Site icon ETHIO12.COM

ምርጫውን ሰላማዊ ለማድረግ የሳተላይት ቁጥጥርና የድሮን ቲክኖሎጂ ጥቅም ላይ ይውላል

ምርጫውን ፍጹም ሰላማዊ ለማድረገና ዜጎች በአስተማማኝ ሁኔታ ድምጻቸውን እንዲሰጡ ፖሌስ፣ የአካብባኢ ጸጥታ መዋቅር፣ የክልል ሃይሎች ከሚያደርጉት በተጨማሪ በመላው የፌዴራል እና የክልል ማዘዣ ጣቢያዎች ባሉ የመረጃ መጋራት መሳሪያዎች፣ የሳተላይት ቁጥጥር ስርዓቶች እና የድሮን ቴክኖሎጂ ለዚሁ ዝግጅት መሰማራቱ ተጠቆመ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በነገው ዕለት የሚካሄደውን ጠቅላላ ምርጫን አስመልክቶ ከብሔራዊ ምርጫ ደህንነት ስትራቴጂ ማዘዣ ጋር በተወያዩበት ወቅት ነው ይህ የተገለጸው።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በማዕከላዊ ዕዝ የሁኔታ ክትትል ክፍል ውስጥ ይፋ የተደረገው የብሔራዊ መረጃና ደህንንነት አገልግሎት የምርጫ ደህንነት መድረክ በምርጫ ደህንነት ዘርፍ የተከናወነውን ዝግጁነት አጉልቶ ያሳያል።

የደህንነቱ ዝግጁነት በሁሉም የሀገሪቱ ማእዘናት ላይ አካላዊ ኃይል ማሰማራትን እንዲሁም የሳይበር ደህንነት ማሻሻያዎችን የተመለከቱ ስጋቶችን ማክሸፍን ያጠቃልላል። በመላው የፌዴራል እና የክልል ማዘዣ ጣቢያዎች ባሉ የመረጃ መጋራት መሳሪያዎች፣ የሳተላይት ቁጥጥር ስርዓቶች እና የድሮን ቴክኖሎጂ ለዚሁ ዝግጅት ተሰማርተዋል።

በመግለጫው ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይህንን አዲስ አካሄድና ከብሔራዊ ቁልፍ ተግባራት ቀድሞ ብሔራዊ ደህንነትን በማረጋገጥ ረገድ የተፈጠረውን አቅም ተመልክተዋል።

ከሰሞኑ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በሀገሪቱ የሚገኙ የዲጂታል ሚዲያዎች ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ተከትሎ ከሚደርስባቸው የሳይበር ጥቃት እንዲጠነቀቁ አሳስቧል፡፡ኤጀንሲው ምርጫውን ተከትሎ ዲጂታል ሚዲያዎች ከሚደርሱባቸው የሳይበር ጥቃቶች ራሳቸውን እንዲጠብቁ የሚያስችሉ የሳይበር ደህንነት የጥንቃቄ እርምጃዎች አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በዚህም በሀገሪቱ የዲጂታል ሚዲያ መስፋፋትን ተከትሎ የሚደረግባቸው የሳይበር ጥቃት መጨመሩን ገልጿል፡፡ይህ ተግባር ሀገራት በሚያካሂዷቸው ሀገራዊ ምርጫዎች ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እያሳደረ ይገኛል ይላል መግለጫው፡፡በምርጫ ወቅት በተለይም ከመረጃ ማዛባት ጋር የተያያዙ የሳይበር ጥቃቶች በሰፊው መስተዋላቸውን ኤጀንሲው በላከው መግለጫ ጠቁሟል፡፡

በመሆኑም ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ተከትሎ ዲጂታል ሚዲያዎች የሳይበር ጥቃት ሊደርስባቸው ስለሚችል አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲወስዱ ኤጀንሲው አሳስቧል፡፡በዚህም የሚዲያ ተቋማት የማህበራዊ ሚዲያ እና ድረ ገፅ አስተዳደር እና አጠቃቀምን በተመለከተ የአድሚንስትሬተር ቁጥርን መገደብ ( ከሁለት ሰዎች ባይበልጥ)፣ከዚህ ቀደም የሚጠቀሙባቸውን የይለፍ ቃል በአዲስ እና ጠንካራ የይለፍ ቃል መቀየር ፣ በማህበራዊ ሚዲያ ተደራሽ የሚደረጉ ይዘቶችን የሚያስተዳድር (አግባብነት እና ስርጭት በተመለከተ ) ሀላፊ ሰው በሃላፊነት መመደብ እንደሚገባቸው ኤጀንሲው አሳስቧል፡፡

ችግር ካጋጠማቸው ሪፖርት ማድረግ እንዳለባቸውም ኤጀንሲው ምክረ ሃሳቡን ሰጥቷል፡፡የተቋማት ባለሙያዎች በኮምፒውተር ስርአቶቻቸው ላይ ያልተለመዱ እንቅስቃሴዎች ሲኖሩ ለበላይ አካል ማሳወቅ እንዳለባቸውም ተገልጿል፡፡በተጨማሪም ለኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በነፃ ስልክ መስመር 933 ወይም በስልክ ቁጥር 0993531965/ 0993939270 በመደወል ማሳወቅ እንደሚችሉ በመግለጫው ማመላከቱ ይታወሳል።

Exit mobile version