Site icon ETHIO12.COM

ለምርጫ የወጡ ሰዎችን ቤት ሰብሮ በመግባት ገንዘብ የዘረፈ ግለሰብ በእስራት ተቀጣ

በጎንደር ከተማ ወደ ምርጫ ጣቢያ የሄዱ ግለሰቦች ቤት ሰብሮ በመግባት ጥሬ ገንዘብ ዘርፏል የተባለው ግለሰብ በ1 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጣ እንደተወሰነበት የከተማዋ አስተዳደር አቃቢ ህግ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።የጽህፈት ቤቱ የወንጀል አቃቤ ህግ አቶ ድረስ ዘለለው ለኢዜአ እንደተናገሩት የእስራት ቀጣቱ የተላለፈበት መሃመድ ሃሰን የተባለ ግለሰብ ነው።

ግለሰቡ በከተማው ቀበሌ 18 ከሚኖሩ ግለሰቦች ድምፅ ለመስጠት ወደ ምርጫ ጣቢያ መሄዳቸውን በማወቁ ቤት ሰብሮ በመግባት 18 ሺህ 200 ብር በመዝረፍ ክስ እንደተመሰረተበት ገልጸዋል።ግለሰቡ ገንዘቡን ይዞ ለመሰወር ሲሞክር በፀጥታ ሃይሉ እጅ ከፍንጅ ሊያዝ መቻሉን አስረድተዋል።

አቃቤ ህግ ግለሰቡ ላይ በአስቸኳይ ችሎት በመሰረተበት ክስ የወንጀል ድርጊቱን መፈፀሙ በሰውና ሰነድ ማስረጃ የተረጋገጠበት መሆኑን አመልክተዋል።በዚህም ግለሰቡ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የከተማ አስተዳደሩ ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው አስቸኳይ ችሎት የእስራት ቅጣቱን መወሰኑን አስታውቀዋል።

በአሶሳ የመራጭ ካርድ የቀደደ ግለሰብ ተቀጣ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ የመራጭ ካርድ በመቅደድ የተከሰሰ ግለሰብ በገንዘብ ሲቀጣ በተመሳሳይ ጥፋት የተገኘ ሌላ ግለሰብ ደግሞ በቁጥጥር ስር ውሎ ውሳኔው ለነገ እየተጠበቀ መሆኑ ተገለጸ።የከተማዋ አስተዳደር ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ቡሽራ አልቀሪብ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ግለሰቡ የተቀጣው በከተማው ወረዳ ሁለት ውስጥ የጓደኛውን ምርጫ ካርድ ቀምቶ በህዝብ ፊት በመቅደዱ ነው፡፡

የከተማው ወረዳ ፍርድ በቤት ዛሬ በዋለው ችሎት ግለሰቡ የአንድ ሺህ ብር ቅጣት እንደጣለበት ጠቅሰው፤ “ካርዱ የተቀደደበት ግለሰብ ከምርጫ ጣቢያ ሃላፊዎች ጋር በመነጋገረ ድምጽ እንዲሰጥ ተደርጓል” ብለዋል፡፡ሌላው ግለሰብ ደግሞ የራሱን ምርጫ ካርድ በህዝብ ፊት መቅደዱን ኮማንደር ቡሽራ ጠቅሰዋል።ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ጉዳዩ ነገ በፍርድ ቤት ውሳኔ እንደሚያገኝ አስታውቀዋል፡፡ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በአሶሳ ከተማ በሠላም ሲካሄድ መዋሉን ኮማንደር ቡሽራ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ኢዜአ

Exit mobile version