሪያዎቻችንን ባለማዎቅ አድበስብሶና አሳንሶ እያሳየ አገራችንን ንቀን ሌላውን እንድንናፍቅ፣ ወገናችንን ጠልተን ራስ ወዳድ እንድንሆን በማድረግ እኛ እርስ በእርስ ስንባላና ስንሰደድ ሌላው ያልተነካ ሃብታችንን ለመዝረፍ ወደ አገራችን መግባቱ የማይቀር ነው።

ስለሆነም ለአገራችን ጉዳይ ቀናኢና ንቁ ሆነን መነሳትና የአባቶቻችንን ትውፊት አጠንክረን መያዝ፤ የልቡናችንን ድንበር በሽንገላ ቃል ሊደፍር የሚሞክረውን እምቢ በማለት ልናሳፍረው ይገባል።

ነፃነታችን በእጃችን ነው ያለው፡፡ ከፈቀድን የጠላት መገልገያ እቃ እንሆናለን ካልፈቀድን ደግሞ የአገራችን የቁርጥ ቀን አለኝታ እንሆናለንና ከአሁኑ ምርጫችንን ማስተካከል ይገባናል።

ምሁራንና ወላጆች እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታችሁ አካላት በሙሉ ትውልድን በአዲስ አስተሳሰብ መቅረጽና በአገር ፍቅር ዙሪያ የልቡና ትንሳኤ እንዲኖረው በማስተማር እንድትተጉ በዚህ አጋጣሚ አደራ ለማለት እፈልጋለሁ።

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!

Via ENA

Exit mobile version