የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ምርጫው ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየተከናወነ እንደሚገናኝ ገለጸ

ምርጫው ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየተከናወነ እንደሚገናኝና መራጮችም ድምጻቸውን እስካሁኑ ሰዓት ድረስ እየሰጡ እንደሆነ ምርጫውን እየታዘበ የሚገኘው የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ገለጸ።

የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል 12 ቡድን ያሉትን የምርጫ ታዛቢዎች በአምስት ክልል ማሰማራቱን ገልጿል።

የምርጫ ታዛቢዎቹን ካሰማራባቸው 96 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ የተወሰኑት ላይ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ዘግይቶ መጀመሩን አመልክቷል።

መራጮች መሳተፋቸውን አመልክቶ እስካሁን በምርጫው ሂደት ላይ ምንም አይነት ችግር አለማጋጠሙን ለኢዜአ በላከው መግለጫ ገልጿል።

ከፍተኛ የመራጮች ቁጥር ባሉባቸው አካባቢዎችም ጠንካራ የጸጥታ ቁጥጥር ሲካሄድ እንደነበር አመልክቷል።

በተጨማሪም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶችና ወጣቶች መሳተፋቸውን የገለጸው የታዛቢ ቡድኑ፤ ለአረጋውያንና ለአካል ጉዳተኛ መራጮች ቅድሚያ መሰጠቱን ጠቁሟል።

በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎችም የወረቀት እጥረት ማጋጠሙን ገልጿል።

ህብረተሰቡ የምርጫው ስነስርዓት እስኪጠናቀቅና ውጤቱ እስኪገለጽ ተረጋግተው ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲጠብቁ ጥሪውን አቅርቧል።

የጸጥታ አካላትም ሙያዊ ሃላፊነትን በተከተለ መልኩ የጸጥታ ስርዓትን እንዲያስከብሩ አመልክቷል።

የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል የምርጫ ታዛቢዎቹን ከሰኔ 12 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ማሰማራቱ ይታወቃል።

28 አባላት ያሉት ታዛቢ ቡድኑ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ አፋር፣ ሲዳማና ደቡብ ክልሎች እንዲሁም ድሬዳዋ እና በአዲስ አበባ ተዘዋውሮ የምርጫውን ሁኔታ እየታዘበ ነው።. ሰኔ 14 ቀን 2013 (ኢዜአ)

Leave a Reply