ETHIO12.COM

ትህነግ እየተቃረመ ነው – ውጊያ የለም

ለኢትዮጵያ “አለኝታ” የሚባለው የመከላከያ ሰራዊት በሽብርተኛነት የተፈረጀውን የትህነግ ቀሪ ሃይል እያሰሰና እየቃረመ እንደሚገኝ ባስታወቀበት መልዕክቱ አሁን የደረሱበት ስፍራ ይገባበታል ተብሎ ከማይታሰብ ቦታ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። በዚህም በቁጥር ባይገለጽም ” ጠላትን ማጽዳት ተችሏል” ተብሏል። በአሰሳው ቡድኑ ዘርፎ አከማቸው የተባለ ጤፍ፣ የስንዴ ዱቄት፣ ብርድ ልብስ፣ አንሶላ፣ አዲስ ለሚመለመሉ ልብስ፣ እንዲሁም ጊታቸው ረዳ የሚጠቀምባቸው በርካታ የመገናኛ መሳሪያዎች ተይዘዋል።

አብይ አሕመድ ልዩ ኮማንዶና የሪፐብሊካን ዘብ ሲያደራጁ፣ ትህነግ የበተነውን የፓራ ኮማንዶ ሰራዊት መልሰው ሲተክሉ አብዛኞቹ የትህነግ አመራሮችና አክቲቪስቶች ስድብ ይሰነዝሩ ነበር። አሁን እንደሚወጡ ዘገባዎች ይህ ሃይል ከአየር እየወረደ፣ ምድር ለምድር እየተሳበ፣ ክተራራ ተራራ እየተንጠላጠለ ከፊታቸው በመቅደም የሚሸሸውን ሃይል የሚያጠቃውና የሚያዙትን የሚለቅም እሱ ነው።

በጀግናው አሉላ አባ ነጋ ስም የተሰየመው አዲስ ኦፕሬሽን በሶስት አቅጣጫ በድርጌድ ሁለትና ሶስት ታግዞ ጥቃት እንደሚከፍት በኖርዌይ የሚኖሩ ፕሮፌሰር ሼትል ” አቶ ጊታቸው አሁን ነገሩኝ” በሚል በሰበር ዜና የገለጹት ውጊያ እስካሁን አልተሰማም። ይልቁኑም የ21ኛ ጉና ክፍለ ጦር ህብረት ዘመቻ ቡድን መሪ ሌ/ኮ ብርሃኑ እንዳሉት፣ ዘመቻው አሰሳና ማጽዳት ነው እንጂ ጦርነት አይደለም።

የኢትዮጵያ መከለክያ ሰራዊት እዚህ ውስጥ ገብቶ ነው አሰሳ የሚያካሂደው

ቀደም ባሉት ጊዚያት የጁንታው ሃይል ሊያንሰራራ በማይችልበት መልኩ የተመታና በየጥሻው የሚሹለከለክና ወደ ሌብነት የተቀየረ መሆኑንን ሌተናል ባጫ ደበሌ መግለጻቸው አይዘነጋም። ይህንኑ ተከትሎ አቶ ጌታቸው ረዳ ጀነራሉን ሲሳደቡ የሚያሳይ ረዥም ቪዲዮ ከበረሃ ማሰማታቸውም አይዘነጋም። ዛሬ የመከላከያ ይፋዊ የፌስ ቡክ ገጽ ይፋ እንዳደረገው ሰሞኑን በተደረገው በፈታኝ መሰናክል የታጀበ የአሰሳ ውጊያ ፣ የአካባቢውን አስቸጋሪ ተራራና አቀበት በመጋፈጥ ጠላትን ማፅዳት መቻሉን ተረጋግጧል። ከማህበራዊ ገጻቸው የተገኘው መረጃ እንደወረደ የሚከተለው ነው።

1 / 6

በተወሰደበት እርምጃ የጁንታው አፈ ቀላጤ ጌታቸው ረዳ ታጣቂ ኃይሉን ብቻ ሳይሆን የመዋጊያ ንብረቶቹንም ጭምር በየቦታው ማዝረክረኩን የ21ኛ ጉና ክፍለ ጦር አስታወቀ ፡፡

የደቡብ ዕዝ 21ኛ ጉና ክፍለ ጦር የሠራዊት አባላት ፣ የማይሰበር እልህና ወኔ ሰንቀው ጁንታው በዕብሪት ተወጥሮ በሀገራችን የጀመረውን ጦርነት በማክሸፍ የሀገራችንን ሉአላዊነት በማስከበር የህግ የበላይነትን እንዲረጋገጥ እያደረጉ እንደሚገኙ የ21ኛ ጉና ክፍለ ጦር ህብረት ዘመቻ ቡድን መሪ ሌ/ኮ ብርሃኑ ኃይሉ ተናግረዋል ።

ሰሞኑን በተደረገው በፈታኝ መሰናክል የታጀበ የአሰሳ ውጊያ ፣ የአካባቢውን አስቸጋሪ ተራራና አቀበት በመጋፈጥ ጠላትን ማፅዳት መቻሉን አረጋግጠዋል ፡፡ በተለይም የጁንታው አፈቀላጤ የሆነው አቶ ጌታቸው ረዳ ሲፈረጥጥ አንጠባጥቧቸውና ደብቋቸው የነበሩትን ወታደራዊ ንብረቶች በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ገልፀዋል።

ከተያዙት ወታደራዊ ንብረቶች ውስጥ ፣ ከዘጠኝ በላይ የመገናኛ ሬዲዮኖች ፣ አስራ ሦስት ካርቶን ባትሪ ፣ መጠናቸው የተለያዩ ሁለት ጀነሬተሮች ፣ አስራ ሁለት ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ከሦስት መቶ ጥይትና ከአስር የጥይት ካዝና ጋር በቁጥጥር ስር መዋሉን አረጋግጠዋል ፡፡

ዘመቻ መኮንኑ ፣ ሽብርተኛው በተለያዩ ቦታዎች የደበቃቸው ከ 280 በላይ ኩንታል ጤፍ ፣ ከ 20 ኩንታል በላይ የፊኖ ዱቄት ፣ 120 ብርድ ልብስ ፣ 50 አንሶላን ጨምሮ የተለያዩ ንብረቶች ተይዘዋል ፡፡

ሽብርተኛው ጁንታ በየጊዜው ለጥፋት የሚመለምላቸው ወጣቶችና ሞቶ የተቀበረውን ጁንታ ተመልሶ ይመጣል በሚል ቀቢፀ-ተስፋ የተጠለፉ ሠልጣኝ ምልምሎቹ የሚለብሱት አምስት ከረጢት በላይ አልባሳትና ልዩ ልዩ መገልገያ ቁሳቁሶቹንም በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ነናግረዋል ፡፡

የጁንታው ታጣቂ ሃይል ከሲቪል ተቋማትና ግለሰቦች ዘርፏቸው የነበሩ ጤፍ የጫኑ ሁለት የጭነት ተሽከርካሪዎችን አውድመው መሰወራቸውንም ሌ/ኮ ብርሃኑ ኃይሉ ጨምረው ገልፀዋል።

የጁንታው አፈ ቀላጤ ሰራዊቱ አይገባበትም ብሎ ከተማመነበት ሸጥ ድረስ እግር በእግር ተከታትሎ በመዝለቅ ፣ ለፍርድ ያልቀረቡትን ተፈላጊዎች በከፍተኛ እልህ ፣ ወኔና ጀግንነት በማደን ላይ እንደሚገኙ የገለፁት ሌ/ኮ ብርሃኑ ፣ የ21ኛ ጉና ክፍለ ጦር የሰራዊት አባላት የተሰጣቸውን ተልዕኮ ሁሌም ቀን ከሌት በከፍተኛ ሞራል ፣ ዲሲፕሊንና ወታደራዊ ጨዋነት በመፈፀም የላቀ የማድረግ አቅም እንዳላቸው አረጋግጠዋል።

ብርሃኑ ወርቁ ( ከግዳጅ ቀጣና ) ፎቶግራፍ አብርሃም ሸዋቀና

Exit mobile version