ETHIO12.COM

በትግራይ ከተረጂዎች ጉሮሮ ተዘርፎ በስምንት ጭነት መኪና ሲጓጓዝ የነበረ እህል አዲ ጉደም ተያዘ

ከተረጂዎች የተዘረፈው እህል በዚህ መልኩ ሲያዝ የሚያሳይ ስዕል ኢቲቪ

ከትግራይ ክልል በስምንት መኪናዎች ተጭኖ በህገ ወጥ መንገድ ሊወጣ የነበረ 800 ኩንታል የዕርዳታ እህል አዲ ጉደም ኬላ ላይ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አሰተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በድርጊቱ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን በህግ ጥላ ስር አድርጎ እያጣራ እንደሚገኝም ኮሚሽኑ ገልጿል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አሰተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መንግስትአብ የማነ ለኢቢሲ እንደገለጹት፤ በክልሉ ለስብዓዊ ድጋፉ የመጣውን የእርዳታ እህል ከተረጂው ሰው ጎሮሮ ቀምተው ለግል ጥቅማቸውና ብልፅግናቸው ሲሯሯጡ የነበሩ ነጋዴዎች ናቸው፡፡

ከእነዚህ ሰዎች ጀርባ የነበሩ እነማን እንደሆኑ ፖሊስ በምርመራ እያጣራ ይገኛል። በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር የማነ ገሰሰው በበኩላቸው ተደራጅተው እህልን ከዚህ አከባቢ በመግዛት ወደ ተለያዩ ቦታዎች በመውሰድ እጥረት በመፍጠር በትግራይ ረሃብና ችግር እንዲፈጠር የሚያደርጉ አካላት መኖናረቸውን ገልጸዋል፡፡

የወንጀል አፈጻጸሙ በተደራጀ መንገድ መሆኑንም የገለጹት ረዳት ኮሚሽነሩ፤ በዚህ ህገ ወጥ ድርጊት ውስጥ በየዋህነት የሚሳተፉ ባለሞያዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉም አሳስበዋል፡፡ ከዚህ በፊት በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረው ሶስት ሺህ ኩንታል የእርዳታ ዕህል መያዙን የገለጸው ፖሊስ በወንጀል ድርጊቱ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ሆነው ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል፡፡

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ፣ ከዚህ የከፋ ችግር ስለሌለ ህብረተሰቡ በንቃት መሳተፍ ይኖርበታል፡፡ ከህገ ወጥና ስግብግብ ነዳዴዎች በስተጀርባ ያለ ማንኛውም አካል ከህግ ተጠያቂነት እንደማያመልጥ ማወቅ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ የመቀለ ከተማ ጊዜያዊ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር ግዛው ሐጎስ በበኩላቸው፣ ይህ ህገ ወጥ ተግባር በመጀመሪያው እርዳታ አሰጣጥ ላይ መከሰቱን ጠቅሰው በሁለተኛው ዙር ላይ ይሄ እንዳይደገም በጥብቅ ቁጥጥር እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።


Exit mobile version