Site icon ETHIO12.COM

ራስን በራስ የማጥፋት ወንዝን የማድረቅ ብልህ ትግል

ኃላፊነት የጎደለው ፖለቲካ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚለቀቀው ብሽሽቅና አላታሚ ፕሮፓጋንዳው፣ እንዲሁም መሬት ላይ የሚከሰተው በካራ፣ በእሳትና በባሩድ የሚፋፋም ቀውስ፣ ወዘተ… እነዚህ ሁሉ ካፊያዎችና ዶፎች የሚፈጥሯቸው ጅረቶች የሚፈሱት ወደ አንድ ትልቅ ወንዝ ነው፡፡ ማለትም የኢትዮጵያን ሕዝቦች አባልቶ አገር የለሽና ሰላም የለሽ ገሃነም ውስጥ የመክተት ትልቅ ወንዝ ውስጥ፡፡ የዚህ ወንዝ ሌላ ስሙ ራስን በራስ የማጥፋት አትራፊ አልባነት ነው፡፡

ወደ እዚህ ወንዝ በሚመሩት የጥፋት እንቅስቃሴች ውስጥ ሕዝብ (በተለይም ዋናው የጦስ ዶሮ አማራ)፣ መከላከያና ሌሎች የፀጥታ አካላት ሁሉ ዋጋ መክፈላቸው ቀጥሏል፡፡ ዋጋ ክፍያው እስከ መቼ!!!?

እውነታችንንና ከእውነታችን የበቀለውን በጥባጭ በቅጡ የተረዳ ትልም

በዚህ ትግል ውስጥ ተቀዳሚው የአስተዋይነት ተግባር፣ የኃይል ሚዛንን፣ ነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታዎችን በቅጡ መረዳት ነው፡፡ ራስን በራስ የማጥፋት ወንዝ በአሁኑ ወቅት ብቻውን አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብት ሰንካላ (ትንሽ) የማድረግ የግብፅና የሱዳን ፍላጎት በግርግር መሬት ከመቦጨቅ የሱዳን ፍላጎት ጋር ተወሳስቦ ተገናኝቷል (የነገረኛ ጎረቤቶቻችን ፍላጎት ኢትዮጵያ ላይ ቀጥተኛ ጦርነት ከመክፈት አንስቶ በእጅ አዙር በታጠቁ የውስጥ ‹‹ትግሎች›› ሽፋን እስከማመስ ተግባራዊ ፈርጅ አበጅቷል፡፡ ምዕራባዊ ጫናም በውስብስቦሹ ውስጥ አለበት፡፡ የምዕራባዊው ጫና በኃይል ሚዛን ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ኢትዮጵያ ውስጥ ሥውር እጅ የመስደድ፣ በማዕቀብ የማፈን፣ ተጨማሪ የጎረቤት ባላጋራ በጉርሻ የመግዛትና አበሳ የማብዛት ቅንብር ሊኖረው ሁሉ ይችላል፡፡ ራስን በራስ የማጥፋት ወንዝን የማድረቁ ትግል አዲስ ቅራኔዎች ከውስጥም ከውጭም እንዳይፈለፈሉ ተጠንቅቆ በሚቻለው ሁሉ በአርበኝነት መቆም የሚችለውን የውስጥ ኃይል ሁሉ አንድ ላይ የማገናኘት፣ ከኢትዮጵያ ጎን የሚቆመውን የውጭ ድጋፍም እያበራከቱ፣ ከውስጥ ጣጣ ጋር የተጠላለፈውን ውጫዊ የኃይል ጉድኝት የማለዘብ/የመበተን ሥራ ላይ የመጠበብ ጉዳይ ነው፡፡ አገራዊውን የአርበኝነት ኃይል የማደርጀት ጉዳይም የውስጥና የውጭ በጥባጮች ውስጣችንን ሊያምሱ የሚችሉባቸውን ቀዳዳዎች ፈጥኖ ማመናመን፣ ከማመናመንም አልፎ አገራዊ አቅምን (በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ሰላምም ሆነ በሌሎች የጥቃት መመከቻዎች) ማጎልበት ነው፡፡ ይህ አገራዊ አርበኝነትንና የድል ፍሬውን እያበራከቱ የመጓዝ ስኬት፣ የቆምንበትን የውስጥ እውነታ በቅጡ ከመረዳት ጋር በቅርብ የተያያዘ ነው፡፡ ከእውነታችን ውስጥ ሁለቱን ሰበዞች ብቻ ላንሳ፡፡

የኅብረተሰብ ሥርዓተ-ኑሮ በወንፊቱ እያራገፈ ወራዳ የቁጭራ ኑሮ ውስጥ የሚያዘቅጠው የኅብረተሰብ ክፍል፣ ላዋረደው ማኅበራዊ ኑሮ አክብሮት የለሽነቱን በተለያየ መልክ ይገልጻል፡፡ ከኅብረተሰቡ ወግ፣ ባህልና እሴቶች ጋር የተጣላ ባህርይ ብዙ ጊዜ ያሳያል፡፡ ለሥነ ምግባር አይጨነቅም፡፡ ሆን ብሎ ነውረኛ የሚባሉ ነገሮችን ይፈጽማል፡፡ ጭካኔ መከፋቱን ማሳያ ብቻ ሳይሆን የኑሮ መሣሪያውም ይሆናል፡፡  ቀማኞችና ማጅራት መቺ የምንላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች እዚህ ምድብ ውስጥ ናቸው፡፡ የዚህ ዓይነት የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ የሚያጋጥመን ከሥነ ምግባርና ከርኅራኄ የተጣላ ባህርይ በየትም ዓለም የሚታይ ነው፡፡ በአገራችን ያለው የከሰረና ያበደ የብሔርተኛ ፅንፈኝነት፣ ትግል የሚባል ልብስ ውስጥ ሺሕ ጊዜ ለመደበቅ ይሞክር እንጂ ከማጅራት መቺነት በከፋ ደረጃ ወምኗል፡፡ የአገር መቀጠልና አለመቀጠልንም ሆነ የአገር መፋጀትንና አለመፋጀትን ምንተዳዬ እስከ ማለት ድረስ ጥፋትን ዓላማ አድርጓል፡፡ ርኅራኄ ቢስነትን፣ ጥላቻንና በቀልን ከአፍ እስከ ገደፉ ተሾሟል፡፡ የዚህ አረመኔያዊ ጥፋት ሾፌር፣ ‹‹የተማረ የተመራመረ›› (ዲግሪ በዲግሪ የሆነ)፣ የጎረቤቶችንና የምዕራብ አገሮችን ፍላጎትና ሥነ ልቦና በደንብ የሚያውቅ የልሂቅ ወመኔ እንደ መሆኑም፣ የጥፋት ዓላማንና ስሜትን ብቻ የተሸከመ አይደለም፡፡ መሰሪነትንና የሸር ጥበብን በማዳወርም የተካነ ነው፡፡ ይህ ባህርይው ከባድ የማርከሻ ብልህነትን ይጠይቃል፡፡

በሌላ በኩል ክፍልፋይ ብሔርተኝነት በ30 ዓመታት የኑሮ ልምድ ውስጥ የፈጠረው የተቆራረሰ አስተሳሰብና የተቆራረሰ ‹‹ወገኔ›› ባይነት፣ ከክልሎች ደረጃም ወደ ዞንና ወረዳዎች ወርዶ እያባላ ብዙ ዕንባና ደም፣ ብዙ አመድ ማምረቱን እስኪያንገሸግሽን ዓይተነዋል፡፡ ዛሬም ፅንፈኞችና የውጭ ደጋፊዎቻቸው የሚበጠብጡን ይህንኑ ገመናችንን መሣሪያ አድርገው ነው፡፡ ይሁንና የብሔርተኛነት አናጪነት የፈለገውን ያህል የከሰረና ሬቱ የወጣ ይሁን እንጂ፣ መራራ አዝመራው የፈለገውን ያህልም ያስመርረን እንጂ፣ ገና ሕዝብ ድረስ የገባ ድጋፍ ያለው ዕዳ ነው፡፡ የማይጣጣሙ ሁለት ገጾችን (ማስመረርንና ተደጋፊነትን) አንድ ላይ ይዞ ሊገኝ የቻለውም በብሔርተኝነት ውስጥ አሉታዊና አዎንታዊ (ዴሞክራሲያዊና ፀረ ዴሞክራሲያዊ ነገሮች) ማለትም መብት ፈላጊነትና በቀለኛ ጨቋኝነት አንድ ላይ መተሻሸታቸው ስላልተቋረጠ ነው፡፡

ኅብረተሰብን በብሔረሰብ ማንነት/በቋንቋ አንጓሎ በፓርቲ መደራጀትና ማኅበረሰቦችን አበላልጬ ልግዛ ባይነት ፀረ ዴሞክራሲያዊው የጭቆና ፈርጅ ነው፡፡ ይህ ፈርጅ ጥላቻና በቀልን እየተመገበና እየመገበ ‹‹እንደሰባበርከኝ እሰባብርሃለሁ›› እስከሚል ፋሺስታዊ አራጅነት ድረስ ሊተባ ይችላል፡፡ የሸኔም ሆነ የሕወሓት ወፈፌዎች የዚህ ትባት ማስረጃዎች ናቸው (በእነሱ ድርጅታዊ መዋቅር ውስጥ ያልገባ፣ ግን እነሱ እንዲህ አደረጉ ሲባል አንጅቱ ቅቤ የሚጠጣ፣ የግርግር አጋጣሚ ቢያገኝ የእሱም አውሬው የሚወጣ፣ ጥላቻና ጭካኔ የጨረሰው ሰው በየጓዳው ጥቂት አይደለም)፡፡ ብሔርተኛ አንጓላይነት (ከእነ ፓርቲያዊ አደረጃጀቱና የበቀል ጥማቱ) ከዴሞክራሲና ከእኩልነት መንፈስ ጋር አብሮ አይሄድም፣ አንዱ ሌላውን ይገዘግዛል፣ አንዱ ሌላውን ያጠፋል፡፡

በብሔርተኝነት ውስጥ ያሉት የብሔረሰቦች መብቶችና የእኩልነት/የፍትሐዊነት ጉዳዮች የዴሞክራሲ አካል ናቸው፡፡ በብሔርተኝነት ውስጥ ያለውን የዘይትና የውኃ ዓይነት የማይግባባ ጉድኝት ከተረዳን፣ በዚህ ደረጃ ላይ ልናተኩርበት የሚገባ የድል ፍሬ፣ የጭቆናና የበቀል ወገን የሆነውን አግላይ አበላላጭነትን እዚያው ከጭቆና ወገኖቹ ጋር ትቶ የዴሞክራሲና የእኩልነት ወገን የሆኑትን የብሔረሰብ መብቶችና የፍትሐዊነት ጉዳዮች ወደ ዴሞክራሲ ሠፈራቸው ማምጣትና ከሌሎች መብቶች ጋር አስማምቶ መንከባከብ ነው፡፡ በአሁኑ ደረጃ በዚህ ግብ ላይ ያልተመጠነ፣ ብዙ ነገሮች ፈላጊነት (ለምሳሌ ሕገ መንግሥት ቅድሚያ ይቀየር ባይነት)፣ አስጠቂና ኃይል በታኝ ጀብደኝነት ነው፡፡ ከዚህ ዓይነቱ ቅብጥብጥነት ርቆ፣ ባለንበት ሁኔታ ሊገኝ በሚችለው በተጠቀሰው ስኬት ላይ ማተኮር ያልቻለ ለውጠኝነት የተግባር ለውጠኝነቱ ያጠያይቃል፡፡ በዚህ ደረጃ ላይ ከብሔር አግላይ አስተሳሰብና አደራጃጀት ወደ ኅብረ ብሔራዊነት የመጡ ቡድኖችና ግለሰቦች እንዳያገርሽባቸው የሚያደርግ፣ ገና ያልመጡትን እንዲመጡ የሚስብ፣ ፅንፈኞችን ይበልጥ የሚነጥልና/የሚያደክም መለኛ ትግል ይህንን አቋም የያዘ ነው፡፡ በዚህ የድል ፍሬ ላይ አነጣጥረን እሱን እያቀነቀንን፣ ከፊታችን ያለው ምርጫ በተዓማኒነቱ ተሳክቶለት፣ ምጥኑ ኅብረ ብሔራዊነት የሕዝቦችን አብላጫ ድምፅ ካሸነፈ፣ ይህ በራሱ በአግላይ አደረጃጀት ላይ ትልቅ ድል ነው፡፡

ባለው ሕገ መንግሥት ውስጥ የዴሞክራሲ አስተዳደርን ከታች እስከ ላይ ማደራጃቱ ከያዘልን ደግሞ ኅብረ ብሔራዊ የሆኑት እንደ ብልፅግና ያሉ ፓርቲዎች በጥንቅራቸው ይበልጥ ኅብረ ብሔራዊነታቸው እየበለፀገ የሁሉ ማኅበረሰብ የትግል መድረክ ይሆናሉ፡፡ በየክልሉ፣ በየዞኑና በየወረዳው ሌሎች ብሔርተኛ ቡድኖችም ሁሉን አካታች ወደ መሆን አዝማሚያ መግባታቸው ይጨምራል፡፡ በዴሞክራሲ የትድድር ልምምዳችን ውስጥ ከድል የሚቆጠር ሌላ ኑሮገብ ዕውቀትም ይገኛል፡፡ የብሔረሰብ መብትን ማክበርና ማስከበር፣ በብሔር ተነጥሎ መደራጀትንና ባለቤትና መጤ ብሎ ማንጓለልን፣ እንዲሁም ይዞታዬ ይሠራልኝና የማንነት ታርጋ ልለጥፍ ማለትን እንደማይሻ ይታያል፡፡ የራስ በራስ አስተዳደር መልከ ብዙና ዕርከነ ብዙ እንደሆነ (አጥርም እንደማይሻ)፣ የዴሞክራሲ አስተዳደር በባህርይው ብዙኃን የሆነውን ወገን የማንፀባረቅ ችግር እንደሌለበት፣ እንዲያውም ፈተናው የንዑሳኑ መብትና ጥቅም በብዙኃኑ እንዳይዋጥ የመጠበቅ ጉዳይ መሆኑ በደንብ ልብ ይባላል፡፡ የዚህ ዓይነቱ ልምምድ የሚያስገኘው ትምህርት በራሱ፣ ሕገ መንግሥቱን ሳይጽፉ የማሻሻል መቅድምና መግቢያ ነው፡፡ በዚህ መልክ የተጀመረው አሻሻይነት እየጎለበተ ጊዜውን ጠብቆ (የፓርቲ መቅበጥበጥ ሳያስፈልገው) ዕውን ይሆናል፡፡ ያውም ‹‹አሃዳዊነት መጣ! ለውጡ ተቀለበሰ! የብሔር ብሔረሰብ መብት ተሰናበተ!›› የሚል ቀጣፊ ጩኸት ላጭበርብርህ ብሎ ሳይደፍረው፡፡ በዚያ መቅድማዊና መግቢያዊ ጅምር ላይ፣ እንዲህ ያሉ ማጭበርበሪያዎች ብቅ ቢሉ አገር ከመደናገር ይልቅ እየሳቀ ይዝናናባቸዋል፡፡

እዚህ ትልም ላይ ምን ያህላችን ተገናኝተናል?

አሁን ካሉት የፖለቲካ ቡድኖች ውስጥ ሁኔታዎች በሚፈቅዱት ልክ ግባቸውን መጥነው የሚታገሉና የሚያታግሉ ምን ያህል ናቸው? ብለን ብንጠይቅ የሚያስመካ መልስ ማግኘታችን ያጠራጥራል፡፡ በምርጫ ዘመቻው ውስጥ ከታዩት ቡድኖች መሀል፣ ከብልፅግና በቀር በዚህ አቅጣጫ ውስጥ ግልፅ አቋም ይዞ የታየ ነበር ብሎ ማለት ይቸግራል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከድርጅታዊ ሚጢጢነት ሌላ፣ በፖለቲካ ብስለትና የኢትዮጵያን ወቅታዊ ፈታኝ ሁኔታ ባስተዋለ ጠንቃቃነት ረገድ የታዩት ጉድለቶች፣ በቀጣዩ አምስት ዓመታት ውስጥ እንኳ አገር አቀፍ በሆነ ድጋፍ ብልፅግና ፓርቲን የሚፎካከርልን አማራጭ ፓርቲ ስለማግኘታችንም እንድንጠራጠር የሚጫኑ ናቸው፡፡

በፓርቲዎች የምርጫ ዘመቻ ሐተታዎችና ክርክሮች ላይ ያየናቸው የአቋም ፈሮች ወደ 50 ከተጠጋ የድርጅት ብዛት ይልቅ፣ ቢበዛ በአራት ፓርቲ አካባቢ ሊሰባሰቡ ይችሉ እንደነበር የጠቆመ ነው፡፡ የትውፊት አጥባቂና የቀኝ መስመር ተከታይ የሆኑት አንድ የፓርቲ ፈር ውስጥ ናቸው፡፡ በእነሱ ትይዩ ደግሞ የሶሻል ዴሞክራሲ ፈር ሠፈርተኞች አሉ፡፡ ብሔርተኛ ከሆኑት ውጪ ቀሪዎቹ በሁለቱ ፈሮች መሀል መግባት የሚችሉ ናቸው፡፡ በአንድ ፈር (የመስመር ሠፈር) ውስጥ ዥንጉርጉር ሐሳቦችና ስንጣሪ ዝንባሌዎች መላወሳቸው የፓርቲ አመለካከታዊ ሥምረትን የሚንድ ዕዳ አይደለም፡፡ በአንድ ፓርቲ ውስጥ መሬት በግል ይሁን/የለም የወል መሆን አለበት የሚሉ ሐሳቦች እየተከራከሩ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ፓርቲን ወደ መፍረስ የሚወስደው ሐሳቦችን የማድበስበስና የማፈን ኑሮ ነው፡፡ ይህ ይታወቅ ከነበረ ቁጥቋጦዎቹ ‹‹ፓርቲዎች›› እየተቀላቀሉ የጎሉ ጥቂት ፓርቲዎች ሆኖ ብቅ ለማለት ምን እንደ ቸገራቸው ግራ ያጋባል፡፡ የቱ ቡድን የትኛው የፈር ሠፈር ውስጥ እንደሆነ ጥረት ባደረግሁበት ጊዜ ከብልፅግና ጋር ተቀላቅሎ ለመሥራት በጣም ቅርብ የሆነ ቡድንም እንዳለ አስተውያለሁ፡፡ የጊዜው ማጠር በተዋሀደ ትልልቅ ፓርቲነት ደረጃ ለመምጣት አላዳረሰንም ቢባል እንኳ፣ መቶ ምናምን የቡድኖች ቁጥር ከነበረበት ጊዜ አንስቶ ለምርጫ እስከ መመዝገብ በነበረው ጊዜ ውስጥ፣ ቢያንስ በግንባር ደረጃ ገዝፎ መምጣት ይቻል የነበረበት ዕድል ነበር፡፡ በዚህ ዕድል ከመጠቀም ምን ከለከለ? ትንንሽ የጎበዝ አለቃና ባለርስት ሆኖ ስም መትከል ዛሬም እያናወዘ ይሆን? በዴሞክራሲያዊ አሠራር ትልቅ ድርጅታዊ አውታር ፈጥሮ በአንድ የአመራር ቡድን ውስጥ መግባት፣ ለጌታ ከማደር ጋርና ከማን አንሼ ከማለት ጋር እየተሳከረ አስቸግሮ ይሆን?

ይህንን የአስተሳሰብ ችግር ምክንያት ለማድረግ መከጀል ሲሞካክረን ደግሞ፣ የኢሕአፓ ሙጣጮች የድሮ ስማቸውን ይዘው የመጡት ምን እናተርፋለን ብለውና ለአዲሱ ትውልድ ምን እናወርሳለን ብለው እንደሆነ ለመረዳት ይቸግራል፡፡ ኢሕአፓ ነን ባይ ወጣቶች የማያውቁትን ድርጅት እያሞጋገሱ ሲመኩበትና ደርግና ሕወሓትን ሲነቅፉ ሲታይም፣ ኢሕአፓ በፖለቲካ ሜዳው ውስጥ ከእኔ በቀር ማን ተላውሶና ማን ተንፍሶ በማለት ከደርግ ኢሠፓና ከሕወሓት/ኢሕአዴግ ሩቅ እንዳልነበረ፣ ሥልጣን ይዞ ቢሆን ኖሮም ሰቅዞ በመግዛት ባህርይ ከእነሱ የማይተናነስ እንደነበረ የሚያስገነዝባቸው ጠፋ ወይ ያሰኛል፡፡ ‹‹እናት›› ለፓርቲ መጠሪያ መዋሉና ‹‹እናትን ይመርጧታል እንጂ አያወዳድሯትም›› የሚል መፈክር ለፖለቲካ ንግድ ምልክት መደረጉም፣ በሕዝብ አስተዳደር ግንባታ ውስጥ የሕዝብ እንደራሴ ለመሆን በመብቃትና በእናትነት መሀል ያለውን ትልቅ ልዩነት የመረዳት የፖለቲካ ‹ሀሁ›ም እንዳልተጨበጠ የሚጠቁም ነው፡፡ ‹‹አብን›ን መምረጥ ኢትዮጵያን መምረጥ ነው›› በሚለው መፈክር ውስጥም የብሔር ቡድንነትን መምረጥና ኢትዮጵያን መምረጥ እንዴት እንደተጣጣሙ መረዳት ሌላ እንቆቅልሽ ነው፡፡

በሌላ በኩል የብልፅግና ፓርቲ በአምስት ዓመት የመርሐ ግብር መግለጫው (ማኒፌስቶው) ውስጥ ለሕገ መንግሥቱ ታምኖ የሚሠራ መሆኑን መግለጹ እንደ ቅሌት ተወስዶ ቡድኖች እንደማሳጫ ሲጠቀሙበት ማየታችን፣ ከዚህ ይባስ ብሎ፣ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ መንገድን በዘለለ አኳኋን ቅድሚያ ሕገ መንግሥት እንዲቀየር እናደርጋለን››፣ ‹‹መሬት የግል እንዲሆን አቅደናል›› የሚሉ ቡድኖችን መስማትም ዕጢ ዱብ ያደርጋል፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ ያለችበትን ሁኔታ ተረድቶ በመጪው አምስት ዓመት ሊሠራ የሚችለውንና የማይችለውን ለይቶ በማቀድ ረገድ፣ ለፅንፈኞች የማወናበጃ ስንቅ ላለመስጠት በመጠንቀቅ ረገድም የታየው ጮርቃነት፣ ‹‹ትዝብት ነው ትርፉ›› ተብሎ ልርሳህ የሚባል ዓይነት አይደለም (ኃላፊነት የሚሰማውን ጋዜጠኛ ያህል እንኳ የሚመጥን ቀውሰኞችን ያለ ማገዝ ጠንቃቃነት አንዳንዶቹ የፖለቲካ ቡድኖች ዘንድ አለማግኘታችን ‹‹ኧረ መላ በሉ›› የሚሰኝ ነው)፡፡

‹‹የለውጥ መንግሥት ከሆነ ዜጎችን ከጥቃት ይጠብቅ! … ፀጥታ ማስከበርና የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ ሥራህ ነው! መቼ ነው ሥራህን የምትወጣው? ንገረን!…›› እያሉ ያለውን መንግሥት ማሳቀልስ ዕውን የፖለቲካ ትርፍ የሚያስገኝ ነው? የዚህ ዓይነቱ ‹‹ትችት›› ኢትዮጵያ የተወጠረችበትን ድርብርና አባዛኝ ፈተና አላውቅም፣ ‹ለአፍ ዳገት የለውም› ሊባል የሚችል ነቀፋ ከመወርወር የበለጠም ኃላፊነት የለብኝ ብሎ በይፋ ከማወጅስ ይተናነሳል!? የውስጥና የውጭ እጆች የተቀናበሩበት የአንድ ቤኒሻንጉል ጣጣ እንኳ እንዲህ ያለ ነቀፋ ለመሰንዘር ያስደፍራል? ሕወሓት/ኢሕአዴግ ዙሪያውን በቅዋሜ ይዋከብ በነበረበት 2010 ዓ.ም. ጊዜ በሕጋዊው ጎዳና የለውጥ ቡድን ብቅ ባይልና ሕወሓት/ኢሕአዴግ በቅዋሜዎች ላይ እየተኮሰ የብተና ደባውን ቁልፍ ከፍቶት ቢሆን ኖሮ ዛሬ የት ነበርን? የለውጡ መንግሥት በመከላከያና በሌሎቹ የፌዴራል የፀጥታ አውታሮች ላይ የማዘመን/የቡድን ወገናዊነትን በዘዴ የማጠብ ሥራ ውስጥ ባይገባና ኢሕአዴግ አቀፍ ቡድኖችን ወደ ውህድ ፓርቲነት ባይወስድ ኖሮ፣ አገራችንና ሕዝቦቻችን የፅንፈኞችን ሸር በምንና እንደ ምን ተቋቁመውና ተያይዘው ይቆዩ ነበር? የኦነግ ፅንፈኛ ክንፍ የትጥቅ ቡድኖችን አሥርጎና አባዝቶ ብዙ ሊጎዳን የቻለው የሰላም በር ስለተከፈተ ሳይሆን፣ በጊዜው አገሪቱ የነበራት የደኅንነትና የመረጃ አውታር ሕወሓታዊ ጌትነት ሲሻ ሊያለግመውና ሻጥር መሥሪያ ሊያደርገው እስከመቻል ድረስ መዳፉ ውስጥ የገባ ስለነበር ነበር፡፡ ይህንን አስደንጋጭ ገመና ካስተዋልን፣ የለውጡ መንግሥትና ብልፅግና ፓርቲ እዚህ ደረጃ ድረስ ይዘውን መምጣታቸው በራሱ እንደ ተዓምር የሚቆጠር አይደለም? በግጭቶችና በትርምሶች ውስጥ እየተንጦለጦለና የጌታ ሕወሓቶችን ሸር አዋዝቶ እያረገበ፣ አገር ጉድ ሳትሆንና ውስጡን ለቄስነቷን ባዕድ ሳያይባት ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የአገርን የመረጃና የደኅንነት አውታር እንደ አዲስ ከመገንባት ባልተናነሰ ደረጃ ትልቅ ክፍተት መሙላት የተሳካለትስ የየትኛው አገር መንግሥት ነው? ያለንበትን ሁኔታ በዚህ መልክ የተረዳ ፖለቲከኛ መንግሥት፣ መከላከያና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ያለባቸውን ሽንቁሩ ተደፍኖ ያላለቀ ፈተናና ተጋድሎ የእኔም ፈተናና ተጋድሎ ነው የሚል የርብርብ መንፈስን ይጎናፀፋል እንጂ ‹‹ሥራህን ተወጣ!›› የሚል ኃፍረት የለሽ ምላስ አይዘረጋም፡፡

የርብርቡ ሦስት ፋይዳዎች

‹‹የውስጥና የውጭ የጥፋት ኃይሎች እንድንፋጅና እንድንበታተን እያሴሩብን ነው›› እያልን በነጋ በጠባ ብናወራ ዋጋ የለውም፡፡ በውስጣችን የሚከሰቱ ግጭቶችና ጥቃቶቻቸው በሚያደርሷቸው ጉዳቶች መንግሥትን ብንዘለዝልና ‹‹መንግሥት የዜጎችን የመኖር መብት ያስከብር›› እያልን ወግ ብንጠርቅ ዋጋ የለውም፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ አደጋ ውስጥ ነች፣ ማብቂያ የሌለው ፍጅት ውስጥ ልንገባና አገር የለሽ ልንሆን ነው! በጊዜ የዘመነ ዓድዋ አባቶቻችንና እናቶቻችን እንዳደረጉት አንድ ላይ ተምመን ራሳችንን (አገራችንን) እናትርፍ!›› እያልን በየመድረኩ ካወራን ይበቃን ይመስል፣ ከመድረክ ውጪ በጥርጣሬና በሐሜት እየተራረዱና እየተልጎመጎሙ የመኖር አባዜ ውስጥ  መልወስወስም ከንቱነት ነው፡፡ ‹‹እንደ ዓድዋ ተባብረን አገራችንን እናድን›› እያልን፣ በምርጫ ዘመቻና በክርክር መድረኮች ላይ ግን መንግሥትን የሚያሳቅሉ ቅራሪ ‹‹ድሎች››ን በማንጫለጥ ብንሳከር ድርጊታችን ራስን መቃረን ነው፡፡

የአሁኑ ወቅት በ1997 ዓ.ም. እንደታየው በመድረክ ሙግት ማራኪነት አገር ያካለለ ደጋፊና ወዶ ገብ ካድሬ የምናፍስበት ጊዜ አይደለም፡፡ የምርጫ 97 ቅስቀሳና ሙግት ጠርንፎ ይገዛ የነበረ ገዥን በመድረክ ከማሳጣትም በላይ፣ ተስፋ በሚጭሩ መፈክሮች ሕዝብን ከዳር ዳር ማሞቅ ችሎ ነበር፡፡ ዛሬ ያለንበት ሁኔታ በሞቁ የተስፋ ቃላት የፖለቲካ ሸመታ የሚካሄድበት አይደለም፡፡ ሰላሳ ዓመታት አዕምሮ ላይ የሠራው ብሔርተኛ ሙሽት ሥር ሥሩን እግር ይጎትታል፡፡ ከድርጅቶች የፖለቲካ ትርፍ በላይም አገርን የማትረፍና ለውጡን የማስቀጠል ተግባር በልጦ ያፈጠጠበት ወቅት ነው፡፡ በሌላ አባባል፣ ዛሬ ዋናው ጉዳይ በክርክርና በትችት በልጬ ብዙ አድናቆት እንደምን ልሸምት ብሎ ማሰብ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያንና ለውጡን በማዳን አንገብጋቢ ተልዕኮ የሚቻለኝን እንደምን ላዋጣ ብሎ ማሰብ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ነው በፓርቲዎች ክርክር ውስጥ የሰማነውን ‹‹ኦሮሚያ ውስጥ ገብቶ መሥራት ያልተቻለበት ጫካ! … ተውን አትነካኩን! እኛ አስፈታናችሁ እንጂ እናንተ አላስፈታችሁንም…›› የሚል ንግግር እውነታን በሙሉ ገጾቹ ያልተረዳና ግብዝነትን ከማርካት ያላለፈ ብለን የምንተቸው፡፡

ዛሬ ምርጫ የምናካሂደው በዴሞክራሲ ውስጥ እየተንፈላሰስን አይደለም፡፡ ዴሞክራሲ ውስጥ ለመግባት መንደርደሪያ በሚሆን የዴሞክራሲ ጠረን ባለው ሁኔታ ውስጥ ከፀረ ዴሞክራሲና ከኢዴሞክራሲያዊ ዝንባሌዎች ጋር እየተላፋን የምናካሂደው ምርጫ ነው፡፡ የብሔርተኛ ክፍፍል እስረኝነት ባልተራገፈበት ሁኔታ ውስጥ ሆነን የሚካሄድ ምርጫ ነው፡፡ በየአካባቢው የሚገባንን ያህል የምርጫ ዘመቻ ማካሄድ የተቸገርነውም፣ ከእዚህ የአመለካከትና የቁርቁስ እስረኝነት ስላልወጣን ነው፡፡ ምርጫውን ተዓማኒ ለማድረግ የምንለፋው እነዚህን ትብትቦችና ዝንባሌዎች በሚቻለን ሁሉ በልጠን ለማፍዘዝ ትግል እያካሄድን ነው፡፡ አሁን የምናካሂደውን ምርጫ ውድና የሚያሳሳ ያደረገውም፣ ወደ ልዩ ልዩ ድል ለመጓዝ መጨበጥ ያለብን እርፍ ስለሆነ ነው፡፡ ብዙ ዝባዝንኬ ባለበት በአሁኑ ሁኔታ ውስጥ፣ እንደ ልብ መዘዋወርና መንቀሳቀስ ቢሳሳብንም ሕዝብን የምንኮረኩርበት (ከሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ጋር የምንገናኝበት) ሐሳብ ካለን፣ ዕድሜ ለዛሬው ዘመን ቴክኖሎጂ ከርቀትም ወደ ሕዝብ ለመድረስ ምን ችግር አለ!

ገዳይን ወይም የገዳይን ዘመድ እየገደሉ ደምን በደም ‹‹የመመለስ›› ባህልን እየተንከባከበ ያቆየው በባለ ባህሉ ኅብረተሰብ ውስጥ ያለው፣ የሥጋ ዘመዱን ደም ‹‹ያልመለሰን›› ሰው በንቀት፣ በትዝብትና በሽርደዳ መድረሻ የሚያሳጣ፣ ደም ለመለሰም ክብርና ሞገስ የሚሰጥ ሥነ ልቦና ነው፡፡ በዚያው ዓይነት ግብዝ መኩራራትንና ባዶ አሸናፊነትን የሚኮተኩቱና የሚያፋፉ ሰበዞች በባህላችን ውስጥ ሞልተዋል፡፡ ንግግሮችንና ድርጊቶች በሚያስገኙት አወንታዊ ውጤት ሳንመዝን በጭፍኑ ‹‹እናት ጎበዝ ወለድኩ ትበል! ፍርኃት የማያውቅ ጀግና! ልክ ልኩን አስታጠቀው! ወዘተ›› እያልን እናሞካሻለን፡፡ አጥፍቶ ይቅርታ መጠየቅና ስህተትን መናገር የሞት ሞት የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡ አጠፋሁ ማለት መሸነፍ (ማነስ)፣ ራስን ማቅለል ነው፡፡ ጥፋትን መሸምጠጥ፣ አጥፍቶ ማጉረጥና መቆጣት አለማነስንና አለመንበርከክን መጠበቂያ የብረት ልብሶች ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉ ልብሶችን ለመጣል ሳንጣጣር ዴሞክራሲን ለመገንባት አንችልም፡፡ ከእነ ብረት ልብሳችን ሆነን የሚጥመንንና ‹‹ጎበዝ›› ያሰኘናል የምንለውን ግማሽ እውነት ብቻ እያመሰኳን፣ አንድ ልብ ሆኖ ለመትመም ብንሞክር ሙከራችን ከውሽልሽልነት አያመልጥም፡፡

ርብርባችን ፍሬያማ እንዲሆን ከፈለግን፣ ከይስሙላ ወሬና ከግብዝ ውዳሴ ወጥተን የዓድዋ የመንፈስ ጥንካሬን በተግባር መጎናፀፍ ያሻናል፡፡ የዓድዋ አባቶቻችንና እናቶቻችን አውርተውና አቅራርተው ወደ ቤታቸው አልሄዱም፡፡ በሥውርና በግልጽ አርበኝነት ዘምተዋል፣ በቁርጠኝነት ተዋድቀዋል፡፡ እኛስ በተግባር ሳንዘምት የዓድዋውን ዓይነት ድል ዛሬ እንዴት ልንደግም እንችላለን? ዘመቻችን በምን ይገለጻል? ጥርጣሬን፣ ጥላቻንና ከፋፋይ ሐሜትን አሟሙቶ ዝምታንና እህህታን ወደ ንቁ የአርበኝነት እንቅስቃሴ መቀየርና ሕዝቦችን አንድ ላይ ማገማሸር፣ በዚህም አማካይነት ነገር ሠሪዎችንና አጋጪዎችን ማምከን፣ (ወደ አገር ወዳድ ሚና መሳብ የሚችሉትን መሳብ፣ ዕምቢ ባይ የሴራና የሽብር ሠልፈኞችን የድጋፍ ጫካ አሳጥቶ ማመናመን) እነዚህን የመሳሰሉት ተግባራት ሁሉ የአርበኝነት ዘመቻ መልኮች ናቸው፡፡ እነዚህን ሁሉ አሳልተን፣ በአንድ አገራዊ ግብና ተግባር ላይ መሰማራታችንን ለጠላትም ለወዳጅም ማሳየት ስንችል ነው የዓድዋ መንፈስ ውስጥ ነን ለማለት የምንደፍረው፡፡

 መንግሥት፣ የአገር ቀንዶች፣ ምሁራን፣ ፓርቲዎች፣ የብዙኃን ማኅበራት፣ ሚዲያዎችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ የአርበኝነት እንቅስቃሴያችን በተበታተነ አኳኋን የሚሰምር ነው? ጥረታችንና አስተዋጽኦዋችን እየተመጋገበ እንዲያሻቅብ የሆነ ሰፊ የኅብረት መድረክና የዒላማዎች ንድፍ አያሻንም? በውጭ ያሉ የአገር ልጆችና የኤርትራ ልጆች ‹‹ዲፌንድ ኢትዮጵያ››፣ ወዘተ እያሉ በተያያዘ መልክ ሲረባረቡ፣ በውስጥ ያለነው በኢትዮጵያና በለውጧ መቀጠል ቀጥተኛ ተጠቃሚ የሆንነውና ኢትዮጵያ እሳት ብትያያዝ እሳቱ በተቀዳሚ የሚበላን ወገኖች በተቀናጀ መልክ መሥራት ይበዛብናል?

ይህ ተግባር ከምርጫ ዘመቻ ጋር የሚፋለስ መስሎን ይሆን? ለአገር በአንድ ላይ መቆምና የሕዝብን አብላጫ ፈቃድ ባገኘ መንግሥት እየተመሩ ፈርጀ ብዙ ተጋድሏችንን ወደፊት ማራመድ እንደምን ይጣላል? ክፉ የሚሠሩብንንና የሚያስቡብንን ኩም ማድረጊያ አንዱ መድረክ ምርጫው እንደ መሆኑ፣ ምርጫው ኅብረታችንን ጠንክሮ የሚወጣበት እንጂ የሚፈረካከስበት እንዳይሆን አድርጎ ማሳመር አንዱ ተግባራችን ነው፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ተቋማትና መራጮች ሁሉ ምርጫው እንዲታመን ከተጋገዝንና ውጤቱንም ያለማንገራገር ተቀብለን ከበፊቱ የበለጠ አብሮ ለአገርና ለሕዝብ መሥራት ከቻልን፣ ይህ ድል በራሱ ልካቸውን ላላወቁ ልካቸውን ይነግራል፡፡ ‹‹የምርጫ ሒደታችን መክሸፍና መሳካት በፈረንጅ ታዛቢ ምስክርነት ላይ የተንጠለጠለ አይደለም!›› የሚል ምላስ ያወጣል፡፡

ይህንን ድል መጨበጥ ከቻልን የውስጥ ሰላም አልባነትን የማድረቅ ድል በእጃችን ያለ ያህል ነው፡፡ የምርጫው ውጤት የተፈናከረ ቢሆን እንኳ የመንግሥት ቀውስ ሳይገጥመን፣ በጥምርነት (በኅብረት) አገርን ለመምራት የሚያበቃ የትግግዝ ልምምድ ይሰጠናል፡፡ ይህ ስንቅ ወደ ሌላ ስኬትም ይዞን ይሄዳል፡፡ በዕርቀ ሰላም ውይይት አማካይነት ብዙ የገረሩ ስሜቶችን ለማቃለል መነሻ ይሆነናል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በአካባቢ ደረጃ ሕዝብን ሳያንጓልል የሚጠቅም የልማትና የለውጥ መርሐ ግብር ያላቸው ፓርቲዎች፣ በጥላቻ ዘመቻና በስም ልጠፋ ሳይሰናከሉ ሕዝብ ውስጥ ገብቶ መሥራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ያገኛሉ፡፡ የጥንቅራቸው ኅብረ ብሔራዊ ስፋትና ጥልቀትም ሆነ፣ በሕዝብ የመወደዳቸው ጥልቀትና ስፋት በአያሌው ከራሳቸው በዓላማ የመርታት ስኬት ጋር የሚገናዘብ (ማሳበቢያ የለሽ) ይሆናል፡፡ እዚህ ሁኔታ ውስጥ ተገባ ማለት ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ዕጣ ከአንድ ፓርቲ በሥልጣን መቀጠል አለመቀጠል ጋር የሚያያዝበትን ታሪክ የሚያሰናብት (አገርን አስተባብረው መንግሥትን ሊመሩ የሚችሉ አማራጭ ፓርቲዎች የሚጎለብቱበት የአገረ መንግሥት መቀጠልና የመንግሥታት መቀያየር የማይምታቱበት) ሁኔታ ለማ ማለት ነው፡፡ እነዚህ ስኬቶች ለኢትዮጵያ ህልውና፣ ሰላምና ግስጋሴ እጅግ አስፈላጊ ናቸው፡፡

የታሪክ ጥሪ

እነዚህን ተግባሮች ማሳካት የታሪክ ጥሪን መወጣት ነው፡፡ ይህ ጥሪ የእኩልነትና የነፃነት ሕይወትን የምንሻ ኃይሎችን ሁሉ ይመለከታል፡፡ በአገር አፍራሾቹ ሕወሓት-ሸኔ ተፅፅኖ ሥር ገና ያሉ (ሌላ ፓርቲ ነን እያሉ) ‹‹አሸባሪ›› ተብለው የተፈረጁትን ፅንፈኞች ከማጀብ ያልተለየ የፖለቲካ ሥራ የሚሠሩትን ሁሉ ጥሪው ይጎተጉታል፡፡ የሕወሓትን አገር የማረድ ክህደት ለመቀልበስ የተካሄደውን ዘመቻ በትግራዊነት ላይ የተካሄደ ጭፍጨፋ እያሉ፣ ለመከላከያ ኃይል የተደረገውን የስንቅ ርብርብ ‹‹ትግራዊን ለማጥፋት የተደረገ ርብርብ›› እያስመሰሉ (ከዚህም የባሰ ቅጥፈት እያወሩ)፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲያስራቸውና ‹‹በትግራዊነት ላይ እየተዘመተ ነው›› ባዩ ቅጥፈት የበለጠ እንዲራገብ፣ ያጀቧቸውም ውስን ምዕራብ አገሮች ተፅዕኗቸውን በኢትዮጵያ ላይ እንዲያከፉ በሚለማመኑት ቡድኖች ተፅዕኖ ውስጥ ያላችሁ ወገኖቻችንም እንድትባንኑ ታሪክ እየጠራቻችሁ ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ ንቃ! ጠላትነትን የመረጡ የጎረቤቶቻችንን አጀንዳ  የተሸከሙ ‹‹ለትግራይ ቆመናል›› ባይ የግፍና የበቀል አበጋዞች፣ ገንዘብና መሣሪያ አሸክመው ወጣት ልጆችህን ከስደት እያሠረጉና ከጉያህ እየነጠሉ፣ ዳግመኛ በብሶትህና በነፃነት ስም የውጊያ ሜዳ ሊያደርጉህ እየሠሩ ያሉ ኃይሎችን ዕንቢኝ በል! ከጥንት እስከ ዛሬ አልላቀቅ ያለህን የጦርነት ማሳነት በቃኝ በል! ከቀሪ ኢትዮጵያዊ ወገኖችህ ጋር የልማት ማሳ ወደ የምትሆንበት ምዕራፍ ፊትህን መልስ!!

ከአካባቢ አካባቢ እንደ ጦስ ዶሮ መጠቃት ሳያንስህ፣ ጥቃቱ አማራ ‹‹ክልል›› ድረስ የመጣብህና ከተሞችንና መንደሮችን እስከ ማውደም ድረስ የከፋብህ አማርኛ ተናጋሪ ሕዝብ፣ መንግሥትን ብታማርርና ተስፋ ብታጣ አያንስህም፡፡ ተስፋ መቁረጥህ ምርጫው ለምኔ እስከ ማለት ድረስ ቢያሽቀነጥርህም አይገርምም፡፡ ነገር ግን በኩርፊያ ጥቃትህ ይሽራል? ያጣኸውን የህልውና መብት ትቀዳጃለህ? ታሪክና ኢትዮጵያ የምትጠራህ እዚህ ላይ ነው፡፡ በኩርፊያና በአመፅ መንገድ ህልውናህንም ኢትዮጵያንም አታገኛትም፡፡ የዚህ ዓይነቱ ዘራፍ ባይነት የሕወሓትንና የሸኔን የአገር ብተናና ሕዝብ የማፋጀት ጎዳና መቀላቀል ነው፡፡ ከመከራ መገላገያህ በድንግዝግዙ ውስጥ ያለውን የተሻለ ቀን ጮራ ማየትና ወደ እዚያ መጓዝ ነው፡፡ ወደ እዚያ መጓዝ ደግሞ በብሔር ፖለቲካ ውስጥ ከመሸጎጥ ርቆና ከቀሪ ወገኖች ጋር በኅብረ ብሔራዊነት ተያይዞ ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲና ወደ እኩልነት መውሰድ ነው፡፡

የሸኔንና የሕወሓትን በሽብርተኝነት መፈረጅ ልክ ብላችሁ በፀረ ፅንፈኝነት ትግል ንቁ ተሳታፊ መሆን ሲገባችሁ፣ ውሳኔውን ኦሮሞን ከማሸማቀቅ ጋር ያያያዛችሁ ውስን የኦሮሞ ብሔርተኞችም የኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ አካል እንድትሆኑ እየጠራቻችሁ ነው፡፡ የሸኔ ቡድን እንደ ሕወሓት አሸባሪ መባል የማያንሰው በፋሽስታዊ ጥላቻና በቀል የሰከረ መሆኑን ለመፍረድ፣ ሰሜን ሸዋ ውስጥ ያካሄዱት የዶግ አመድ ጥቃት ብቻውን በቂ ነው፡፡ ይህንን ሀቅ ከተቀበላችሁ፣ አዋጁ ማሸማቀቂያና ማጥቂያ እንዳይሆንበት የሠጋችሁለት ኦሮሞ የትኛው መሆኑ ነው? በፅንፈኛ ጥፋትና አሻጥር ውስጥ ለተሰማራው ጥቂት ወይስ በለውጥ ውስጥ ለተመመው? ለውጡን ከሚመሩት ውስጥ ግንባር ቀደም ሚናውን የሚጫወቱት የኦሮሞ ልጆች መሆናቸውና ኦሮሞ ገና በጅምር ደረጃ ባለው ለውጥ ከመቼውም የተሻለ የልማት ምዕራፍ ውስጥ መሆኑንስ ማየት ያዳግታል? ኦሮሞ ተገፋሁ ከሚያሰኝ እውነታና ከፅንፈኛ ብሔርተኛነት ተፅዕኖ ወጥቶ እዚህ ሁኔታ ውስጥ መግባቱ ለኦሮሞም ለኢትዮጵያም ድል ነው፡፡

የኦሮሞ ለውጠኞች ከሌሎች የኢትዮጵያ ለውጠኞች ጋር ሆነው ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ሕይወት ለማሸጋገር እያደረጉት ያሉት ተጋድሎ፣ ድርብርብና ከባድ መሆኑ ዕውቅ ነው፡፡ ለለውጥ በሚሠራው ፓርቲና መንግሥት ውስጥ የለውጥ አርበኛ መስለው ፅንፈኞችን የሚያገለግሉ መሰሪዎች ይኖራሉ፣ ከእነሱ ጋር ትግል አለብን፡፡ የውስጥ መሰሪዎች በግልጽ ከተሰማሩ የጥፋት ኃይሎች ጋር ተቀናጅተው የኦሮሞ ለውጠኞችንና ለለውጥ የሚሠራውን መንግሥት ድጋፍ የሚያሳጣ (በዓድሏዊነት የሚያሳማና አኩራፊ የሚያበዛ)፣ ከዚያም ሲብስ ለውጡን በአመፅ የሚያስመታና ወደ መፋጀት ሲዖል የሚያስገባ ሴራ ከመሥራት አይመለሱም፡፡ የሰሜን ሸዋው ጥቃት ይህን ሁሉ ዒላማ ያካተተ ምርጥ የሴራ ትርዒት ነበር፡፡ ኦሮሞ ፅንፈኞችና ሴረኞች አማራንና ቀሪውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፋፍለው በለውጡ ላይ እንዲሸፍት ለማድረግ እንደሚሠሩ ሁሉ፣ ኦሮሞ ያልሆኑ ፅንፈኞችና ከአፍንጫ አይርቄዎች፣ በኦሮሚያ ውስጥ የፅንፈኝነትን ተፅዕኖ እያንኮታከተ ያለውን የለውጥና የልማት እንቅስቃሴ በተረኝነት እየተረጎሙ ኦሮሞን ወደ ፅንፈኝነት የመገፍተር ሥራ ለሸኔዎች ይሠራሉ፡፡ ምንም ቢባልና ምንም ቢሠራ ግን፣ አገራችንን ተባብረን እስካቆየን ድረስ የኦሮሞ ልማት፣ የኢትዮጵያን እምብርት ማልማት እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ እምብርት ላይ እየታየ ያለውና ሐሜት የበዛበት ልማትም በሁሉም አቅጣጫ እየተሠራጨ ሐሜቱን ማትነኑ አይቀርም፣ ሒደቱም ተጀምሯል፡፡ የምጣዳችን አያያዝ፣ በመጪው አምስት ዓመት ውስጥ ተዓምር የሚያሰኝ ግስጋሴ እንደሚታይ በልበ ሙሉነት መናገር የሚያስችል ነው፡፡ እናም ዛሬ ወደ ኩርፊያ ያዘነበላችሁ አንዳንድ የኦሮሞ ብሔርተኛ ቡድኖች፣ ታሪክ ትናንትና ላይ ጥላችሁ ከመሄዷ በፊት ንቁ ተሳታፊ እንድትሆኑ እየጋበዘቻችሁ ነው፡፡

በመጨረሻ የምሰናበትበት ነጥብ ከጥሪም በላይ ተማፅኖ ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንዳልኩት ያለንበት ጊዜ ምላስ የባጠጠበት፣ ማጥወልወልና ቁርጠት የሚመላለስበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ አንዱን ሕመም አሳልፈን ተንፈስ አልን፣ ‹‹ከእንግዲህስ…›› ከማለታችን፣ በህልማችንም ይሆናል ያላልነው ሁሉ ብቅ ይላል፡፡ የለየላቸው በጥባጮች የሚበጠብጡን ሳያንስ፣ በአገር ወዳድ የሕዝቦች ሠልፋችን ውስጥ ቁንጥንጦች አይታጡምና ቀላል ጥያቄና ብሶት ለነገ ማሳደር ቸግሯቸው አጀንዳ ይሰጡናል፡፡ ምሽት ላይ ቀላልና የሚያፋቅር ነው ያልነው ጉዳይና ጥያቄ ለበነጋታው ነገረኛ ትርጉምና ጉምጉም ወልዶ እናገኘዋለን፡፡ ባላሰብነው ቁርጠት እንደገና መንቆራረጥ! ሽል የሌለበት የምጥ ኑሮ! የዕፎይታ ዕድሜ ከስንዝር አላልፍ ያለበት የሥጋት ኑሮ!

የረመዳን የፆም ፍቺንም ሆነ ሌላ የሙስሊም በዓልን በአብዮት/በመስቀል አደባባይ የማክበር መብትን ይህች ሰበበኛ ጊዜ ካለፈች በኋላ ማሟላት አንችልም ነበር? ጥያቄው ከመጣ ወዲያስ ከኦርቶዶክስ ክርስቲያን ወገኖች በኩል አንዳንዶች እንዳጦዙት ከቤተ ክርስቲያኗ መከራ ጋር ምን ከምን ሆኖ ይገናኛል? ትንፋሻቸው አውሬ የሚያለምድ የሃይማኖት መሪዎች ባሉበት አገር፣ ስለክርስቲያኖችና ስለሙስሊሞች የትግግዝ ልምድና ታሪክ የወጣቶቻችን ግንዛቤ እንደምን ሳሳ? አፍንጫችን ሥር ያለውን የራጉኤል ቤተ ክርስቲያንንና የአንዋር መስጊዲን የትቅቅፍ ኑሮ የሚያስተውል ልብ እንደምን ታጣ? የራጉኤል ቤተ ክርስቲያንን ካለበት ለማንሳት ሲሞከር፣ ክርስቲያንና ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ተጋግዘው ያከሸፉበት የቅርብ ታሪክስ እንደምን ይታዘበን?

ስንት ዘመን ጥምቀት የሚከበርበት ጃንሜዳ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ንብረት አይደለም፡፡ የጃንሜዳን መጠሪያ ወደ ‹ጥምቀት ሜዳ› ብንቀይረውም የስም ለውጥ ሜዳውን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ንብረት አያደርገውም፡፡ ከዚህ አኳያ የድጋፍ ደሃ የነበረው ኢሕአዴግና ኦርቶዶክሳዊ ብልጣ ብልጦች ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ መስቀል አደባባይ ያሰኙት አብዮት አደባባይ፣ የአገልግሎት ገዳቢና ከልካይ ሊኖርበት የማይገባ የሕዝብ ሀብት መሆኑ በስም መንፏቀቅ ምክንያት ስንዝር ታህል አይቀነስም፡፡ አንዴ ስሙ ከተለወጠ በኋላ ጩኸት ያልበዛው የመስቀል ክብረ በዓል የኦርቶዶክሳዊያን ብቻ ሳይሆን፣ የመላ ኢትዮጵያ ሀብት ስለሆነ ነው፡፡ ለኢሬቻ በዓል ቦታ ሲመደብም እሰይ ያልነው ኢሬቻ ክብረ በዓል የማይንጓለል የኢትዮጵያ ሀብት ስለሆነ ነው፡፡ ለኢሬቻ በተመደበው ቦታ ሌላ ነገር አይሠራ፣ የዱሮ ማክበሪያዬ ስለሆነ ባለመብቱ እኔ ብቻ ነኝ የሚል ስስት ከመጣም መታገላችን አይቀርም፡፡

ይህ መሠረታዊ ግንዛቤ እንደ ተጠበቀ ሆኖ ጮርቃዎቻችን መለስ ብላችሁ የኋላ ታሪክ እንደትጠይቁና እንድታጠኑ የሚያመላክቱ ነጥቦች ላክልላችሁ፡፡ እኔ ወጣት ታዳሚ በነበርኩበት በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ የመስቀል ክብረ በዓል የሽብርቅና የቅርፃ ቅርፅ ሥራ መሰናዶውን፣ በቤተ መንግሥት ጋራዥ ውስጥ በተሽከርካሪዎች ላይ አጠናቆና በመብራቶች ተንቆጥቁጦ በዕለተ በዓሉ፣ ዛሬ እንደምናየው በእስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያንና በቱሪስት ድርጅት ትይዩ በነበረው መንገድ እየሰፈፈ ይከበር ነበር፡፡ በአፄው ጊዜ ‹‹መስቀል አደባባይ››ም ሆነ ‹‹አብዮት አደባባይ›› የሚባል የሕዝብ አደባባይ አልነበረም፡፡ የራሱን ‹‹በዓል›› ለማክበርና ለማስከበር ሲል የሕዝብ አደባባይን አስቦ የሠራው ደርግ ነበር፡፡ ዛሬ በአደባባይነት ተዘርግቶ የምናየው ቅንፋማ ሥፍራም ኦናውን የነበረ አልነበረም፡፡ ድድ ማስጫ ከነበረ ውስን ኮረብታማና ጎርባጣ መስክ በስተቀር ብዙው ሥፍራ በቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤትና በራስ ብሩ ቤት (የዛሬ አዲስ አበባ ሙዚየም) ግቢ ውስጥ የተካተተ ነበር፡፡ የራስ ብሩ ስምም ለአካባቢው መጠሪያነት ተርፎ ነበር፡፡ ደርግ አደባባዩን ከሠራው ወዲህም የዚያ አደባባይ ታሪክ ከመስቀል ክብረ በዓል የትና የት ያለፈ ነው፡፡ ያ ሥፍራ የእስጢፋኖስን ደጃፍ ሁሉ አካቶ፣ ‹‹ኮሙዩኒስት›› ነን ባይ መንግሥታዊ መፈክርና ድንፋታ ብዙ ተስተጋብቶበታል፡፡ ብዙ የወታደርና የሲቪል ሠልፍ ረገጣ፣ ብዙ የተቃውሞ ሠልፍና የብሶት ጥያቄዎች ብዙ ጥይትና ደም አስተናግዷል፡፡ ሥፍራው ይህን ሁሉ ታሪካችንን የያዘ ዓምድ ነው፡፡ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ሸርፎ ሲሸጠው የቆጠቆጠንም ለዚህ ነበር፡፡ አሁንም መስቀል አደባባይ ለሁሉም የሕዝብ አገልግሎት እስከ ዋለ ድረስ ‹‹መስቀል›› ከሚል ስም የማንጣላ ቢሆንም፣ ነባር ስሙ እንዳልነበር ተደርጎ እንዲደመሰስ እንፈቅዳለን ማለት አይደለም፡፡ የማንፈቅደው አንዳንድ ህሊና ቢሶች እንደሚሉት ‹‹አብዮት›› የኢዓማኒነት መታወሻ ስለሆነ ሳይሆን፣ የዚያ ዘመን መስዋዕትነት ‹‹በኢዓማኒነት ላይ የወረደ ቅጣት›› ተደርጎ መጣጣልም መረሳትም የማይገባው፣ ዛሬ ለደረስንበት የድል ምዕራፍ ሁነኛ የአገዳ ክፍል ስለሆነ ነው፡፡

ወደ ተማፅኖ ጉዳያችን ልመለስ፡፡ ለፅንፈኛ ነገር አራጋቢዎች የሚመቹ ጥያቄዎች በዛሬው አጉል ጊዜ ማንሳት፣ የቋፍ ሰላማችንንና ብዙ ሥውርና ግልጽ ሥራ ያለበትን መንግሥትንም ፈተና ውስጥ መክተት መሆኑን አጢኖ ትዕግሥት ማድረግ ፈፅሞ ሰባኪ ሊኖረው የማይገባ ኃላፊነት ነው፡፡ ምርጫውን እንዳይሆን አድርጎ፣ ሕዝብንና መንግሥትን የትርምስ አዙሪት ውስጥ ለመክተት በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች አሸባሪ ፍንዳታዎችንና የተኩስ እሩምታዎችን ለማካሄድ የጥፋት ኃይሎች እያደቡ ባሉበት ወቅት፣ መስቀል አደባባይ ላይ የፆም ፍችን ከማካሄድ ጥያቄ ጋር የተያያዘ ግርግር ተፋፍሞ ቢሆን ኖሮ ለአሸባሪዎች መሹለክለኪያ ሽፋን ሆኖ ለከፋ ጥቃት ሊያጋልጠን ይችል አልነበረም? የአዲስ አበባ አስተዳደር ፈቀድኩ/አገድኩ ማለቱ እኮ ከድክመት ይበልጥ የጭንቅ ኑሯችንን የሚያንፀባርቅ ነው! ተራ ዜጎች ደጅ ደጁን ከምናውቀው በላይ መንግሥታዊ አስተዳደሮችን የሚወጥሩና የሚያመናትሉ በይፋ ሊነገሩ የማይችሉ ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ የጦር መሣሪያ እንቅስቃሴዎችን፣ የአሸባሪ ደባ ሰንሰለቶችንና የገንዘብ ምንጮችን መከታተል፣ ቀዳዳ እንዳያገኙ መላ መሥራት፣ ወዘተ ሁሉ ባለበት ሁኔታ ውስጥ የእኛ የማያስቸኩል (ግን የጉምጉም መዘዝ ሊሆን የሚችል) ጥያቄ ሲታከል መንግሥታዊ ክፍል የሚይዝ የሚጨብጠው ቢቸግረው ምን ሊደንቅ! ለጥያቄው ‹አይሆንም› የሚል መልስ ብንሰጥ ሙስሊሙ አማኒ ምን ይሰማው ይሆን? ነገር ሠሪዎች ያምሱት ይሆን? ቢፈቀድስ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ለመሰነጣጠቅ ውስጥ ለውስጥ የሚሄድ ተንኮል ባለበት ጊዜ፣ ኦርቶዶክስ ምዕመናን እንዴት ይቀበሉት ይሆን? ምዕመናኑን ነገረኞች ያምሱብን ይሆን? ከዚህ ዓይነት ጥያቄዎች ጋር ያለው ፈተና ቀላል ጭንቅ ነው!?

በየትም አገር ለውጥ መጥቶ ዘመን መቀየር ሲጀምር በሁሉም የሕይወት ዘርፎች ውስጥ ብዙ ነገሮች ቋቋታ… ጓጓታ… ንፍፊት… ይገጥማቸዋል፡፡ ስለለውጥና ተጋቦቱ ስለለውጥና የእምቢታ ቃሩ የነገሮችን ቅርፊት፣ አስኳልና ውል እየበለቱ ብዙ ማተት ቢቻልም፣ ከውጭና ከውስጥ ያሉብን ጣጣዎች የሳቢያና የውጤት መስተጋብራቸው ከአንዱ ወደ ሌላው እየተላለፈ የሚመጋገብ በመሆኑ በጣም ጥንቃቄ ይሻሉ፡፡ ከዚሁ አኳያ የሁሉን ነገር ውስጠ ሚስጥር ላትት ማለትም ሆነ ሁሉን መሰሪነት አንዴ ላጥቃ ማለት ጅልነት እንደሚሆን ሁሉ፣ መብት ቀረን ብሶት አለን የምትሉ ወጣቶቻችንም ይህ የብርቱ ፈተና ቀን እስኪያልፍ ታገሱ፡፡ ክፉውን ቀን ከተወጣነው በኋላ ብዙ ነገሮች እንደሚቃኑና መብቶች እንደሚበዙ አስተውላችሁ፣ አሁን በሚብስብን የአገር ጉዳይ ላይ አተኩሩ፡፡ በአንገብጋቢ ተግባራት ላይ የተጠመደ የመንግሥትን ትኩረት በማያስቸኩሉ ጉዳዮች አትሻሙ፡፡ ለመፍረድ፣ አቋም ለመያዝና በስሜታዊነት ውስጥ ለመግባት ከመጣደፍ ይልቅ የወሬዎችን እቅጭነት፣ የሐሳቦችንና የፍላጎቶችን ጥቅምና ጉዳት አገላብጦ ለመረዳት እንድትጣጣሩም ‹‹እባካችሁ! እባካችሁ!›› እንላለን፡፡ ይህ ተማፅኖ የእኔና የባልንጀሮቼ ብቻ ሳይሆን፣ አገሬንና ሰላሜን የሚሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይመስለኛል፡፡ ድል ለኢትዮጵያ! ድል ለዴሞክራሲና ለሰላም!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

በበቀለ ሹሜ reporter amharic


Exit mobile version