ነዳጅ በህገ ወጥ መንገድ ለማጓጓዝ የሞከሩ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ ገለፀ

የንግድ ህጉን በመተላለፍ ነዳጅ በህገ ወጥ መንገድ ለማጓጓዝ የሞከሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ ገለፀ

የንግድ ህጉን በመተላለፍ ነዳጅ በህገ ወጥ መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ አሶሳ ከተማ ለማጓጓዝ የሞከሩ ግለሰቦች በህብረተሰቡ ጥቆማ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለፀ።

የካቲት 27 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ገርጂ ማርያም አካባቢ ከሚገኝ ኖክ ፈጣን ነዳጅ ማደያ በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 A 10734 አ/አ በሆነ ኤፍ ኤስ አር ተሽከርካሪ 39 በርሜል ነዳጅ በመቅዳት ጭነው ከአዲስ አበባ ወደ አሶሳ ከተማ ሲያጓጉዙ የተገኙ ሁለት ግለሰቦችና ሁለት የማደያው ሰራተኞች ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ ተይዘዋል፡፡

ከህብረተሰቡ የደረሰን ጥቆማ መሰረት በማድረግ በተወሰደ እርምጃ 50 በርሜል ተዘጋጅቶ ሰላሳ ዘጠኝ በርሜል ናፍጣ ተቀድቶ የተያዘ ሲሆን ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው አራት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና የተያዘው ነዳጅ 7,800 (ሰባት ሺህ ስምንት መቶ ) ሊትር መሆኑን ተረግጧል፡፡

ግለሰቦቹ መመሪያ ቁጥር 12/2011 አንቀፅ 14 ንዑስ አንቀፅ 16 ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ምንም አይነት ህጋዊ ሰነድ ሳይኖራቸው ነዳጁን ለማጓጓዝ ሲሞክሩ ተይዘዋል።

ህገወጦቹ በህብረተሰቡ ጥቆማ መያዛቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልፆ መሰል ድርጊቶች ሲያጋጥሙ ጥቆማ የመስጠት ልምዱን አጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡ ከሀገር ጥቅም ይልቅ የግል ጥቅማቸውን በማስቀደም የሚንቀሳቀሱ አካላት እና በህጋዊ የንግድ ፍቃድ ሽፋን ህገወጥ ተግባር የሚፈፅሙ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት ከህገወጥ ተግባራቸው ሊታቀቡ እንዲሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል።

(ኢ ፕ ድ)

Leave a Reply