Site icon ETHIO12.COM

አሜሪካ በሌሎች አገራት የምታደርገውን ጣልቃ ገብነት እንድታቆም ቻይና አሳሰበች


አሜሪካ በሌሎች አገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ የምታደርገውን ጣልቃ ገብነት በማቆም የሀሰት መረጃ ከማሰራጨት እንድትቆጠብ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሳስቧል።

አሜሪካ በራሷ የውስጥ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የገዛ ዜጎቿን ደህንነት ማረጋገጥ እንደሚገባትም የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ዣኦ ሊጂያን በሰጡት መግለጫ አሳሰበዋል።

ቃል አቀባዩ ዣኦ ሊጂያን ይህንን የተናገሩት በአሜሪካ በፖሊስ መኮንን በተገደለው ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ አንደኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ ከመገኛና ብዙሀን ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ነው።

ቃል አቀባዩ ዘር ተኮር ያደረጉ ጥቃቶች በአሜሪካ ውስጥ ዋና ዜና ሆነው ቀጥለዋል ብለዋል።

በፍሎይድ የፍርድ ሂደት ባሉት 21 ቀናት ውስጥ ብቻ በአሜሪካ 64 ሰዎች በፖሊስ በጥይት የተገደሉ መሆናቸውን መረጃዎች እንደሚያመለክቱ የገለጹት ዣኦ እነዚህ የተገደሉ ሰዎች አብዛኛዎቹ የቆዳ ቀለማቸው የተለየ መሆኑን ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ እንዳሉት በተደረገው የሕዝብ አስተያየት ጥናት መሠረት ባለፉት ዓመታት በአፍሪካ-አሜሪካውያን እና በአሜሪካ ፖሊሶች መካከል ያለው ግንኙነት ወደ ከፋ እና የተባባሰ ቀውስ እየተሸጋገረ ነው።

72 በመቶ የሚሆኑት አፍሪካ-አሜሪካዊያን በሰጡት መልስ ወጣት አፍሪካ-አሜሪካውያንን እና ሌሎች አናሳ የህብረተሰብ ክፍሎች በፖሊስ የሚደረገው ተኩሶ መግደል እየተባባሰ መምጣቱን ተናግረዋል።

የጆርጅ ፍሎይድ ሞት በአሜሪካ ውስጥ የዘረኝነትን ጫፍ የሚያንፀባርቅ ነው ሲሉ ዣኦ ገልፀው 60 በመቶ የሚሆኑት አሜሪካውያን ዘረኝነት “እጅግ የከፋ ችግር ነው” ብለው ያምናሉ ብለዋል።

ቃል አቀባዩ አሜሪካ በራሷ ጉዳይ ላይ እንድታተኩር፣ የራሷን ችግሮች እንድትፈታ፣ የዜጎቿን ደህንነት እንድትጠብቅ እንዲሁም በነጻነት እንዲተነፍሱ እና ከፍርሃትና አድልዎ የመላቀቅ መብት እንዲሰጣቸው አሳስበዋል።

በሁሉም ቦታ ችግር በመፍጠር በሌሎች አገራት ውስጣዊ ጉዳዮች ጣልቃ በመግባት የምታሰራጨውን ሀሰተኛ መረጃ እንድታቆም ዣኦ አሳስበዋል ሲል የዘገበው ሺንዋ ነው። via EBC

Exit mobile version