Site icon ETHIO12.COM

ለ68 ዓመታት በሥራ ላይ የቆየውን የዳኝነት ክፍያ አገልግሎትን ለማሻሻል በቀረበ ረቂቅ ላይ ውይይት ተካሄደ



ከ1945 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ የቆየውን የፌደራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ክፍያና የአከፋፈል ሥርዓትን ለማሻሻል በቀረበ ረቂቅ ላይ ውይይት ተካሄደ።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አመራሮች፣ ዳኞች፣ ጠበቆችና የህግ ባለሙያዎች በውይይቱ ተሳትፈዋል።

በውይይት መድረኩ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ፣ ምንም ማሻሻያ ሳይደረግበትና ትኩረት ሳያገኝ ለረጅም ጊዜ የቆየው የዳኝነት ክፍያ የፍርድ ቤትን ተደራሽነት በማያጣብብ መልኩ ህብረተሰቡ ከደረሰበት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብር አንጻር ዘግይቶም ቢሆን ለማሻሻል ረቂቅ ደንቡ መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡

ረቂቅ ደንቡ የተዘጋጀበት ዓላማ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ለሚሰጡት አገልግሎት ተመጣጣኝ የሆነ የዳኝነት ክፍያ እንዲያስከፍሉ ለማስቻል፣ የዳኝነት ክፍያን ፍርድ ቤቶች እንዲያስተዳድሩ በማድረግ ዘመናዊና ቀልጣፋ የዳኝነት አገልግሎት ለህብረተሰቡ በመስጠት የዳኝነት ነጻነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም የዳኝነት ሥርዓቱ ለዜጎች ተደራሽ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር መሆኑ ተገልጿል፡፡

በውይይት መድረኩ የተሰጡ አስተያየቶችን በረቂቅ ደንቡ ውስጥ በማካተትና የመጨረሻ ቅርጽ በማስያዝ ረቂቅ ደንቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተልኮ ውይይት ተደርጎበት እንዲጸድቅ ይደረጋል ተብሏል።

የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ ጸድቆ ተግባራዊ ለማድረግ ፍርድ ቤቶች በዝግጅት ላይ መሆናቸው፣ መመሪያውን ሥራ ላይ ለማዋል ፍርድ ቤቶችና ዳኞች ብቻቸውን ተግባራዊ ሊያደርጉት የማይችሉ በመሆኑ ከጠበቆችና ከአቃቢያነ ሕግ ጋር ውይይት እንደሚደረግም በመድረኩ ላይ ተጠቅሷል፡፡

ከዚህ ቀደም የፍርድ ቤትን አወቃቀርና ሥልጣንን የሚመለከተው የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ እና የዳኞች አስተዳደር አዋጅ መጽደቃቸው ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ተጨማሪ የመረጃ አማራጮቻችን ‼

(ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version