ETHIO12.COM

ዜና ምርጫ – አጫጭር መረጃዎች

የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል የምርጫ ታዛቢዎቹን ከነገ ጀምሮ እንደሚያሰማራ ተገለፀ ሰኔ 11-2013

በኢትዮጵያ የፊታችን ሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ለሚካሄደው 6ኛው አገራዊ ምርጫ የዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን አካል የሆነው “የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል” ከነገ ጀምሮ ታዛቢዎቹን እንደሚያሰማራ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።“የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል” ታዛቢ ቡድን ከ10 አባል ሃገራቱ የተውጣጣና 28 አባላት ያሉት ሲሆን በኦሮሚያ፣ አማራ፣ አፋር፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ክልል፣ ድሬ ዳዋ እና በአዲስ አበባ ተዘዋውሮ የምርጫውን ሁኔታ የሚታዘብ ይሆናል ተብሏል።ምንጭ-ኢብኮ

May be an image of 1 person, standing and text that says '#EASF4PEAC EASF Election Observer Mission Ethiopia June 2021'

ፕሬዘዳንት ሣህለ ወርቅ ከአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን ጋር ተወያዩ

ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የተመራው የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን ጋር ተወያየ፤ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ከ45 በላይ አባላት እንዳሉት ተገልጿል፤ በተመረጡ የምርጫ ጣቢያዎች በመዘዋወር ቅድመ ምርጫ ፣ የምርጫ ቀን እና በድህረ ምርጫ ያሉትን እውነታዎች እንደሚታዘብ ይጠበቃል፣

ፕሬዘዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዘዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ከተመራው የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን ጋር ተወያይተዋል።ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡት የምርጫ ታዛቢ ቡድኑ ከ45 በላይ አባላት አሉት።በተመረጡ የምርጫ ጣቢያዎች በመዘዋወር ቅድመ ምርጫ፤ የምርጫ ቀን እና በድህረ ምርጫ ያሉትን እውነታዎች እንደሚታዘብ ቡድኑ አብራርቷል።

ፕሬዘዳንት ሣህለ ወርቅ የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ከመሆኑም በላይ የቀድሞውን የናይጄሪያ ፕሬዘዳንት ኦባሳንጆን በቡድን መሪነት መመደብ አመስግነው፤ለቡድኑም መልካም የሥራ ጊዜ ተመኝተዋል።በተጨማሪም ”ምርጫ በእራሱ ግብ አለመሆኑን:፤ካለፈው እያሻሻልን እንደምንሄድ፤ለምርጫ ስኬት ብቸኛ ፎርሙላ እንደሌለ አብራርተዋል።ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን በአባልነትና በመምራት በአፍሪካ ሀገሮች ምርጫ መታደማቸው አይዘነጋም።ምንጭ-ፕሬዝደንት ጽ/ቤት

6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለመዘገብ ሰማኒያ ዘጠኝ አለም አቀፍ ጋዜጠኞች ኢትዮጵያ ገቡ

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣንአዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2013 (ኢዜአ) እስከ ዛሬ ባለው መረጃ ሰማኒያ ዘጠኝ አለም አቀፍ ጋዜጠኞች 6ኛውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምርጫ ለመዘገብ ፍቃድ አግኝተው ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አስታወቀ።

አሃዙ እስከ አሁን ምርጫውን ለመዘገብ ፍቃድ ያገኙ የ29 የውጭ ሚዲያዎች ጋዜጠኞች ብዛት ብቻ መሆኑንና በቀጣይም ጥያቄ አቅርበው ለመዘገብ የሚገቡትን ዝርዝር ይፋ እንደሚያደርግ ባለስልጣኑ ገልጿል።

እስካሁን ባለው መረጃ ጋዘጠኞቻቸውን የወከሉ የውጭ ሚዲያዎች ቢቢሲ፣አልጀዚራ፣ ኒውዮርክ ታይምስ፣ ሮይተርስ፣ ኤ.ኤፍ.ፒ፣ ቪ.ኦ.ኤ፣ ኤ.ፒ፣ ዶቼ ዌሌ፣ ፈይናንሻል ታይምስ፣ ስካይ ብሮድካስቲንግ፣ ከዮዶ ኒውስ፣ አውስታራሊያን ብሮድካስት፣ ዴት ዜይት፣ ዬሌ ብሮድካስት፣ ዣይስ ኒውስ፣ ፍራንክፈርት ሩንዶሽ፣ ዜድ ዲ. ኤፍ ጀርመን ቲቪ፣ ናሽናል ፕብሊክ ሬዲዮ (ኤን ፒ.አር)፣ ቬሪጀስ ሬዲዮ፣ ጃፓን ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ስዊድን ደጀንስ፣ ዴር ስተርን፣ ፊኒሽ ብሮድካስቲንግ፣ ትሮው ሚዲያ፣ አሽራቅ ኒውስ ሰርቪስ፣ ኖርዊጂያን ብሮድካስቲንግ፣ ኤጅንሲያ ኤፍ ኤም፣ ሲ.ኤን.ኤን እና ሲ.ቢ.ኤስ መሆናቸውን የባለስልጣኑ መረጃ ያሳያል።

ቦርዱ በድምጽ መስጫ ዕለት ክልከላ ስለተደረገባቸው ተግባራት ማብራሪያ ሰጠ

ሶሊያና ሽመልስ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በድምጽ መስጫ ዕለት የተከለከሉ ናቸው ባላቸው ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል።የቦርዱ የኮሙኒኬሽን ሃላፊ ሶሊያና ሽመልስ በሰጡት መግለጫ በመጪው ሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በሚካሄደው የድምጽ አሰጣጥ የተከለከሉ ድርጊቶችን በዝርዝር ገልፀዋል።

በእለቱ በቦርዱ እውቅና ከተሰጣቸው አካላት ማለትም ከምርጫ አስፈጻሚዎች፣ ከጋዜጠኞችና ከዓለም አቀፍ ታዛቢዎች በስተቀር በ200 ሜትር ከባቢ ውስጥ ሆኖ መመልከትም ሆነ መቆም አይፈቀድም።መራጮችም ድምጽ ለመስጠት ወደ ምርጫ ጣቢያ ሲመጡ የሚደግፉት ፓርቲ ምልክት ያለበት ቲሸርት፣ ፖስተሮችና ማንኛውንም የፓርቲ የድጋፍ መልዕክት ያለበት ቁሳቁስ ይዘው መግባት አይችሉም።እውቅና ከተሰጣቸው አካላትና ከመራጮች በስተቀር ማንኛውም ሰው በምርጫ ጣቢያው 200 ሜትር ራዲየስ ወይም አካባቢ ውስጥ በመሆን የሚገባና የሚወጣውን ሰው ማየትም የተከለከለ ነው።

የኮሙኒኬሽን ሃላፊዋ በዕለቱ ማንኛውም የድጋፍም ሆኑ የተቃውሞ ሰልፎች፣ ቅስቀሳዎች ማድረግ በጥብቅ የተከለከለ እንደሆነም አክለዋል።ድምጽ ሰጪዎች ሲገቡና ሲወጡ በርቀት መመልከት፣ ማባበያ የሚመስል ነገር ማሳየት የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን ሚስጥራዊነት የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን ነጻነት በሚጋፋ መልኩ መንቀሳቀስ የማይቻል መሆኑንም ተገልጿል።የጦር መሳሪያ ይዞ በምርጫ ጣቢያ አካባቢ መገኘት የማይቻል መሆኑንም እንዲሁ።

የፓርቲ ወኪሎች፣ የታዛቢዎችና የጋዜጠኞችን እንቅስቃሴ ማስተጓጎል ክልከላ የተደረገበት እንደሆነም ጨምረው ገልጸዋል።የምርጫ ቁሳቁስን በተመለከተ እሸጋው ሙሉ በሙሉ መጠናቁንና የስርጭት ስራው ከአዲስ አበባ በስተቀር በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች እየተከናወነ እንደሆነም ጠቁመዋል። (ኢዜአ)

Exit mobile version