Site icon ETHIO12.COM

“አማራ ሚዲያ በውጭ ሀገራት የራሱ ማሰራጫ ጣቢያዎች እንዲኖሩት እየተሠራ ነው” –

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን አሁን ካለው ቴሌቪዥን ስርጭት በተጨማሪ “አማራ ሕብር” ኹለተኛ የቴሌቪዥን ጣቢያ በቅርቡ የሙከራ ሥርጭት እንደሚጀምር የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥየ አስታወቁ፡፡
///*

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይህን ያሉት የደብረ ማርቆስ ኤፍ ኤም 95.1 ሥርጭትን ዛሬ ሲያስጀምሩ ነው፡፡

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ደብረ ማርቆስ ኤፍ ኤም 95.1 አካባቢያዊ ሥርጭት ዛሬ ጀምሯል፡፡ በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ሙሉቀን ሰጥዬ ራዲዮ ጣቢያው ደብረ ማርቆስ እና አካባቢው በተለይ ደግሞ ብዙ አማራጭ ለሌለው የገጠሩ ማኅበረሰብ መረጃ ተደራሽ ለማድረግ ዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንዳሉት አሚኮ የአማራ ክልልን ብሎም የክልሉ አዋሳኝ አካባቢዎችን የሚዲያ ተደራሽ ለመድረግ የሚያስችለውን ማሰራጫ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ስናን ወረዳ ጮቄ ተራራ ላይ ተክሏል፤ ደብረ ማርቆስ ኤፍ ኤም 95.1 ምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ ምእራብ ጎጃም ዞን፣ አዊ ብሔረሰብ አስተዳደርን፣ የደቡብ ወሎ ዞን ምዕራባዊ ወረዳዎችን፣ የተወሰኑ የሰሜን ሸዋ ዞን አዋሳኝ ወረዳዎችን እንዲሁም ከአማራ ክልል ውጭ የተወሰኑ የኦሮሚያ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ ወረዳዎችን ተደራሽ ማድረግ ይቻላል፡፡

ይህም የአካባቢውን ኅብረተሰብ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር እና ሁለንተናዊ የማደግ ጥያቄዎችን ማቅረብ ከማስቻሉም በላይ የሕዝብ ለሕዝብ መስተጋብር እንዲዳብር ከፍተኛ ጉልበት ሆኖ ማገልገል የሚችል የሬዲዮ ጣቢያ ነው ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት አሚኮን ለማሳደግ በሰጠው ትኩረት በተለይም የሕዝቡን የመረጃ አማራጮች ለማስፋት በተለይ የቴሌቪዥን እና ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች ተደራሽ ያልሆኑ የገጠር አካባቢዎችን ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል፡፡

በሰቆጣ ከተማ አዲስ የኤፍ ኤም ራዲዮ ጣቢያ ለማስጀመር የግንባታ ሥራ መጀሩንም አቶ ሙሉቀን አስታውቀዋል፡፡ አቶ ሙሉቀን የአማራ ሕዝብ ወግ፣ ባሕል፣ ታሪክ፣ እሴት እና እውነተኛ አስተምህሮ ለመላው ኢትዮጵያውያን ለማሳወቅ በቴሌቪዥን እና በአዲሱ የሚዲያ አማራጮች ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ የራዲዮ አገልግሎት ዘርፉን ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል፡፡

የራዲዮ ዘርፉም እውነተኛውን የሕዝብ ባሕል፣ ትክክለኛውን ታሪክ አና እሴት ማስተዋወቅ እንዲችል በአዲስ አበባ ከተማ አማራ ኤፍ ኤም አዲስ አበባ 103.5 የሙከራ ስርጭት ማስጀመሩን አንስተዋል፡፡

የአሚኮ ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች አቅም እያደገ መምጣቱን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው አብዛኛው ማሰራጫ ተከላው በኮርፖሬሽኑ ባለሙያዎች መከናወኑን ተናግረዋል፡፡ አሚኮ ተደራሽነቱን ለማስፋት በጥናት ተመስርቶ እና እቅድ ነድፎ እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ አቶ ሙሉቀን ሚዲያውን በመደገፍ እና አብሮ በመሥራት ረገድ ሁሉም እንዲሳተፍም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው በሀገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች የዘገባ ወኪሎች እንዲኖሩት በሥራ አመራር ቦርዱ ጸድቆ የሰው ኃይል ለማሟላት እየተሠራ ነው፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ መስተጋበሩን ብሎም ሀገራዊ አንድነቱን ለማጠናከር አሚኮ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ሙሉቀን ተቋማቸው በተመረጡ የውጭ ሀገራትም ዘገባዎችን በመሥራት ይበልጥ አድማሱን ለማስፋት እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ ቀስ በቀስም በውጭ ሀገራት የራሱ ማሰራጫ ጣቢያዎች እንዲኖሩት እየተሠራ ነው፡፡

ይህ እቅድ እውን እንዲሆን በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ሀገር ወዳዶች ዘርፈ ብዙ እገዛና ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አሁን አገልግሎት እየሰጠ ካለው ቴሌቪዥን ስርጭት በተጨማሪ “አማራ ሕብር” ኹለተኛ የቴሌቪዥን ጣቢያ በቅርቡ የሙከራ ሥርጭት እንደሚጀምርም አቶ ሙሉቀን አብስረዋል፡፡ አሚኮ የሁሉም መሆኑን በመረዳት ሁሉም አብረውት እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አሚኮ


Exit mobile version