ETHIO12.COM

ማዕድን ቀጣዩ የኢትዮጵያ ጉሮሮ – “የሕዝብ ሃብት ለሚያባክኑ ዝምታ የለም” ታከለ ኡማ

ከለፈው ዓመት ጀምሮብኈራዊ ባንክ የወርቅ መቀበያ ክፍያን ሰላሳ በመቶ ከፍ ማድረጉ እንደ አቅርቦቱ እንዲጨምር አድርጎታል። ከዚህም በላይ አሁን ላይ በዓለም የወርቅ ግብይት በግራም እስከ ስልሳ ዶላር /የሚቀያየር ነው/ መሆኑ ወርቅ ቢሰራበት ከፍተና ገቢ እንደሚያስገኝ ጥርጥር የለውም። የብሄር ፖለቲካ መጋኛ የመታት ኢትዮጵያ ሃብቷን እንዳትጠቀምና ዜጎቿን ለመታደግ እንቅፋት ቢገጥማትም ባለፉት አስር ወራት በዘርፉ የታየው እድገት በንፅፅር አድጓል። ለዚህም ይመስላል ወርቅ ” ቀጣዩ የኢትዮጵያ ጉሮሮ” እየተባለ ያለው።

ዛሬ ላይ ማእድን በተለይም ወርቅ የኢትዮጵያ ጉሮሮ እየሆነ መምጣቱን አሃዞች ያሳያሉ። የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ታከለ ዑማ ከሳምንት በፊት በማህበራዊ ገጻቸው ላይ “ስለማደግና ባለን ላይ ስለመጨመር እያሰብን የሀገርና የህዝብ ሀብት ይዞ ማባከንን አንታገስም” በሚል ዘርፉን በሚቻለው ሁሉ ተንቀሳቅሶ የገቦ ምንጭ ለማድረግ እንደሚሰራ አመልክተው ነበር።

በታናናሽ ከተሞች የአስተዳዳሪነትን ስራ ጀምረው ከለውጡ ማግስት አዲስ አበባን በከንቲባነት የመሩት ታከለ ኡማ፣ሰሞኑንን ይፋ እንዳደረጉት ከፖሊሲ ማሻሻያ በሁዋላ ኢትዮጵያ ባለፉት ተከታታይ ወራት ለውጭ ገበያ አቅርባ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ካገኘችባቸው ዘርፎች መካከል የማዕድኑ ኤክስፖርት በተለይም ከወርቅ የተገኘው ገቢ ጨምሯል።

ባለፉት 10 ወራት ብቻ ከ5 ሺህ 921 ነጥብ 52 ኪሎ ግራም የማዕድን ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ 6 ሺህ 785 ነጥብ 42 ኪሎ ግራም ያህል ወርቅ ለሽያጭ ማቅረብ ተችሏል። በዚሁ አሃዝ መሰረት 513 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። ለማግኘት የታቀደው 501 ነጥብ 73 ሚሊየን ዶላር በመሆኑ ከዕቅድ በላይ ሆኗል። ከወርቅ ብቻ የተገኘው 504 ነጥብ 73 ሚሊየን ዶላር ነው። ገቢው እንደሚያሳየው ወርቅ ቡናን እየተካ መሆኑንን ነው።



ታከለ ኡማ ስኬቱን ባነሱበት መግለጫቸው ለማልማት ፈቃድ ወስደው ወደስራ መግባት ያልቻሉ ፣ ስራውን በተጓተተ መልኩ ያከናወኑ እና ቃል በገቡት መሰረት ማከናውን ያልቻሉ ስልሳ ሶስት ተቋማት ፈቃድ ተነጥቀው መሰናበታቸውን አመልክተዋል። ፖሊሲው ለሚሰሩ ምቹ አድርጎ ገቢን ለማተናከር የተሰራውን ያህል ውላቸውን አክብረው ባልተገኙት ላይም በተመሳሳይ ደረጃ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።

መግለጫውን ከመስጠታቸው ቀደም ብለው “ከዚህ ቀደም የተፈጥሮ ጋዝ፣ የነዳጅ ድፍድፍ የማዕድን ፍለጋና ማልማት ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ ያልገቡ ተቋማት ላይ እርምጃ እንደወሰድን ሁሉ አሁንም የህዝብ ሀብት ይዘው ወደ ስራ ያልገቡ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዳችን የሚቀጥል ይሆናል።በቅርቡም፦ የገቡትን ውልና ስምምነት ማክበር ባለመቻላቸው ፈቃዳቸውን የተነጠቁ ተቋማትን ዝርዝር ይፋ የምናደርግ ይሆናል” በሚል አስጠንቀቀው ነበር።

“የህዝብ ሀብትን ማባከን ከፈቃድ ስረዛ በላይ በህግ ፊት የሚያስጠይቅም ይሆናል፤ምክያቱም ስለ ዕድገት እና ብልፅግና ማሠብ ኢንዱስትሪ ዕድገት እና መስፋፋት ፣ ከግብርና ምርታማነት እንዲሁም የወጪ ንግድ በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግን ይጠይቃል።መንግሥትም የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ዕድገት መሰረት መሆኑን አምኖ አንዱ የዕድገታችን ምሶሶ ያደረገውም ለዚህ ነው።ምሶሶው እንዲጠነክርም ህግ እያስከበርን፣ያለንን እያዳበርንና አዲስ ነገር እየጨመርን የምንጓዝ ይሆናል” ሲሉ የማዕድን ዘርፉ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠው ሚኒስትሩ አክለው ገልጸዋል

የሚድሮክ ለገደንቢ ወርቅ 537 ኪ.ሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ማድረጉን ገልጸዋል። ይኸው ተቋም እግድ ከተጣለበት ሁለት ዓመት በሁዋላ እንደገና ወደማምረት ተመልሶ ይህን ያክል ወርቅ ማምረቱ እንደ ስኬት ነው የተገለጸው።

በብክለት ወንጀል ተከሶ የታገደው ሚድሮክ ለገደንቢ ወርቅ ውሉ ለ30 ዓመታት ከታደሰ በሁዋላ ቢታገድም መደረግ ያለበት ተደርጎ ወደ ስራ እንደተመለሰ በተለያዩ አጋታሚዎች ተገልጿል። አካባቢውን ሊበክል በማይችልበት አገባብ እንዲሰራ ከተለያዩ የአስተዳደር አካላትና ከመንግስት በተውጣጡ ክፍሎች፣ የጤና ባለሙያዎች የተካተቱበት ጥናት ከተካሄደ በሁዋላ ሚድሮክ ወደ ስራ መመለሱን ታከለ ኡማ አመልክተዋል። ይህ ሁሉ ከሆነ በሁዋላ ነው ሚድሮክ የተጠቀሰውን መጠን ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ ማቅረብ የቻለው።

ሚድሮክ ቀደም ሲል ለሰላሳ ዓመታት ውሉ ሲራዘምለት ያልተካተቱ ጉዳዮች በዳግም ድርድር እንዲሻሻሉ መደረጉን ሚኒስትሩ ይፋ ባያደርጉም ሌሎች ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ አስታውቀዋል። በዚሁ መሰረት ቀደም ሲል በውሉ ያልነበረ የዘጠኝ በመቶ የተጣራ ትርፍ ድርሻ ለኦሮሚያ ክልል ገቢ ያደርጋል። የፊደራል መንግስት ሰላሳ አራት በመቶ ይጠቀማል። ይህ ስሌት በአዲሱ ድርድር መሰረት የተሰላ ሲሆን ግብርና ለሎያሊቲ ክፍያን አያካትትም።

በአሁን ሰዓት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ወርቅ የማምረቱ ስራ እንዲስፋፋ እቅድ ተያዞ እየተሰራ ሲሆን በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ሳካሮና የወርቅ ማምረቻ እውን ለመሆን እየተቃረበ መሆኑ ተመልክቷል። አሁን ስራ ላይ ካሉት በተጨማሪ አዲሶቹ ስራ ሲጀምሩ ገቢው ከፍተኛ ይሆናል።

ኢትዮጵያ ሰላሟን ማስጠበቅ ከቻለችና የተረጋጋ ሁኔታ ከተፈጠረ ከማዕድን ዘርፍ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ለውጥ ለማስመዝገብ እንደምትችል በዘርፉ የተሰማሩ እየገለጹ ነው። ኢንቨስትመንት ሰላም ስለሚፈልግ በዚሁ ዘርፍ ብዙ መሰራት እንዳለበት እሙን ነው።


Exit mobile version