ETHIO12.COM

24 ሠዓታት በውትድርና ህይወትክፍል 7 – “ውስብስብ ፈተና ያላንበረከከን…” (የዝንጀሮ ጦርነት)

May be an image of 21 people, people standing and military uniform

ከግንባር ተመልሰናል። ወደ ትንታግ መኮንኖች ማፍሪያ አጭር ኮርስ ማሰልጠኛ ሁርሶ ተጉዘን የሰባተኛ ዙር ትዝታን በወፍ በረር እንቃኛለን።በዚህ ዙር የውጊያ ጠቢባንና የመድረክ ፈርጦች ይበዙ ነበር።

በሁሉም ዙሮች የሚገቡት በእሳት የተፈተኑ ሃምሣ አለቆች መሆናቸው ግድ ሆኖ ይኼኛው የተቋሙ ጋዜጠኞች፣ ገጣሚያንና የመድረክ ሰዎች መብዛታቸው ልዩ አድርጎታል።ወጋችንንም መሠል ገጠመኞችና የጥበብ ጉዳዮች ላይ ያተኮረበት አንዱ ምክንያት ይሄው ነው።ብቸኛ ምክንያት ግን አይደለም።

ከሠልጠኞች ውስጥ አንድ ጓድ ይሄንን አጋጣሚ ተጠቅሞ የሠራዊቱን ሀገራዊ ፍቅር ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሳድግ ፣ ጥበብን በሠራዊቱ ውስጥ ወደ ፊት የሚያራምድ እቅድ ነደፈ።እቅዱን ለጥበቡ ቅርብ ለሆኑ አባላት አወያየና በሙሉ ድምፅ ተቀባይነት አገኘ።ቀጣዩ እቅድ አውጥቶ ማሰልጠኛውን ማስፈቀድ ነበር።

የአጭር ኮርስ አዛዡ ሐሳቡን ወደዱት።ዝርዝር ሥራውን ሲሰሙ ግን ተናደዱ። የታሰበው ሥራ በአብዲሣ አጋ ጀግንነት ዙሪያ የሚያጠነጥን ትያትር አዘጋጅቶ ለግቢው ሠልጠኝ ፣ ነዋሪዎችና የአካባቢው ማህበረሰብ ምቹ በሆነው አንፊ ትያትር ማቅረብ ነበር።በወቅቱ የነበሩት አዛዥ ከ1983 ዓ.ም የነበሩ የሀገራችን ጀግኖች ታሪክ አይመቻቸውም ።

እናም “ምንድነው ትላንትን መናፈቅ? የአፍሪካን ግዙፍ ሠራዊት የገበሬ ጦር መርተው ድል ያደረጉ ሐየሎም የመሣሠሉት ጀግኖች እያሉ የምን የተሸነፈ ሠራዊት ላይ መንጠልጠል ነው።በዚያ ላይ የማሰልጠኛው ስያሜ ሐየሎም አርአያ ወታደራዊ አካዳሚ ነው” አሏቸው።

የኮርሱ አባል የነበረው ተራኪያችን ፈጠን ብሎ “ታሪኩ ላይ እኮ ሐየሎም አለበት” አለ ።ሌሎች አባላት ደንግጠው እርስ በርስ ተያይተው ወደ እሱ ሲዞሩ ጠቀሳቸው።አዛዡ ተገርመው “እንዴት? ማን ነው ያላችሁት አብዲሣ እና ሐየሎም ምን ያገናቸዋል።እየቀለዳችሁብኝ ነው እንዴ? ብዙ ሥራ አለብኝ በሉ ሂዱ ።ቁምነገር የያዛችሁ መስሎኝ” ብለው ሊያሰናብቷቸው ሲሉ ይሄው አባል ፈጠን ብሎ”የሚያገናኛው ታሪክ በደንብ አለ።

እኛም ታሪኩን ስናነብ ማመን አቅቶን ነበር።ግን ተገናኙ”አለ። አባላት አዛዡ ልብ አላሉዋቸውም እንጂ መደነቃቸው ፊታቸው ላይ በደንብ ያስታውቅ ነበር።”እንደዚያ ዓይነት ታሪክ አለ እንዴ? እስቲ ንገሩኝ እንዴትና መቼ ተገናኙ ?”ሲሉ ጠየቁ። “ከፈለጉ ሐየሎምና ክራሩ የሚል መፅሐፍ ላይ ታሪኩን በደንብ ያገኙታል።

አብዲሣ አዋጊም አሰልጣኝ ነበር።ታዲያ ያሰለጠነውና በርካታ ጦርነቶች ላይ የመራው በደንብ የሚያውቀው አጋጣሚ ሆኖ በሰሜኑ ውጊያ የተማረከ አንድ መኮንን በትግሉ ወቅት ተማርኮ ተሃድሶ ወስዶ በዓላማው አምኖ ታጋዮችን ያሰለጥን ነበር “በወቅቱ በዙሩ አባል የነበረች የመከላከያ ተዋቂ ጋዜጠኛ ሳቋ አመለጣት።አዛዡ ግን በጣም ተመስጦ ስለነበር ገልመጥ ብሎ ፊታቸውን ወደ ተራኪው መለሱ።ተራኪው በአዛዡ መመሰጥ ተበረታታ። ኮስተር ብሎ ቀጠለ። አሰልጣኙን በጉብዝናው ይወደው ስለነበር ሐየሎም ያቀርበዋል።

አንዴ ጊዜ ስለ አብዲሣ የሀገር ፍቅር፣ የአመራር ጥበብና ከዑጋዴን በረሃ እስከ አውሮፓ የጣሊያን ዱርና በረሃዎች የዘለቀ ጀግንነቱ አወጋው።ሐየሎምም መኮንኑን ብቻ ሳይሆን አብዲሣንም ወደደው። ክራር ሲጫዋት ሁሌም ትዝ ይለኛል ቆራጡ መረሳ ፣ እንደ ያኛው ጀግና ልክ እንደ አብዲሣ ፡ የሚል ግጥም ጣል ያደርግ ነበር” ብሎ ታሪኩን ደመደመ። መረሳ ሐየሎም በጣም ይወደው የነበረ በትግሉ የተሰዋ ጓድ ነው።ይሄን መቼም ያውቁታል ብዬ እገምታለሁ አለ። “አውቀዋለሁ።በጣም ይገርማል።

በሉ በደንብ አርጋችሁ ሥሩት’ ብለው ፈቀዱ።ከወጡ ቦኃላ አባላቱ እስኪበቃቸው ስቀው “ምንድነው ያወራኸው ብለው ጠየቁት።መልሱ ትያትሩን መሥራት ትፈልጋላችሁ አትፈልጉም? መልሳችሁ እንፈልጋለን ከሆነ ደራሲው አሁኑኑ ተውኔትህ እኚህን በተለያዩ ወቅት ፣ ለተለያየ ዓላማ ሠራዊት የመሩ ኢትዮጵያውያንን የሚያገናኝ እንዲሆን አድርገው “ሆነ ።አማራጭ አልነበረም።

አብዲሣና ሐየሎም በአንድ ታሪካዊ ወቅት የዕጩ መኮንኖች ድርሰት ተገናኙ።በማሰልጠኛው ከስልጠና ጎን ለጎን አከባቢን በፈጠራ ሥራ ማስዋብ እና ከሌላው በልጦ ለመገኘት መጣር ግድ ነበር። ፈጣራው ደግሞ አንዳንድ ነገሮች ለማሟላት ወጪ ይጠይቅ ነበር።ወጪው የሚሸፈነው በሠልጣኙ መዋጮ ነው ፡፡አባላቱ ውስጥ ደግሞ ቤተሰብ የመሠረተ ደመወዙን ወክሎ የገባ አለ።

ከእንደዚህ ዓይነት ጓዶች ውስጥ አንዱ ለፈጠራ ሥራ አላዋጣም አለ።ለምን ተብሎ ምሽት በግምገማ ሲጠየቅ የሰጠው መልስ መቼም የሚረሳ አይደለም።”የእናንተ ፈጠራ አያልቅምና እኔ የፈጠርኳቸው ልጆቼን በረሃብ ልጨርስ?” የሚል ነበር።ተራኪው ከማይረሳቸው የዙሩ ትውስታዎቹ የሴት ሠልጠኞች ጥንካሬ አንዱ ነው። ስልጠና እጅግ ከባድ በመሆኑ ድካሞች ነበሩ።

በጉዞ ላይ የደከመውን አባል ንብረት የራስ ሸክም ላይ ደርቦ መያዝ የሠራዊቱ ባህልም ግዴታም ነው።ሴቶች ደክመው ሲታገዙ ቢያንስ መኮንኑ ያላየ ሲሆን የደከመ ጓዳቸውን ሲያግዙ ግን ደጋግሞ በዓይኑ በብረቱ አይቷል።ወታደር ከምንም በላይ ለጀግና አክብሮት አለው።ሴቶች ሲሆኑ ደግሞ ስሜቱ ከፍ ይላል።

በወቅቱ በቁጥር አነስተኛ የነበሩ ትንታግ እንስቶችም የከበዳቸው ስልጠናው ሳይሆን አፍቃሪን በትህትና ከፍቅር ስሜት ወደ ጓዳዊነትና ወንድምነት መመለስ ነበር።ሌላው አስደናቂ ገጠመኝ የዝንጀሮ ጦርነት በመባል የሚታወቀው ውስብስብ ፈተና ካላንበረከከው ሰባተኛ ዙር ትዝታ የማይጠፋው አስገራሚ ክስተት ነው።በአካቢው ዝንጀሮዎች በብዛት ይኖራሉ።የተረፈ የሠልጠኝ ደቦ ፍለጋም ከማሰልጠኛው ዙሪያ አይጠፉም።

ታዲያ አንድ ቀን አንዱ የአንዷን ዝንጀሮ ልጅ ወስዶ ለማላመድ ሠፈር ያስራል። ለቀናት ዝንጀሮቹ የታሰረችበትን ማወቅ አልቻሉም። በኋላ በስለላ ደረሱበት።የት እንዳለች እንዳወቁ ለሁለት ቀናት ከአከባቢው ተሠወሩ።ሠልጠኙም በቃ ተስፋ ቆረጡ ሲል ደመደመ። ጉዳዩ ግን እንደ ግምቱ አልነበረም።የጠፉት ለማዘናጋት ሲሆን ቀጣይ የምናነበበውን ምርጥ እቅድ ለማቀድ ነበረ።በሦስተኛው ቀን የስልጠና ሠዓት ጠብቀው ወደ ማሰልጠኛው መጡ። ዝንጀሮዋ ከምትገኝበት ከሚርቅ በአንዱ የግብር አደራሽ ላይም ወረራ ፈፀሙ። ወጥ መድፋት ዕቃ መሰባበር ተያያዙ።

ሠራተኞቹ ከአቅማቸው በላይ ስለሆነ ጩኸታቸውን ለቀቁ።ረቂቁ የውጊያ ስልት ተግባራዊ የሆነው በዚህ ወቅት ነበር።በተለያዩ ምክንያት ሠፈር የቀሩ የሠራዊት አባላት ወረራውን ለመከላከል ወደ ጩኸቱ ሥፍራ ሄዱ ።ይሄኔ የተለየ ተልዕኮ የተሰጣቸው ዝንጀሮዎች በሌላ አቅጣጫ ገብተው በቀላሉ ልጃቸውን ፈትተው ወሰዱ።ይሄን ታሪክ ውስብስብ ፈተና ያላንበረከከው የሰባተኛ ዙር አጭር ኮርስ ዕጩ መኮንን ሁሉ ያስታውሰዋል።

ሰልፍ ፣ ደፈጣ ፣ በደረት መሳብ ፣ ትብብር ፣ ጠንካራ የሥራ ባህል ፣ ደፈጣ እና የመሣሰሉ ወታደራዊ ስልቶች ከእንስሳት እንደተገኙ የተማርነው እውነት ላቅ ባለ የዝንጀሮች ጥበብ በተግባር ተገለጠ። የሠለጠነ ሰው ብቻ ሳይሆን ወታደርም ለአንድ ቀንም ቢሆን በዱር እንሰሳ ተበለጠ።ዙሩ መጠሪያውን ያገኘው “ውስብስብ ፈተና ያላንበረከከን” ከሚለው ዝነኛ መዝሙሩ ነው። በትክክልም ያንን ኮርስ ገላጭ ነበር።ለምን ለሚል ጥያቄው ተራኪው በቂ ምላሽ አላቸው።የኮርሱ አባላት የምክትል አሥር አለቃ ማዕረግ ያገኙት በውጊያ እንደ ወርቅ ተፈትነው ነው።

ሙሉ አሥር አለቃን ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ ተይቶ በማይታወቅ በቃላት ለመግለፅ በሚከብድ ስልጠና ብርሸለቆ ላይ ከደም ያለነሰ ላቡን አፍስሶ ፣ እንደ ጦርነት የህይወት መስዋዕትነት ጭምር ከፍሎ ነው።ሃምሳ አለቃ ለመሆን በየክፍሉ በልዩ ሁኔታ ሰልጥኗል።በስልጠና ቆይታው ፊልም የሠራ ፣በበርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ኤች አይ ቪን ጨምሮ ትያትር አዘጋጅቶ ለሠላም ማስከበር ፣ ለምልምል ወታደሮች ፣ በወቅቱ በአከባቢው ለነበሩ የፌዴራል ፖሊስ ሠልጣኞች ፣ ለግቢው ሁሉም ማህበረሰብ በአንፊ ትያትር ያስኮመከመ ዙር ነው።መሠል ተግባር የፈፀመ ሌላ ዙር ካለ ይሞግተኝ ብለዋል የዚህ ታሪክ ተራኪያችን።

እውነት ነው። ያ ዙር ተፈትኗል ግን አልተንበረከከም።አሁንም በሁሉም የሠራዊታችን ክፍሎች በታክቲካል አመራር ሀገሩን እያገለገለ የሚገኝ ፣ በጥበቡ ዘርፍ መፅሐፍት ፣ መድብሎች ያሳተመ ፣ በፊልም ፣ በትያትርና የሬዲዮ ድራማዎች ወዘተ ላይ አሻራውን ያሳረፈና በማሳረፍ ላይ የሚገኝ ነው፣ በትምህታቸውም ከዲኘሎማ የመጀመሪያ ዲግሪ ሁለተኛ ዲግሪ አልፈው ዶክትሬታቸውን የያዙ በርካታ ናቸው።ግቢው ላይ በሳረፈው ታሪክ የማይዘነጋው አረንጓዴ አሻራውን ጨምሮ እልፍ መገለጫዎቹን መነካካት ላይገልፀው ጊዜ ማበከን ነው።

ከመገለጫዎቹ ይቺን ታህል በትውስታ ዳሰስን። ተራኪያችን በአንድ ነገር እርግጠኛ ነው። ለውስብስብ ትላንት ያልተንበረከከ ፣ ነገም የማይንበረከክ ታሪክ የሠራና በመሥራት ላይ የሚገኝ እውነተኛ የኢትዮጵያ መከላከያ ማሳያ ናሙና ነው ።

ሻለቃ ፈይሳ ናኔቻ – FDRE Defense Force – የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት 


Exit mobile version