ፌደራል ፖሊስ ሆን ብለው ሐሰተኛ መረጃ በሚያሰራጩ አካላት ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል አለ

ሆን ብለው ሕብረተሰቡን ለማሳሳት ሐሰተኛ መረጃ በሚያሰራጩ ግለሰቦች ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።

ተቋሙ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት ለህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል የሰብአዊ መብት ጥሰት ይፈፀምበት የነበረውን ማዕከላዊ የወንጀል ምርመራን መዝጋት መሆኑንና ይሄንን ተከትሎ በፖሊስ የወንጀል ምርመራ ስራ ላይ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ስር ነቀል ማሻሻያ ማድረጉን አመልክቷል፡፡

ከሪፎርሙ በኋላ ተቋሙ የወንጀል ምርመራ አሰራር መቀየሩንና በቴክኖሎጂ የታገዘ ግልፅ አሰራር በመዘርጋት ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የወንጀል ምርመራ ስታንዳርድን እየተከተለ እንደሚገኝ ጠቅሷል።

በዚህም ውጤታማ የወንጀል ምርመራ ስራ በማከናወን የተጠርጣሪዎችን የሰብአዊ መብት አያያዝ በከፍተኛ ሁኔታ ለማሻሻል መቻሉን ገልጿል።

በዚህ ተግባሩ ከአገር ውስጥና ከውጭ ሀገር የሰብአዊ መብት ጥበቃ ተቋማት የምስጋና እና የእውቅና የምስክር ወረቀት ማግኘቱን አውስቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን አንዳንድ ግለሰቦች በማህበራዊ ሚዲያ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በተጠርጣሪዎች ላይ “ኢ-ሰብአዊ አያያዝ ፈጽሟል” እያሉ ሆን ብለው የተቋሙን መልካም ስም ለማጠልሸት ሐሰተኛ መረጃዎችን እያሰራጩ እንደሚገኙ ጠቁሟል።

ይህንን መሰረተ ቢስ ውንጀላ እየፈፀሙ ያሉት በአሸባሪነት ተጠርጥረው እንደሚፈለጉ ስም ዝርዝራቸው ለህዝብ በይፋ ከተገለጹት መካከል መሆናቸው እንደተደረሰበት ነው ተቋሙ ያስታወቀው።

ሐሰተኛ መረጃውን የሚያሰራጩት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ላይ እያካሄደ ያለውን የምርመራ ሂደት ለማደናቀፍ እንደሆነ ገልጿል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በአሸባሪዎች ላይ የጀመረውን የምርመራ ሂደት አጠናክሮ እንደሚቀጥል እና ሕብረተሰቡ በዚህ ሐሰተኛ ወሬ ሳይደናገር ትክክለኛው መረጃ በቦታው ተገኝቶ ከፖሊስ እና ከተጠርጣሪዎች አንደበት ማረጋገጥ እንደሚችል አመልክቷል።

See also  ማንነታቸው በማይታወቀ ሰዎች ስም ካሳ በሚል መንግስት ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ ተዘረፈ

Leave a Reply