Site icon ETHIO12.COM

ከሃገር ለመውጣት የሞከሩ 60 ወጣቶች መያዛቸውን ፖሊስ አስታወቀ

ከአማራ ክልል ከተለያዩ ዞኖች በደላሎች ተታለው በህገ ወጥ መንገድ ከሃገር ለመውጣት የሞከሩ 60 ወጣቶች መያዛቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የባቲ ከተማ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር መሃመድ አሊ ለኢዜአ እንደገለጹት  ወጣቶቹ ጨለማን ተገን አድርገው ከሃገር ለመውጣት ሲሞክሩ ትላንት ከለሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በባቲ ከተማ ተይዘዋል ።

ወጣቶቹ በህገ ወጥ መንገድ ወደ አረብ ሀገር ለመውጣት የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3- 43619 አአ በሆነ የጭነት አይሱዙ ተሽከርካሪ ተሳፍረው ከደጋን መስመር ወደ አፋር በመጓዝ ላይ እንዳሉ በከተማው ቀበሌ 03 ቀርሳ ፍተሻ ጣቢያ  ላይ መያዛቸውን ተናግረዋል ።

ወጣቶቹ ከ17 እስከ 28 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ መሆናቸውን ጠቁመው ከወጣቶቹ መካከል ሶስቱ ሴቶች እንደሆኑ ገልጸዋል።

እንደ ዋና ኢኒስፔክተሩ ገለጻ ወጣቶቹ ከሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሽዋና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች በህገ ወጥ ደላሎች ተታለው የተሰባሰቡ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ወጣቶቹን በህገወጥ መንገድ ከሀገር ለማሶጣት በታሰበ ወንጀል ተሳትፎ እንዳላቸው  የተጠረጠሩ አሽከርካሪውን ጨምሮ ሁለት ግለሰቦች ተሸከርካሪውን አቁመው መሰወራቸውን ተናግረዋል ።

ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትል መጀመሩን አመልክተዋል ።

ወጣቶቹን በሂደት ወደ አካባቢያቸው ለመመለስ ከወዲሁ ስራዎች መጀመራቸውንም ጠቁመዋል።

ዜጎች ጫካ ለጫካ ጭምር በእግራቸው በመጓዝ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ ሀገራት ለመውጣት በሚያደርጉት ሙከራ ለሞት፣ ለአካል ጉዳትና ለመደፈር እየተጋለጡ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ድርጊቱ በተደራጀ አግባብ የሚፈፀም በመሆኑ ለመከላከል አስቸጋሪ እንዳደረገው ያመለከቱት ዋና ኢኒስፔክተሩ የባለድርሻ አካላት ጠንካራ ትብብር  በመፍጠር ድርጊቱን ለመከላከል ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ። via (ኢዜአ)


Exit mobile version