Site icon ETHIO12.COM

“ኢትዮጵያን ማስቆም የሚችለው ፈጣሪ ብቻ ነው”

Tibor Nagy ( former assistant secretary State Dept. )

ኢትዮጵያን 2ኛውን ዙር የህዳሴ ግድብ ውሃ ከመሙላት ሊያስቆማት የሚችለው ፈጣሪ ብቻ ነው ሲሉ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስርያ ቤት የቀድሞው የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ቲቦር ናጊ ተናገሩ።
አሜሪካዊው ዲፕሎማት ይህንን የተናገሩት “Al-Masry Al-Youm” ከተባለ የግብጽ ተነባቢ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ ነው።

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ጋር በተገናኘ የቀድሞው እና የአሁኑ የአሜሪካ አስተዳደር አቋም እንዴት ይገለፃል በሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ቲቦር ናጊ በሰጡት ምላሽ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በግልጽ ለካይሮ የመወገን ባህሪ እንደነበረው አንስተው የአሁኑ አስተዳደርም መጀመርያ ላይ ከያዘው የተለሳለሰ አቋም አሁን ለጉዳዩ ከፍተኛ ቦታ መስጠት ስለመጀመሩ ተናግረዋል።
በተለይም የእስራኤል እና ሀማስ ግጭት እንዲቆም ግብጽ የተጫወተችው የአሸማጋይነት ሚና ፕሬዝደንት ባይደን ለህዳሴው ግድብ ትኩረት እንዲሰጡ እንዳደረጋቸው ቲቦር ናጊ ገልጸዋል።

“በሚቀጥሉት 12 ወራቶች 3ቱ ሀገራት ከስምምነት ላይ እንደሚደርሱ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል” ያሉት የቀድሞው ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ነገር ግን ይሄ ሊሆን የሚችለው ኢትዮጵያ በቀጣዩ ክረምት 2ኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ካከናወነች ብቻ ነው ብለዋል።

“ምንም መደባበቅ አያስፈልግም በመጪው ክረምት የህዳሴው ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት ይከናወናል። ምክንያቱም መጪው ክረምት በኢትዮጵያ ከፍተኛ የዝናብ ወቅት ስለሆነ ዝናብ መዝነቡን እስካላቆመ ድረስ ግድቡ ውሃ መያዙን አይተውም” ብለዋል። በመሆኑም ኢትዮጵያን በመጪው ክረምት ውሃ ከመሙላት ሊያስቆማት የሚችለው ፈጣሪ ብቻ ነው፤ ፈጣሪ ከሰማይ ዝናብ እንዳይዘንብ ካደረገ ብቻ ነው ኢትዮጵያን ማስቆም የሚቻለው በማለት ገልጸዋል።

“ግብጽ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት ጋር የፈፀመቻቸው ወታደራዊ ስምምነቶች፤ እንዲሁም ከሱዳን ጋር ያከናወነቻቸው ተደጋጋሚ ወታደራዊ ልምምዶች ኢትዮጵያን አያሰጋትም ወይ፤ በቀጠናውስ ጦርነት ሊቀሰቀስ አይችልም ወይ” በሚል ከጋዜጠኛው ጥያቄ የቀረበላቸው ቲቦር ናጊ ”የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) በሩስያ ድንበር አቅራቢያ የጦር ልምምድ ስላደረገ ሩሲያን ይወራል ማለት አይደለም። ይሄ የተለመደ ተቀናቃኝን በሥነልቦና የማስጨነቅ ተግባር ነው“ ሲሉ መልስ ሰተዋል።

ግብጽ የህዳሴውን ግድብ ድርድር ለመፍታት ጦርነትን ጨምሮ ሁሉም አማራጮች በጠረጴዛ ላይ እንዳሉ ልታስብ ትችላለች ነገር ግን እውነታው ጦርነት ለግብጽ ምርጫ ሊሆን አይችልም። ድርድር ብቻ ግብጽን ወጤታማ ያረጋል ሲሉ መግለጻቸውን ጂ ኤም ኤን ከአል ማስሪ አል ዮም ድህረ-ገጽ ያገኘው መረጃ ያመላክታል።

በዶናልድ ትራምፕ ዘመን የአፍሪካ ጉዳዮች ሀላፊ ሆነው ያገለገሉት ዲፕሎማቱ ቲቦር ናጊ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነውም ሰርተዋል።

ምንጭ፦GMN

Exit mobile version