Site icon ETHIO12.COM

ለማይሞት ታሪክ የሚሰዋ ማንነት

የፍቅርና ተስፋ እንዲሁም የአንድነት እሴቶችን በሰፊው ያቀፈችው ፣ ለሰላም ባላት የፀና አቋም ከራሷ አልፋ ለሌሎች ሰላም ከቋጥኝ ጫካው ውላ ያደረችው ኢትዮጵያ ፣ ያልነካትን የማትነካ ፣ አክባሪ እንጂ በማይመለከታት የምትገባ ተንኳሽ አይደለችም ።

ለክብሯ እና ለሉዓላዊነቷ ትዋደቃለች እንጂ ሌሎችን ለመጉዳት አስባ አታውቅም። ለነኳት ግን አልተነረበረከከችመረ ፡፡ ታሪክ ማስረጃ ነው። ኢትዮጵያን የማትነካዋን ነክተው በግድ ቆስቁሰው አመድ ሆነው እንደ ጉም ከመበታተን አስቀድሞ ለጋራ ጥቅም በጋራ ለመስራት እና ተከባብሮ የመኖር እሳቤን የመሰነቅ እድል የምትሠጥ ነገን ዛሬ ላይ የመቋጨት ራዕይ ያላት ሀገር ናት።

ህይወትን በድሎት እየመሩ ሌላው በድህነት ተጨናብሶ ይኑር የሚል አስተሳሰብ ፣ ራስ ወዳድነት ፅንፍ እንደረገጠና የስግብግብ ሆድ አደር የጠላት ባህሪያትን የሚያሳይ ሲሆን ፤ በመተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ፣ ለጋራ ጥቅም አብረን እንስራ የሚለው የሀገራችን አካሄድ ግን ምን ያህል ከራስ አልፎ ለሌላው በሚለው እሳቤ ከጨለምተኞች እንደላቀች እና በዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ከብኩኖች ሁሌም አንድ እርምጃ እንደቀደመች ማሳያ ነው ።

የሀገር ሉዓላዊነት ተገፎ ሰላም እማይታሰብ ነው ። አትንኩኝ ብትል ራሷን አርቃ ከመንካት ተቆጥባ ነው። በአሳማኝ ምክንያት የራስን የተፈጥሮ ሀብት በራስ መጠቀም መብት እንጂ ከማንም የምንቸረው እና በይሁንታ የምናገኘው አይደለም ።

አስመሳይ በሆነ የቅዠት አለም ውስጥ ራስን አስከብሮ አገርን አፍርሶ በራሱ የሚነግስባት ሀገር ለመመሥረት የሚያስከፍለው መሰዋእትነት ቢከብድም ለመመሳሰል ተብሎ ማንነቷ የተገፈፈ ፣ ማንነቷ የጠፋ እና ያላትን ስብዕና ያጣች ሀገር ከማኖር ፣ በተጣበቀ አንጀት እና በጠወለገ ሰውነት የክብሯን ዙፋን የያዘች ሀገርን እንመርጣለን ።

ሁሌም ለቆምንለት አላማ እና ለጨበጥነው እውነት የምንሞት እንጂ ፣ በተሽሞነሞነ ቃል ታብየን አንገት የሚደፋ ማንነት እና ብዙ ስለተጮኸ የሚበረግግ ልብ የለንም።

ለጥሩ መሳይ አስመሳይ የማትመች ፣ በጭፍን እሳቤ እና ጭብጥ ባልቋጠረ ወቀሳ የማትሸበር ፣ በውጣ ውረዱ ቢደክሙ እንጂ በክፋታቸው ልክ ቅንጣት እማያተርፉባት ሀገር ብትኖር ኢትዮጵያ ናት።

ብትኖር በራሷ ዛቢያ ግን ለጋራ ጥቅም በጋራ የምትሰራ ሲሆን ያን ለማስከበር ደግሞ ሀገሩን ከቀዬው ፣ ህዝቦቿን ከወዳጅ ዘመዶቹ አስበልጦ ራሱን ከዱር አውሎ እያሳደረ የሚጠብቅ ታማኝ ወታደር አላት ።

የኢትዮጵያ ወታደር እምነቱ ፅኑ ፣ የአደራ ቃል ያለበት እና የተጣለበትን እምነትና የተቀበለውን አደራ ለመወጣት ወበቅ እና ብርዱን በበረሃ ተቋቁሞ እሚዋደቅ ፣ ቃል አባይ ከመሆን መስዋትነትን የሚመርጥ ፣ ጀግንነትን ከታሪክ አርበኞች የወረሰ ፣ እንደ ጥንቱ ሁሉ በሀርረ ክብር ላይ የማንም ቀማኛ ሲረማመድ ከማየት አንዴ እንጂ ደግሞ ማይኖራትን ህይወቱን በሀገር ፍቅር ሂሳብ አሳልፎ የሚሰጥ ኩሩ ወታደር ነው።

እኛም የጀመርነውን እንጨርሳለን ። ያ ደግሞ አባቶቻችን ያሳዩን እና የምንታወቅበት የተግባር ታሪካችን ነው። ላወራ ሁሉ ቆሞ መልስ መስጠት ለሰነቅነው ራዕይ መንገድ ከሚያስቱ ምክንያቶች አንዱ ስለሚሆን ፣ ንቆ ማለፍን ባህል በማድረግ ሁሌም ተግባር ላይ ልናተኩር ይገባል ።

አላማችን ነገን ብሩህ ማድረግ ነው። ተስፋችን ለምልማ በብርሃን የታጀበች ሀገር ገንብተን ማየት ነው ። ያን ለማድረግ ሁሉ በእጃችን ነው ። ከሌላው የምንሻው በመደጋገፍ እና በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነት ለጋራ ጥቅም የሚል እሳቤን ብቻ ነው ።

ቢገለጥ ተነቦ ማያልቅ ማንነት ያላት ሀገራችን ታሪክ ታሪክን ይደግማል እንጂ በማንም ምላስ ቅንጣት ስንዝር የኋሊት አትመለስም ።

ተስፋ የሰነቀው ራዕያችን የምናሳካው በራሳችን ትከሻ እንጂ በማንም ጫንቃ አይደለም ። ጀግናው ሰራዊት ደግሞ እንኳን ለሀገሩ ለጎረቤቱና ለአለም ቀድሞ በመድረስ ወደር የሌለው ሲሆን ፣ ይህም ሀገራችንን ኢትዮጵያን በክብር ማማ ላይ በማስቀመጥ የተመሰገነች እንድትሆን አድርጓታል ።

ሰራዊታችን ከማንም በፊት ከአርበኛ አባቶቻችን የወሰደውን አደራ እና የገባውን ቃል ኪዳን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ውድ ህይወቱን በመክፈል ፅንፈኛ እና ወራሪውን ኃይል ከጅምሩ በማስቀረት ለእናት ሀገሩ ኢትዮጵያ የገባውን ቃል በተግባር እያሳየ ይገኛል ።

“ከራስ በፊት ለሕዝብ እና ለሀገር ” የሚለውን እሴቱን ተላብሶ የሚኖር ፣ የሚሰጠውን ማንኛውንም የግዳጅ ተልዕኮ በጀግንነት የሚፈፅም ፣ የሕዘብ ሀብት የሆነው እና በአለም በመልካም ስሙ የሚታወቀው ሰራዊታችን ፤ አንዳንድ ጋጠወጥ ባንዳዎች ስሙን አጠልሽተው ፣ የሌለውን ጭካኔ በበሬ ወለደ አጉልተው የአለም ማህበረሰብን ለማሳሳት ቢጥሩም አይሳካላቸውም ፣ ሰራዊታችን ጀግንነትን በተጎናጸፈ ማንነቱ ፣ ዘውድ በጫነ ራሱ፣ ሕዝብን ከራሱ እያስቀደመ ቃልን በተግባር እያስደገፈ ፣ ሀገርን ከፅንፈኛ ፈንጪዎች ፣ ዳር ድንበሯን ከወራሪዎች እየጠበቀ ይባስ ከመጣም ለማይሞት ታሪክ እንደቀደምት ጀግኖች ሁሉ ራሱን እየሰዋ ደማቅ አሻራውን ለትውልድ በቅብብሎሽ እያስተላለፈ ይቀጥላል ።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ተከብራ ትኖራለች !

መ/ወ/ር የኃላሸት ሶርሳ – defence Fb

Exit mobile version