“ቀስ በቀስ በሚወሰዱ እርምጃዎች” ሲል የአረብ ሊግ ኢትዮጵያ ላይ አሴረ፤ ኢትዮጵያ ከ”የአፍሪካ ሽምግላና በቀር” ብላለች

“ቀስ በቀስ በሚወሰዱ እርምጃዎች” ግብጽና ሱዳንን ለመርዳት መምከራቸውን ከማንሳታቸው ውጪ እርምጃዎቹ ምን እንደሆኑ ያፋ አላደረጉም። ኢየሩሳሌም ፖስት የግብጽን ወታደራዊ ቁስ በመዘርዘር ጦርነት ቢጀመርስ አይነት ሟርት እያሰማ ባለበት ወቅት የአርብ ሊግ ይህን ማለቱ ኢትዮያን አቋሟን የሚያስቀይር አልሆነም። ይልቁኑም ” ሚዛናችሁን ጥብቁ” የሚል መልስ ነው የተሰጠው።

የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አገራቸው ካስተናገደችው የአርብ ሊግ አገሮች ስብሰባ በሁዋላ ” የአረብ አገር አህገራት በውንድማዊ ስሜት በህዳሴው ግድብ ላይ ድጋፍ እንሰጣለን” ሲሉ ለሚድል ኢስት ሞኒተር ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የናይል ተፋሰስ አገራት ሰብስባ ስትመክር፣ ጉዳዩ የማይመለከታቸው የአረብ ሊግ አገራት ኢትዮጵያ አስገዳጅ ውል ሳትፈርም ወደ ውሃ ሙሌት እንዳትገባ አሳስበዋል። ” ቀስ በቀስ የሚወሰዱ እርማጃዎች” ሲሉ ማስፈራሪያ አስከትለዋል።

የኢትዮጵያ ወዳጅ የነበረችው ኳታር በቅጽበት ታጥፋ እንዲህ ያለ መግለጫ በሚኒስትሯ መስጠቷ አስገራሚ ሆኗል። ቢቢሲ አማርኛ የሁለቱንም ወገን አካቶ ያሰፈረውን ሚዛናዊ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ ውይይት እንዲያደረግ በአረብ ሊግ በኩል የቀረበውን ሐሳብ እንዳማትቀበለው ኢትዮጵያ አሳወቀች።

ኳታር ዶሃ ላይ ተሰብስበው የነበሩት የአረብ ሊግ አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አወዛጋቢውን የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ጉዳይን በተመለከተ ተወያይተው የመንግሥታቱ ድርጅት ጸጥታ ምክር ቤት እንዲመለከተው ጥሪ አቅርበዋል።

ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አገሪቱ የአረብ ሊግ የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ባሳለፈው “የውሳኔ ሐሳብ” በእጅጉ ማዘኗን ገልጿል።

መግለጫው ጨምሮም የአረብ ሊግ ግድቡን በተመለከተ የተሳሳተ አቋም ሲያንጸባርቅ የመጀመሪያ ጊዜው አለመሆኑን ገልጾ ትናንት ማክሰኞ ያወጣውን የውሳኔ ሐሳብ “ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ እንደማትቀበለው” አሳውቋል።

በሱዳንና በግብጽ ጥያቄ በግድቡ ጉዳይ ላይ የተሰበሰበው የአረብ አገራቱ ማኅበር፤ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ እንዲወያይበት ሃሳብ ማቅረቡን የሊጉ ዋና ጸሐፊ አህመድ አቡል ጋሂት ናቸው ከስብሰባው በኋላ የተናገሩት።

የሚኒስትሮቹ ስብሰባ በተጨማሪም በውዝግቡ ውስጥ ግብጽንና ሱዳንን ለማገዝ “ቀስ በቀስ በሚወሰዱ እርምጃዎች” ላይ ከስምምነት መደረሱን የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሐመድ ቢን አብዱልራህማን አልታኒ ለጋዜጠኞች የገለጹ ሲሆን ዝረዝር ከመናገር ተቆጥበዋል።

የአረብ ሊግ ባወጣው መግለጫ ላይ ኢትዮጵያ በግብጽና በሱዳን ላይ ጉዳት ከሚያደርስ የተናጠል እርምጃ ካለው የሁለተኛው ዙር የግድቡ ውሃ ሙሌት ተቆጥባ “በቅን ልቦና” ድርድር እንድታደርግ ጠይቋል።

ሊጉ የአባይ ውሃ የግብጽና የሱዳን የህልውና መሠረት እንደሆነ በመጥቀስ አገራቱን የሚጎዳ ተግባር እንዳይፈጸም የጠየቀ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም የአባይ ውሃን በመጠቀም ሚሊዮኖችን ከድህነት ለማውጣት ለምትጥረው ኢትዮጵያም ውሃው የህልውና ጉዳይ ነው ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

ሊጉ ሱዳንና ግብጽ ግድቡን በሚመለከት የሚያቀርቡትን “መሰረት ቢስ” መረጃን በመተራስ በወሰደው የተሳሳተ አቋም ሳቢያ ሊጫወት የሚችለውን አውንታዊ ሚና አበላሽቷል ሲል የአረብ ሊግን ገለልተኝነትን ጥያቄ ውስጥ ከቶታል።

የሊጉን የውሳኔ ሃሳብንም የሕዳሴ ግድብን ጉዳይ “ዓለም አቀፋዊና ፖለቲካዊ ለማድረግ የታሰበ የማይሳካ ሙከራ” ነው በማለት ይህም የአባይ ወንዝን ዘላቂ በሆነ አካባቢያዊ ትብብር ለመጠቀምና ለማስተዳደር ምንም አይነት አስተዋጽኦ አይኖረውም ብሏል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጨምሮም ሱዳንና ግብጽ ድርድሩን የአረብ አገራት ጉዳይ ለማድረግ መሞከራቸው እንዳሳዘነው አመልክቶ “ይህም በአፍሪካ ሕብረት ለሚመራው የሦስትዮች ሂደት ታማኝ” እንዳልሆኑ ያመለክታል ብሏል።

ግብጽና ሱዳን ቀደም ሲል ከአፍሪካ ሕብረት በተጨማሪ በድርድሩ ላይ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአደራዳሪነት እንዲሳተፉ ቢጠይቁም ኢትዮጵያ ጉዳዩ በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት ብቻ መፍትሔ ማግኘት አለበት በማለት ሳትቀበለው ቀርታለች።

ግድቡን በሚመለከት በአፍሪካ ሕብረት አሸማጋይነት በተከታታይ ሲካሄድ የነበረው ድርድር በመጨረሻ ኮንጎ ኪንሻሳ ውስጥ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም አንዱ ወገን ሌላኛውን ለድርድሩ አለመሳካት ተጠያቂ በማድረግ ያለውጤት ተበትኗል።

ይህንንም ተከትሎ ሁለተኛው ዙር የግድቡ የውሃ ሙሌት ከመጀመሩ በፊት ሱዳንና ግብጽ በተለያዩ ወገኖች በኩል በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ጥረት እያደረጉ ሲሆን የአረብ ሊግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባና ያወጣው መግለጫ የዚሁ ጥረት ውጤት ነው።

ግብጽና ሱዳን ለረጅም ጊዜ ሁሉን አቀፍ ሕጋዊና አስገዳጅ ስምምነት በሦስቱ አገራት በኩል እንዲፈጸም ይህ ካልሆ ግን ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌቱን ማከናወን እንደሌለባት ሰወተውቱ ቢቆዩም ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት የመጀመሪያ ዙሩን የውሃ ሙሌት አከናውና በመጪው ሐምሌ ወር ደግሞ ሁለተኛውን ዙር ለመሙላት እየተዘጋጀት ነው።

ሱዳን ቀደም ሲል ይዛው ከነበረ አቋም በተቃራኒ የአረብ ሊግ ስብሰባ ከመካሄዱ አንድ ቀን ቀደም ብላ ሰኞ ዕለት በመስኖ ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ያሲር አባስ በኩል ቅድመ ሁኔታዎችን አቅርባ ከኢትዮጵያ ጋር ጊዜያዊ ስምምነት ለመፈረም ፍላጎት እንዳላት አሳውቃለች።

በዚህም መሠረት በቅድመ ሁኔታነት የቀረቡት ጉዳዮች በሐምሌ ወር ለማካሄድ ዕቅድ ከተያዘለት ሁለተኛ ዙር የግድቡ የውሃ ሙሌት በኋላም ድርድሩ እንደሚቀጥል ማረጋገጫ ከተሰጠ፣ እስካሁን በተደረጉ ድርድሮች ስምምነት የተደረሰባቸው ሁሉም ጉዳዮች ላይ አገራቱ የመጨረሻ ፊርማቸውን እንዲያኖሩ እና ድርድሮች የሚካሄዱበት ግልጽ የጊዜ ሰሌዳ እንዲኖር የሚሉ ናቸው።

ሱዳንና ግብጽ ሕጋዊና አስገዳጅ ስምምነት ሳይፈረም ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት እንዳታካሂድ አጥብቀው ሲቃወሙ ከመቆየታቸው አንጻር ይህ የሱዳን ጥሪ የአቋም ለውጥ እንደሆነ እየተነገረ ነው።

የአፍሪካ ሕብረትና አሜሪካ በተለያዩ ወቅቶች ሦስቱን አገራት ለማሸማገል ለተራዘመ ጊዜ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም በየትኛውም ድርድር ሁሉንም ከሚያስማማ ውጤት ላይ ለመድረስ አልቻሉም።

ግብጽና ሱዳን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የምናገኘውን የውሃ መጠን ይቀንሰዋል በሚል ተደጋጋሚ ተቃውሞ ሲያቀርቡ የቆዩ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ግን የግድቡን ውሃ ለ65 ሚሊዮን ዜጎቿ የኤሌትሪክ ኃይል ለማቅረብ የምጠቀምበት በመሆኑ ችግር አይፈጥርም በማለት ስጋታቸው ተገቢ እንዳልሆነ ስትገልጽ ቆይታለች።

ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታው እየተካሄደ ያለውና ግንባታው ከተጀመረ አስር ዓመት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከአፍሪካ ትልቁ እንደሆነ የሚነገር ሲሆን፣ ከአምስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችል አቅም ያለው ግዙፍ ግድብ ነው።

የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ባለፈው ዓመት ክረምት ላይ የተከናወነ ሲሆን ሁለተኛው ዙር ደግሞ በመጪው የሐምሌ ወር እንደሚከናወን ኢትዮጵያ ያስታወቀች ሲሆን፤ በሚጥለው ዓመት በተወሰነ ደረጃ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ይጠበቃል።

Leave a Reply