ETHIO12.COM

የአሜሪካ መንግስት የጣለው የቪዛ ክልከላ የዓለም አቀፍን ህግ የጣሰ መሆኑን ምሁራን ገለጹ

የአሜሪካ መንግስት ከአሸባሪው ጁንታ ጎን በመቆም የጣለው የቪዛ ክልከላ የዓለም አቀፍ ህግን የጣሰ መሆኑን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ምሁራን ገለጹ፡፡

በዩኒቨርሲቲው የዓለም አቀፍ ህግ መምህር ዘሪሁን ቦዳ እንዳሉት፤ አንድን ማዕቀብ ሊያስጥል የሚችሉ የዓለም አቀፍ ህግ ዕውቅና የሰጣቸው ጉዳዮች ቢኖሩም ያለበቂ ምክንያት የጆባይደን መንግስት በኢትዮጵያ መንግስት ያስተላለፈው የቪዛ እገዳ ተገቢነት የለውም፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ዙሪያ እየሰራ ባለበት በአሁኑ ወቅት የተላለፈው ውሳኔ የዓለም አቀፍ ህግን የጣሰ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም ሰላምና ፀጥታ በጎ ሚና ከማበርከቷ ውጭ ደንቃራ ሆና አታውቅም ያሉት ምሁሩ የሀገሪቱ ዳር ድንበር በሚጠብቁ የሰሜን እዝ መከላከያ ሠራዊት ላይ አሰቃቂ ጥቃት በፈጸመው አሸባሪው ጁንታ ላይ የወሰደችው የህግ ማስከበር እርምጃው ከህግ አንፃር ተቀባይነት ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከጁንታው ህወሃት ጋር ሰላምና እርቅ ለመፈጸም በተለያዩ ታዋቂ ሰዎች፣በሀገር ሽማግሌዎችና ሃይማኖት አባቶች በመታገዝ የኢትዮጵያ መንግስት ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም አሸባሪው ቡድን አሻፈረኝ በማለቱ ሊሳካ አለመቻሉን አውስተዋል፡፡

ለኢትዮጵያ ህዝብ ጠንቅ በሆኑ የውስጥ ቡድኖች ላይ ህግ ለማስከበር የትኛውንም አገርና መንግስት ማስፈቀድ አይጠበቅም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሉዐላዊ ሀገር እንደመሆንዋ መንግስት የሀገሪቱን ህግ የማውጣት፣ ፖሊሲ የመቅረጽና ሰላም የማስከበር መብት እንዳለው ጠቅሰው በጂንታው ህወሃት ላይ የተወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃም ከውስጥ ሉዐላዊነቷ ማስከበር የመነጨ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አሸባሪው የህወሃት ጁንታ በኢትዮጵያ የሰሜን እዝ ሠራዊት ላይ፣ በማይካድራ እና ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢ ህዝቦች ላይ ዘግናኝ ድርጊት ሲፈጽም እንዲሁም ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ ወረራ ስታካሂድ ምንም ያላለው የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ሊያስገባ የሚችል ህጋዊ መሠረት የሌለው ነው ብለዋል፡፡

አሜሪካ ያለበቂ ጥናት በኢትየጵያ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ላይ ማዕቀብ መጣሏ ተገቢነት እንደሌለው የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የህግ መምህር ዳግም ወንድሙ ናቸው፡፡

ማዕቀብ የሚጣለው በዘፈቀደ ሳይሆን የዓለም አቀፍ ህግ ተጥሶ ሲገኝ እንደሆነ ጠቅሰው አሜሪካ በጉዳዩ በቂ ጥናት ሳታደርግ ፈጥና ወደ እርምጃ መግባቷ ተገቢነት የለውም ብለዋል፡፡

ከቀድሞ የአሜሪካ መንግስት ጀምሮ በኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ጥልቅ ማስረጃ ሳይኖራቸው ግብፅንና ሱዳንን ለማስደሰት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገባች መሆንዋ የዴሞክራሲን መሰረት ከጣለች ሀገር የማይጠበቅ ተግባር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ጁንታው ህወሃትና ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ አንዳንድ የዓለም አቀፍ የዜና አውታሮችም ችግሮችን የተረዱበት መንገድ ከእውነታው የራቀ ነው ብለዋል፡፡

የትግራይን ክልል እንደሉዐላዊ ሀገር አድርገው ማሰባቸው ተገቢ አለመሆኑን ጠቅሰው ትክክለኛ ችግሩን ያልተረዳች አሜሪካ ትክክለኛ መፍትሄ ልትሰጥም አትችልም ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የሉዐላዊነት ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም ያሉት ምሁሩ በሀገር ውስጥና ውጭ ያሉ የኢትዮጵያ ዜጎች ድምፃቸውን ልያሰሙ እንደሚገባቸው አመላክተዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ሃላፊ መምህር ካሱ ጡሚሶ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያና አሜሪካ መካከል በፖለቲካ፣ንግድና ዲፕሎማሲ ግንኙነት ረገድ ረዥም ጊዜ ታሪክ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር እንደመሆንዋ በዓለም ፖለቲካ ላይም ያላት ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት መምህር ካሱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅትና በአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ሚና እንዳላት ጠቅሰዋል፡፡

አሜሪካ በራሷ የውስጥ ጉዳዮች ሌሎች ሀገራት ጣልቃ እንዲገቡ እንደማትፈልግ ሁሉ በኢትዮጵያም የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንድትገባ ማንም አይፈቅድም ብለዋል፡፡

ዴሞክራሲን በመገንባት በዓለም ግንባር ቀደም የሆነችው አሜሪካ በሀገሯ እየተፈጸመ ያለው ሰብአዊ መብት ረገጣ ማስቆም ያቃጣት በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ማሳብ ተገቢነት እንደሌላ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአሜሪካ ድጋፍ ብቻ የምትኖር ሀገር ባለመሆንዋ ከአሜሪካ ለምታገኘው ጥቅም ስትል ሉአላዊቷንና ብሔራዊ ጥቅሟን ለማንም አሳልፋ እንደማትሰጥ መገንዘበ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

ENA

Exit mobile version