Site icon ETHIO12.COM

ድራማው – ዶላር አዝናቢዎች ተያዙ

ይህ ታሪክ ያስታወሰኝ “ዶላር እናዘንባለን” ሲሉ የነበሩ መታሰራቸውን ስሰማ ነው። ሮጠው ካከማቹት መካከል ለነዚሁ መንታፊዎች አስረክቦ ብቻውን ሲያወራ የነበር ሰው ታወሰኝ። እሱ ብቻ አይደለም አንድ የሩጫ ታዋቂ አሰልጣኝ እዚሁ ዶላር አውራጅ ቤት እንዴት እንዳጠቧቸው አስምለው ነግረውኝ ነበር።

እኙሁ አባት አሰልጣኝ በሚቀርቧቸው ሰዎች ተጀንጀነው፣ ዶላር እንዲዘንብላቸው ሜርኩሪ ግዙ እየተባሉ ነበር የተሸለሙትን ያራገፉት።

አንድ ካሜሩናዊና ኢትዮጵያዊ ዶላር እናባዛለን በሚል መያዛቸውን ፖሊስ ይፋ ቢያደርግም ገና በምርመራ ላይ በመሆናቸው እንዴትና በምን ዘዴ እንደሚያጭበረብሩ አላስታወቀም።

የዚህ ዓምድ አዘጋጅ ቀደም ሲል ከተዘረፉ እንደሰማው ከሆነ ዶላር እንዲወርድላቸው የሚፈልጉ “ሜርኩሪ ግዙ” ይባላሉ። ይህን ለግለሰብ የተከለከለ ውድ ንጥረነገር የሚሸጠው ሰው ደግሞ የዚሁ የሌብነት ኔትዎርክ አባል ነው። ነገሩን እውነት ለማስመሰል በሰው ሰው ነው የሚገኙት።

አቅራቢዎቹ አረቦች ወይም ሌላ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው እንዲሆኑ የሚደረገው እምነት ለመጨመር ነው። በዚህ ሂደት ዶላር እንዲዘንብላቸው የሚቋምጡ ይህ ኔት ዎርክ የመለመላቸው ሃብታሞች ” እኔ ይህን ያህል አገኘሁ” በማለት ልክ እኚህን አሰልጣኝ እንዳደረጉት ይቀሰቅሳሉ።

ምንም ያልጎደለባቸው ሰዎች ያላቸውን እንዳይበሉ ንብረት ጭምር እያስያዙ ዶላር እንዲዘንብላቸው ምንነቱን የማያውቁትን ሜርኩሪ መሳይ ነገር እየሸመቱ እንደ ቃሊቻ ዶላር አወርዳለሁ እሚለው ሰው ዘንዳ ይሄዳሉ። “ሜርኩሪ ነው” ተብል የተሰጣቸውን ቅመም አቅርበው የሚሆነውን ይጠብቃሉ። አውራጁ ሜርኩሪ የሚባለውን ይሁን ሌላ የማይታወቅ ነገር እያጨሰ ትንሽ ዶላር ያሳይና / የተቀረው ፎርጂድ ነው/ የሚጨሰው ሜርኩሪ እንዳለቀ በመናገር ሌላ እንዲያቀርቡ ያዛል።

ድራማው የሚሰራበት ክፍል፣ የሚሰራበት የቅንብር ደረጃውና፣ ከመንፈሳዊ ዛር ጋር የሚመሳሰልበት ጥበብ የሚያማልል በመሆኑ ባለጉዳይ ሜርኩሪ የተባለውን ባዕድ ነገር ለመግዛት ይሮጣል ወይም ትሮጣለች። በዚህ ስልት ሃብታቸውን ጨርሰው ያጨበጨቡ በርካታ ናቸው። ደላሎቹ ሃብታሞች አውቀው እነሱም አብረው እንደከሰሩ ሆነው ሃዘን ይቀመጣሉ። ፖሊስ ምርመራውን በደንብ ከያዘው ብዙ ጉድ ይወጣዋል። ኢዜአ የዘገበው እንደሚከተለው ነው።

በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ዶላር እናባዛለን በማለት የማጭበርበር ተግባር ሲፈጽሙ የነበሩ ግለሰቦች በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ኢንተለጀንስ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለፀ።

በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው ‘ሲኤምሲ’ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ዶላር እናባዛለን በማለት የአካባቢውን ህብረተሰብ ሲያጭበረብሩ የነበሩ ካሜሮናዊና ኢትዮጵያዊት በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ኢንተለጀንስ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል፡፡

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ሰዓት ዶላር እናባዛለን በማለት ለማጭበርበሪያ የሚጠቀሙባቸው ሁለት ካርቶን ዶላር የሚመስል ወረቀትና ሁለት ጠርሙስ ኬሚካል ይዘው መገኘታቸው ታውቋል፡፡ ከማህበረሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ኢንተለጀንስ ሁለቱንም ግለሰቦች በቁጥጥር ስር በማዋል በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራ እየተጣራ ይገኛል፡፡

እንደነዚህ አይነት ህገ-ወጥ ተግባር በሚፈጽሙ ግለሰቦች ዙሪያ ጥቆማ በመስጠት ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ድጋፍና ትብብር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ፖሊስ ጥሪ ማቅረቡን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በማህበራዊ ገፁ ይፋ አድርጓል፡፡


Exit mobile version