“ከደብረ ታቦር እስከ ጨጨሆ በተካሄደው ውጊያ በአሸባሪው ህውሃት ላይ የተመዘገበው አኩሪ ድል በቀጣይ ተልዕኮም ይደገማል” በማለት የ34ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ተወካይ ኮሎኔል ያለው አድማስ ከሃያ አራት ሰዓት በፊት አስታውቀው ነበር። የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን ይፋ እንዳደረገው ደብረ ዘቢጥ የጠላት መቀበሪያ ሆነች፤ሙሉ በሙሉ ነጻ ወጣች” ሲሉ በወገን ሃይሎች ቁጥጥር ስር መዋሏን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ይፋ አደረገ።

አቶ ጌታቸው ረዳ ከሃምሳ ጊዜ በላይ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ስም እየጠሩ እርግማንና ስድብ ባሰሙበት የትግራይ ቲቪ ውይይታቸው ላይ ” እየቸረስናቸው ነው። ምንም ምድራዊ ሃይል የሚቀይረው የለም። የእኛ ተዋጊዎች አናት እየመረጡ የሚመቱ ናቸው…” በሚል ከቀናት በፊት መናገራቸው ይታወሳል።

እሳቸው ይህን ቢሉም የአማራ ልዩ ሃይል አመራሮች፣ አስተዳደሩና የመከለከያ መኮንኖች “የገባው ወራሪ ህይል እንዳይወጣ ተደርጎ እንዲመታ ስራ እየተሰራ ነው” በሚል ሲዘጋጁበት የነበረው ውጊያ በታሰበው መልኩ እንደሱ እንደሚፈልጉት እየሄደ እንደሆነ ሲያስታውቁ ነበር።

 በደብረ ታቦር ዙሪያ፣ በጋሳይ፣ በክምር ድንጋይና በጉና አካባቢዎች በተካሄደው ውጊያ ከፍተኛ ድብደባ የደረሰበት የትህነግ ቡድን 120 ኪሎ ሜትር አፈግፍጎ የመሸገበት የደብረ ዘቢጥ ኮረብታና ጋራ ተከቦ እየተመታ እንደሆነና የሚረዳው ሃይልም ሆነ የሎጂስቲክ ድጋፍ እንዳያገኝ ተደርጎ በተካሄደ እርፍት የነሳ ማጥቃት ደብረ ዘቢጥ ሙሉ በሙሉ ነጻ መውጣቷን ነው ፖሊስ ያስታወቀው።

በርካቶች መማረካቸውና መገደላቸውን ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች አመልክተዋል። ይህን ዜና አስመልክቶም ሆነ ከሌሎች አካባቢ “ትህነግ ተመቶ ለቋል” ስለመባሉ በይፋ ምላሽ አልሰጠም። ቃል በቃልም የትኛውን ቦታ እንደያዘና የትኛውን ቦታ እንደለቀቀ አላስታወቀም።

አቶ ጊታቸው ከቀናት በፊት በትግራይ ሚዲያ ሃውስ ይህንን በግልጽ እንዲያብራሩ አልተጠየቁም። እሳቸውም በደጋፊዎቻቸውና በማያቋርጥ እርዳታ ትህነግን ለሚረዱ አካሎቻቸው ግልጽ ያለ መረጃ አልሰጡም። አዲስ አበባ በመግባት በሳምንት ጊዜ ውስጥ ወደ እስር ቤት የሚጣሉትን እስር ቤት ወርውሮ አዲስ መንግስት እንደሚያቋቁም በስፋት በአቶ ጌታቸው በኩል ሲያስነግር የነበረው ትህነግ፣ ወደ ክልሉ እየተሸበሸበና ሽንፈት እየደረሰበት ነው መባሉ በበቂ ሁኔታ አለመስተባበሉ ወይም በቂ ምላሽ አለመስጠቱ ከጉምጉምታ በላይ እየሆነ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ያስቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ በማንሳት ወደ ድርድር እንደሚያመራ እያስታወቀ ያለው ትህነግ፣ የጦር ሜዳ ውሎውን አስመልክቶ እንደወትሮው መረጃ የማይሰጥ መሆኑ፣ አቶ ጌታቸውም ቢሆኑ በየቀኑ መንገድና ስፋራ እየመረጡ ” በየት በኩል ወደ አዲስ አበባ እንግባ፣ በህር ዳር እንድረስ፣ ጎንደር በጃችን ነው…” ሲሉ እንዳልነበር አሁን ላይ ዝምታን መምረጣቸው ደጋፊዎቻቸውን እንዳስደነገጠ እየተሰማ ነው።

ዛሬ እንደተሰማው ደብረ ዘቢጥ ሙሉ በሙሉ በመከላከያና በአማራ ልዩ ሃይል እጅ መውደቋ ወደ ላሊበላ በመሄድ የመጨረሻውን ኦፕሬሽን ለማካሄድ መንገድ ከፋች እንደሆነ ተገልጿል።

የአማራ ክልል የተወረረበትን ቦታ እያስለቀቀና ነጻ እያወጣ መሆኑ፣ የአፋር ክልል መልሶ ማጥቃት ተጠናክሮ እንዲካሄድ ዘሬ መወሰኑ፣ ምን አልባትም ከመስከረም መጥባት ጋር ተያይዞ በሁሉም አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ የማጥቃት እርምጃው መጀመር አመላካች እንደሆነ ግምታቸውን የሰጡ አሉ።

Leave a Reply