Site icon ETHIO12.COM

‹‹ የውጭ ጫና ዋና ዓላማ ከድህነት እንዳንወጣ ለማድረግ ነው›› –ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ

blinken


የአሜሪካ መንግሥት ያደረገው ማዕቀብና የጎረቤት አገራት ጫና የማሳረፍ ሙከራ ዋና ዓላማው ኢትዮጵያ ከድህነት እንዳትወጣ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ አስታወቁ።

ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ በተለይ አዲስ ዘመን እንዳስታወቁት ፤ ጎረቤት አገራትም ሆኑ አሜሪካ የኢትዮጵያን መልማትና ራሷን በራሷ ማስተዳደር መቻል ብዙ ነገሮቻቸውን እንደሚያሳጣቸው አድርገው ያስባሉ።

በተለይም ኢትዮጵያ ከድህነት ከወጣች ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም አይበገሬነቷን ስለምታረጋግጥ ይህም የእነሱን ጥቅም ይጎዳዋል በሚል በአገሪቱ ላይ ጫና ለማሳረፍ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ያመለከቱት ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ፣ አጀንዳቸው ኢትዮጵያ ከድህነት እንዳትወጣ፣ ጠንካራ መንግሥትና የሕዝብ አንድነት እንዳይኖር ለማድረግ ነው ብለዋል። አሁን እየታየ ያለውም ጫና ይህንን ኢላማ አድርጎ እንደሆነ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ድሮም ሆነ አሁን ኩሩ ሕዝብ ያላት፤ እግዚአብሔርን የምታምንና በእምነቷ የምትሻገር አገር ነች የሚሉት ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ፤ ማንም ግርድናን ፈልጎ ከአገሩ አይሰደድም። በአገራችን ምቹ ሁኔታዎች ከተፈጠሩ ኢትዮጵያ ሳትሆን አሜሪካ ቪዛ ጠያቂ የምትሆንበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን አስታውቀዋል።

በውጭም ሆነ አገር ውስጥ ያለው ዜጋ ስለአገሩ አንድነት መሥራት አለበት ያሉት ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ፣ ጥላቻን ትቶ ልማት ላይ በማተኮርም ለጫናው መልስ መስጠት አለበት ብለዋል።

‹‹ክፉ ጎረቤት እቃ ያስገዛል›› እንደሚባለው የአገራችን ብሂል የአሜሪካ ማዕቀብም ጠንክሮ ለመሥራትና አንድነትን ለመመለስ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል። ዛሬ አንድ የምንሆንበት አጀንዳ ተሰጥቶናል። ቀን ከሌሊት እየሠራን የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል ያስፈልጋል። ቅናታቸውን በሥራ እንጂ በንግግር መመለስ አይቻልምና የፈሩት እውነት እንዲሆን ማድረግ ላይ ሁሉም መረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

(ኢ ፕ ድ )

Exit mobile version