Site icon ETHIO12.COM

“ቴሌብር ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ተቋቁመን የጀመርነው ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ቴሌብር ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ተቋቁመን የጀመርነው ነው ብለዋል፡፡

“እንደ ሀገር በሞባይል ብር ማዘዋወር አገልግሎትን ስንጀምር ለዓለም አቀፍ ተቋማት ፈቃድ አለመስጠታችን ጫና ቢያሰድርብንም ቅድሚያ ለሀገር በሚል የገባንበት ነው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፡፡

ቴሌብር የሞባይል ገንዘብ ማዘዋወር አገልግሎት ፈቃድ ለኢትዮ ቴሌኮም ሲሰጥ ድርጅቱ አቅም አጎልብቶ ከውጭ ተቋማት ጋር የመወዳደር አቅምን እንዲያጎለብት መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ይህን አገልግሎት ስናስጀምር ጫናው ከባድ ቢሆንም ብሔራዊ ጥቅም በማስቀደም እንደተወሰነ እና ኢትዮ ቴሌኮም በጥብቅ ዲሲፕሊን ሥራውን በውጤታማነት መፈጸም እና አቅሙን ማጎልበት እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡

በሞባይል ገንዘብ ማዘዋወር አገልግሎት ከ10 ዓመት በፊት ለመንግስት ቀርቦ የነበረ ቢሆንም በወቅቱ ሳይሳካ መቅረቱንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ በበኩላቸው፣ ድርጅታቸው በ127 ዓመታት ውስጥ ለደንበኞቹ ሲያቀርብ ከነበረው አገልግሎት የተለየ የቴሌብር አገልግሎት ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡

ቴሌብር በገጠር ያሉ እና ዝቅተኛ የገቢ ምንጭ ያላቸው ዜጎችን በፋይናንስ ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ አልሞ የተዘጋጀ ሲሆን ገንዘብ ለመላክ፣ ለመቀበል፣ ክፍያ ለመፈጸም እና ለመገበያየት የሚስችል ዘዴ ነው መሆኑን ዋና ስራአስፈጻሚዋ ገልጸዋል፡፡

ቴሌብር የጥሬ ገንዘብ ህትመት ወጭን በመቀነስ ገንዘቡ ሰፊውን የማህበረሰብ ክፍል የልማት ፍላጎት ተደራሽ ያደርጋል ብለዋል፡፡

53 ሚሊዮን ዜጎች ቴሌብርን ይጠቀማሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን አገልግሎቱን በአምስት ቋንቋዎች ማግኘት ይቻላል ብለዋል ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፡፡ via EBC

Exit mobile version