Site icon ETHIO12.COM

የተጠርጣሪዎችን መብት በጠበቀ መልኩ ምርመራ ለማካሄድ የሚያስችል የሪፎርም ስራ ተከናውኗል … ወንጀል ምርመራ ቢሮ

Demelash police

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የተጠርጣሪዎችን ሰብአዊ መብት በጠበቀ መልኩ የምርመራ ስራ ለማከናወን የሚያስችል የሪፎርም ስራ ማከናወኑን ገለጸ።

ቢሮው ያከናወናቸውን አጠቃላይ የሪፎርም ስራዎች አስመልክቶ ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ማብራሪያ ሰጥቷል።

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ሃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ በዚህ ወቅት እንዳሉት ከለውጡ በኋላ በተጠርጣሪዎች አያያዝ ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም የተለያዩ ማሻሻያዎች ተደርገዋል።

ከተቋም አደረጃጃት ጀምሮ በቴክኖሎጂ የተደገፉ የምርመራ ስራዎችን በመዘርጋት በተጠርጣሪዎች ላይ ቀደም ሲል ይፈጸሙ የነበሩ በደሎችና የመብት ጥሰቶችን ማስቀረት ተችሏል ብለዋል።

የፖሊስን ስነ ምግባር ባልተከተለ መንገድ በተጠርጣሪዎች ላይ ይፈጸም የነበረው ያልተገባ አሰራርና ሀሰተኛ መረጃ በማደራጀት ተጠያቂ የማድረግ ህገ ወጥ ተግባርም እንዳይኖር ተደርጓል ብለዋል።

በግለሰቦችና በፖለቲካ ሹመኞች ጫና የፖሊስ የምርመራ መርህን ያልተከተለ ተግባር በተጠርጣሪዎች ላይ ይፈጸም እንደነበርም አስታውሰዋል።

በተለይ ‘’ማዕከላዊ‘’ በሚባለው ማቆያ በዜጎች ላይ ይፈፀም የነበረው አስከፊ ኢሰብአዊ ተግባር የተቋሙንና የአገሪቱን ገጽታ አበላሽቷል ብለዋል።

ለውጡን ተከትሎ መንግስት በህዝብ ላይ በደረሰው ጉዳት በይፋ ይቅርታ በመጠየቅ በወሰደው ቁርጠኛ ውሳኔ በአገራችን ብሎም በወንጀል ምርመራ ቢሮ ከፍተኛና ታሪካዊ የሚባል በአጭር ጊዜ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አያያዝ የማሻሻያ ስራ ተከናውነዋል።

በመሆኑም ባለፉት ሶስት ዓመታት የተቋሙን ገጽታ ለመቀየርና ማዕከላዊን ወደ ሙዝምነት ከመቀየር ባለፈ አዲስ ተቋማዊ አደረጃጀትና አሰራሮች መዘርጋታቸውን ሃላፊው ገልጸዋል።

በፖለቲካ ወገንተኝና በጥቅም ትስስር ወንጀል እንዳይፈጸም አዲስ “የኢትዮጵያ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ መመሪያ” ተግባራዊ በማድረግ ወጥ የሆነ አሰራር እንዲኖር ተደርጓል።

አዲሱ መመሪያ ሳይንሳዊ የምርመራ ስልቶችን የሚከተል ሲሆን በተጠርጣሪዎች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይኖር ያስችላል ብለዋል ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም።

አዲሱ መመሪያ ከተጠርጣሪዎች መረጃን ለማግኘት ሃይል መጠቀምና ጨለማ ቤት ማስር እንዲሁም ሌሎች ኢሰብአዊ ተግባራትን በጥብቅ የሚከለክል መሆኑን ተናግረዋል።

ለምርመራ ከተዘጋጀ ቦታ ውጪ ተጠርጣሪዎችን መመርመርም ፍፁም የተከለከለ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተቋሙ የተሳካ የሪፎርም ተግባራት ለማከናወን ሃላፊዎችና ሰራተኞች ከፍተኛ ርብርብ ያደረጉ ሲሆን የተለያዩ የመንግስት ተቋማትም ከፍተኛ ድጋፍ አድርገዋል ብለዋል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በበኩላቸው ቢሮውን በቴክኖሎጂ፣ በሰው ሃይልና በተቋም አደረጃጃት የተሻለ በማድረግ የተጠርጣሪዎች መብት እንዲሻሻል ተደርጓል ብለዋል።

በምርመራ ወቅት ምንም ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይኖርም አዲስ አሰራር ተዘርግቷል ብለዋል ኮሚሽነር ጀነራሉ።

በቀጣይም አሰራሩን ለማዘመንና በሳይንሳዊ አሰራር ይበልጥ እየተጠናከረ እንዲሄድ ለማስቻል የፎረንሲክ ምርመራ ላይ ልዩ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።

በፕሮግራሙ ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ማአዛ አሸናፊ፤የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ፣ የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብረሃም በላይን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል። via – (ኢዜአ)

Exit mobile version