Site icon ETHIO12.COM

የጎንደር ከተማን ሰላምና ደህንነት ለማወክ አቅደው የተንቀሳቀሱ ተጠርጣሪዎች እየተያዙ ነው

የጎንደር ከተማን ሰላምና ደህንነት ለማወክ አቅደው የግድያና እና ወንብድና ወንጀል የሚፈፅሙ ተጠርጣሪዎች እየያዘ መሆኑን የጎንደር ከተማ ፖሊስ መምሪያ ገለፀ።የመመሪያው ሀላፊ ኮማንደር አየልኝ ታክሎ እንደገለፁት ከሰሞኑ በጎንደር ከተማ ቁስቋም ፣ ሽንታ፣ ሳኒታ በሚባሉና ሌሎች አካባቢዎች የግድያና የእገታ ወንጀሎች ተፈፅመዋል።

እስካሁን በተገኘ መረጃ መሰረት ወንጀሉ የተፈፀመው የከተማዋን ሰላምና ደህንነት ለማወክ አላማ ባላቸው “የጠላትን ተልኮ በሚያስፈፃሙ አካላት ነው” ብለዋል።ከሰሞኑ የተፈፀሙ ወንጀሎች ካሁን በፊት ይፈፀሙ ከነበሩት የተለየ እቅድና አፈፃፀም እንዳላቸው መረጃዎች እንዳሉ ተናግረዋል።

የተፈፀመውን ወንጀል የሚያጣራ ቡድን ተደራጅቶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው ፤ መሰል ወንጀል ድጋሜ እንዳይፈፀም ሰምሪት መሰጠቱን የገለፁት የፖሊስ ሀላፊው፥ የታገቱት ግለሰቦች እንደተለቀቁ በውንብድና እና ግድያ ወንጀሉ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋል ተጀምሯል።

የከተማዋ ፖሊስና ሌሎች የፀጥታ አካላት ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ፤ በተደጋጋሚ መሰል ድርጊት የሚፈፀምባቸው አካባቢዎችን የመጠበቅና አጥፊዎችን ለህግ የማቅረብ ስራ እያከናወኑ ነው ያሉት።ህብረተሰቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ የፀጥታ አካላትን ለማገዝ ፍላጎት እንዳለው የተናገሩት ኮማንደር አየልኝ ፖሊስ ይህን አቅም በመጠቀም ይሰራል ብለዋል።

በጎንደር ከተማ ህዝባዊ በአላት ያለምንም ችግር መከበራቸውን ያስታወሱት የፖሊስ ሀላፊው አሁንም በፖሊስና ሌሎች የፀጥታ አካላት በኩል ያሉ ክፍተቶችን በማስተካከልና ህብረተሰቡን በማሳተፍ የከተማዋን ሰላም አስተማማኝነት እናሰቀጥላለን ሲሉ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አስታውቀዋል።

FBC በነብዩ ዮሐንስ



Exit mobile version