ETHIO12.COM

የዋዜማው ጥሪ- “ሰላማዊ ምርጫ የውቅቱ ታላቁ ድል ነው”ተክሌ ኤርጊቾ ኦስሎ

No description available.
ተክሌ ኤርጊቾ ሎቤ

አገራችን ኢትዮጲያ በታሪኳ በርካታ መሪዎችና የመንግስታት ስርዓት አስተናግዳለች። ሁሉም መንግስታት በስልጣን ዘመናቸው የየራሳቸዉ ደካማና ጠንካራ የታሪክ አሻራ አሳርፈዋል። ሲመዛዘን መጠኑ እንደፍሬዜቸው ቢለያይም፣ ሁሉም በጊዜያቸው በበጎና በተቃራኒው በአሉታዊ ጎን የሚዘከር ታሪክ አላቸው።

በቅርቡ ከሶስት ዓመታት በፊት ለ30 ዓመታት ያህል ከተቆናጠጠዉ የስልጣን መንበሩ በህዝብ ትግል የተገረሰሰዉ አሮጌው ኢህአዴግ፣ በአገራችን ኢትዮጵያ ካስመዘገባቸው መልካም ተግዳሮቶች ይልቅ፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በኢትዮጵያና ሕዝቧ ላይ ያስከተለው ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀዉስ በጅጉ ያይላል። ይህንኑ ፍሬውን ሁሉም ወገን እያየው ነው።

ለውጡን ተንተርሶ በላፉት ሶስት ዓመታት የታየው መፈናቀልና፣ የዜጎች ስቃይ፣ ግድያ፣ የፖለቲካ ሴራና አሳዛኝ ዜናዎች ሁሉ የዚሁ ከስልጣን የተባረረው ክፍል አሉታዊ አሻራ ውጤት የሆነዉ ርዝራዥ ያካናወነው ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም።

ላለፉት ሶስት ዓመታት፣ ዛሬ ድረስ በአገር ውስጥ የደረሰው ሰብአዊና ቁሳዊ ቀውስ አልበቃ ብሎት በሰላሳ ዓመታት የአገዛዝ ዘመኑ በዘረጋቸዉ ስዉር ኔትዎርኮቹ፣ በስመ ኢትዮጵያዊነት አገራችንን ዉክለዉ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተሾሙት ተላላኪዎቹ፣ ለእንደዚህ አይነት ወቅት ምቹ በሚሆን መልኩ ቀድመው ቀምረውት ባራመዱት የፖለቲካ ትርክት፣ አንዱን ብሄር በሌላዉ ብሄር በማነሳሰት በቀን፣ በጠራራ ጸሃይ፣ ንጹሃን ሲሰደዱ፣ ሲያፈናቅሉ፣ ሲያስገድሉ፣ ሁላችንም ሰምተናል። ሁላችንም አይተናል። ማየት ብቻ ሳይሆን ሃዘናችንን የምንገልጽበት መንገድ እስኪጠፋን ሃዘን ገርፎናል። አልቅሰናል።የሞቱትን ቀብረናል። ለተፈናቀሉት የቅማችንን ያህል በማድረግ ደርሰናል።

በተቃራኒው የዜጎች መከራ የሚስጨፍራቸውን ጉዶች ልባችን እየነደደ አይተናቸዋል። ዛሬም ድረስ ሃዘናችንን ለማራዘምና ቅጥ እንዲያጣ ለማድረግ እየተጉም ነው። ይህ አገራችን ላይ ሆን ተብሎ የተቀመረው የፖለቲካ ትርክት ብሄርን ብቻ መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ማኑፌስቶ ያነገቡ፣ በዚሁ የጎሳ ትርክት የተቃኙ እጅግ በርካታ የፖሊቲካ ፓርቲዎችን እንድናይም ምክንያት ሆኗል።

ይህ የማይበጅ አካሄድ አገራችንን ዛሬ ለደረሰችበት በሽታ ዳርጓታል። ሌላም አለ። ይኸው ላለፉት ሰላሳ አመታት ኢትዮጵያ ላይ ሰልጥኖ የቆየው ቡድን፣ በስመ ኢትዮጵያዊነት አገራችንን ወክለዉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስቀመጣቸውን ሹማምንቶቹን ይገዛት የነበረችውን አገር ለመፈረካከስ ተጠቅሟል። የመጨረሻ በሚመስል መልኩ ያለ የሌላዉን ጉልበትና ስልት ሁሉ በመጠቀም አገራችንን ለማፍረስ በኢትዮጵያ ህዝብ ወኪልነት ያስቀመጣቸውን ታማኞቹን በመጠቀም ያልሞከረው ሙከራ የለም። ግን አልተሳካም!!

አገሪቱን በውክልና ተባብረው መበተን፣ ካልተቻለም የሚደጉሟቸው ክፍሎች የሚመኙትን ስርዓት ጫንቃችን ላይ ዳግም በመዘርጋት በእጅ አዙር ሊገዙን እየተረባረቡብን መሆኑን ሁላችንም የምንገነዘበዉ እዉነታ ስለመሆኑ መከራከሪያ የሚያቀርብ የለም። በዚሁ እሳቤና መሰረት፣ በግልጽና በስዉር፣ ከላይ የተገለጹት ክፍሎች ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ለማንበርከክ በጥምረት እየሰሩ ነው። በዚሁ ክፉ ተልዕኮ ተጠምደዉ ከጫፍ እስከጫፍ በሚባል መልኩ አገራችንን እንድትወጠር አድርገዋል።ምዕራባዊያኑና ጉልበተኞቹ ጎሮቤቶቻችንን ሳይቀር እየተጠቀሙ ከፍተኛ ጫና ዉስጥ ከተውናል።

የዚህ ሁሉ መረባረብ መነሻዉ በዲሞክራሲ፣በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ትስስር የተሻለችና የጠነከረች ኢትዮጵያ የመመስረቷ ጉዳይ ስጋት ስለሆነባቸው ነው። ሌላኛዉ በታሪክ መካከል ለወራሪ ሃይሎች ያልተንበረከከች፣ ለቅኝ ግዛት ህልም አላሚዎች እጅ ያልሰጠች የጠንካራ ታሪክ ባለቤት መሆኗ የፈጠረባቸዉ ራስ ምታት ነዉ። ይህንን የኖረ ሃቅና ያልተሳካላቸው ያቄሙትን ቂም የማይረዳ ኢትዮጲያዊ አለ ብሎ ማሰብ ይከብዳል።

ምንም እንኳን በርካታ ሊታረቁ የሚገባቸው የውስጥ የኖሩ ችግሮች ቢኖርብንም፣ ይህ የተከመረው የውስጥ ጣጣችን ከውጭ ከተነሱብን ጫናዎች ጋር ተዳምሮ እያንገዳገደን ባለንበት ወቅት ወደ ምርጫ አምርተናል። ይህን ሁሉ ችግር ተሽክመን፣ ከላይ እስከታች የተበተበንን የተቀናጀ ሴራ እያከሸፍን ነው የምርጫ መንገድ ስንጠርግ የቆየነው። አንዱን ስናመክን፣ ሌላ እየተጠነሰሰልን ሳንበተን የምርጫውን ጎዳና አቅንተን ዛሬ ላይ መድረሳችን ለእኛ አገራችንን ለምንወድ ድል፤ በተቃራኒው ለሚመኙ ታላቁ ሽንፈት ሆኗል።

በዚህ መስቀለኛ ወቅት የዉስጥ ችግሮቻችንን አቻችለን፣ የዉጭ ተግዳሮቶቻችንን በልካቸዉ ምላሽ በመስጣት የተጀመሩ ልማቶቻችንን የሚያስቀጥል አቅም ያለዉ ፓርቲ በመምረጥ፣ ጠንካራ መንግስት መመስረት ከመቼዉም በላይ ያስፈልገናል። ግድም ነው። ለዚህም ተግባር ደግሞ መሳካት አስተዋጾ ማበረከት የእያንዳንዳችን የዜግነት ግዴታችን መሆኑን ለቅንጣት መዘንጋት የለብንም።

ሌላኛው አንድ መዘንጋት የሌለበትና ሁሉም ኢትዮጲያዊ ሊያዉቀዉ የሚገባዉ እዉነታ የዚህ ሁሉ ዓለማቀፍ ጫና ዋና ተዋንያን በዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንደ ተባበሩት መንግስታትና በእነርሱ በሚመሩ ድርጅቶች ዉስጥ በሰመ ኢትዮጲያዊነት የተቀመጡ ግለሰቦች የመሆናቸው ጉዳይ ነው። ይህን ሁሉ ግንዛቤ ዉስጥ በማስገባት የዉጭ ተግዳሮቶቻችንን በጋራ ለማለፍ ሰላማችን ቁልፍ ሚና አለዉ።

ስለሆነም በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ መንግስት መመስረት የምንችልበትን ድምጽ በመስጣት፣ ብሎም አብላጫ ድምጽ ያገኛዉን የፖለቲካ አካል በጨዋነት አሸናፊነቱን በመቀበል፣ ከዚያም አልፎ ችግሮችን ለመፍጠር በሚደርግ በማንኛዉም ሂደት ባለመሳተፍ፣ መሰል እንቅስቃሴዎች ሲኖሩ ከህግ አካለት ጋር በመተባብርና አስፈላጊውን ሁሉ ማበርከት ግድ ነው።

ካለፈዉ ታሪክ ልምድ በመዉሰድ፣ ለመጪው ትውልድ ልዕልናና ተስፋ ለመሰነቅ፣ በታሪካችን ሌላ አዲስ የሰላም ውብ ታሪክ በማስመዝገብ ጠላቶቻችን እንዲያፍሩ ማድረግ አለብን። ይህን በማድረግ አገራችንን ማራመድ የውቅቱ ጥሪና፣ የውቅቱ ታላቁ ድል ነው። ሰላም ለአገራችንና ለህዝባችን!

ተክሌ ኤርጊቾ ሎቤ ከኦስሎ ዩኒቨርሲቲ

ዝግጅት ክፍሉ – አቶ ተክሌ በኦስሎ ዩኒቨርስቲ ህክምና ፋኩሊት በሞሎክዩላር ማይክሮባዮሎጂ የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ናቸው። በያዝነው ዓመት ፒኤችዲ ያገኛሉ። አቶ ተክሌ በተለያዩ ወቅቶች መልካምና ቀና ሃሳብ የሚያመነጩ፣ ይህንኑ ሃሳባቸውን በማህበራዊ ገጻቸው የሚያጋሩ ኢትዮጵያዊ ናቸው። ኢትዮ 12 እንዲህ ያሉ በጎ አሳብ ያላቸውን ኢትዮጵያዊያን ለሌሎች ዝምተኞች አርዓያ ይሆኑ ዘንዳ ስራቸውን ታበረታታላቸ

Exit mobile version