Site icon ETHIO12.COM

ረሃብን እንደመሹለኪያ

ረሃብ ምድር ላይ ከሚፈጠሩ አስቀያሚ እና የሰውን ልጅ ድምጽ ሳያሰማ በጅምላ የሚጨርስ አደገኛ ክስተት ነው ። ይሁን እንጂ አሁን ላይ ምዕራባውያን ረሃብን በኢትዮጵያ ላይ ለፈለጉት የፖለቲካ ቁማር መቆመሪያ እያዋሉት እያየን ነው ። በረሃብ ስም ለተቸገሩ እንርዳ በሚል ሰበብ አሜሪካ እና እንግሊዝ ረሃብን ለሚፈልጉት የፖለቲካ ማስፈጸሚያ ግብዓትነት እየተጠቀሙ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

ከዚህ ጋር ተያይዞ «የአል ማሪያም » ተንታኝ የሆነው አል ማሪያም ከሰሞኑ ባደረገው ገለጻ ምዕራባውያን ረሃብን እንደምክንያት በመጠቀም በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የሴራ ድራቸውን እያደሩ መሆናቸውን ይናገራል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ኔቶ ወደ ኢትዮጵያ እንዲዘምት ፍላጎታቸውን የሚያንጸባርቁ ብዙዎች ናቸው።

ይህን ሴራ የሚመለከት ማንም ሰው ምዕራባውያን እውነት ስለኢትዮጵያውያን መራብ አንድም ቀን መጨነቅ ይቅርና ለሰኮንዶችም እንደማያስቡ ለማንም የተሰረወ አይደለም ። በረሃብ ስም አሜሪካ እና ተከታይ ጄሌዎቿ የእገሌ ብሄረሰብ ተጎዳ፤ የከሌ ብሄረሰብ ተራበ ለዚህ ደግሞ ተጠያቂው መንግሥት ነው ብሎ ሉዓላዊ በሆነች አገር መንግሥት ላይ ጣት መቀሰር የሚያዋጣ አይደለም ። የሚያስኬድም አይደለም ።

አል ማሪያም በትንተናው አክሎም እንዳመላከተው የአንድ ቀልድ አዋቂን አባባል ተጠቅሞ ምዕራባውያን ጥቅማቸውን ለማሳደድ በየቀኑ ደፍጣጭ እና ሰልቃጭ ቃላትን በመፈብረክ የተካኑ መሆናቸውን ይናገራል። አሜሪካ ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ዩናይትድ ኪንግደም እነዚህን መደፍጠጫ እና መሰልቀጫ ቃላት በመፈብረክ እና የእነዚህ ቃላቶቻቸውን መሸርከቻ ወፍጮዎቻቸውን በመጠቀም ኢትዮጵያን በረሃብ ስም እንደፈለጉ ለማድረግ እሩጫ ላይ መሆናቸውን ይተነትናል። ከሰሞኑም እነኝህ ሀጋራት “የረሃብ ዝናብ በኢትዮጵያ ላይ ይወርዳል” የሚል ሰልቃጭ እና ደፍጣጭ ቃላትን በመፈብረክ አዲስ ዘመቻ በማካሄድ ላይ መሆናቸውን ይናገራል።

ይህንንም የውሸት ገበያቸውን ለማጧጧፍ እና ለመሸጥ “የሰብአዊ ተደራሽነት” ፣ “የሰብአዊ መብት ጥሰቶች” ፣ “ጭካኔዎች” ፣ “ጭፍጨፋዎች” ፣ “የጦር ወንጀሎች” ፣ “የዘር ማጽዳት” እና የመሳሰሉት ወዘተ የሚሉ ማታላያ ቃላትን ይጠቀማሉ የሚለው አልማሪያም ፤ በአውሮፓ እና በአሜሪካ የሚገኙ ነጮች በኢትዮጵያ ላይ ትክክል ያልሆነ ወይም የተንሻፈፈ ሃሳብ እንዲኖራቸው በማድረግ መንግሥታቸው በኢትዮጵያ ላይ እርምጃ እንዲወስዱ በመካከላቸው ቁጣ ለመቀስቀስ እየሰራ መሆኑን ይናገራል።

ሌላው ምዕራባውያን የዓለም አገራትን ከሚያደናግሩበት፣ ለመሰልቀጥ እና ለመደፍጠጥ ከሚጠቀሙባቸው መደለያ ሃሳብ አንደኛው ከግጭት ጋር ተያይዞ የሚከሰት “ወሲባዊ ጥቃት” የሚል ነው። ከግጭት ግር ተያይዞ አይደለም በማንኛውም ሁኔታ የሚደረግ ወሲባዊ ጥቃት ማንም የሰው ልጅ የሆነ ፍጡር የሚጸየፈው ሆኖ ሳለ ምዕራባውያን ግን ለዚህ አጸያፊ ወንጀል ዘብ ቋሚ እንደሆኑ በማራገብ አድራጊ እና ፈጣሪ ራሳቸውን አድርገው በመቁጠር በሌላው የዓለም አገራት ላይ የኢኮኖሚያ ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ጫና በመፍጠር ጥቅማቸውን ያሳድዱበታል።

ምዕራባውያን “ከግጭቶች ጋር የተዛመደ ወሲባዊ ጥቃት በዓለማችን ውስጥ አስጸያፊ እና ተቀባይነት የለውም” ሲሉ በተደጋጋሚ መግለጫን ሲሰጡ ይሰማል።በአንድ ሉዓላዊ አገር ወታደራዊ ጣልቃ ለመግባት በመፈለግ እንጂ ወሲባዊ ጥቃት የሚደግፍ ሀገር እንደሌለ የሚታወቅ ሃቅ ነው ። ነገር ግን ይህን ሰበብ አድርጎ የራስን ጥቅም ለማሳደድ ወሲባዊ ጥቃት በሚል ምክንያት ወታደራዊ ጣልቃ በመግባት የሀገራትን ሉዓላዊ መብት ሲጥሱ በተደጋጋሚ ተመልክተናል።

አሸባሪው ህወሓት በሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ዩኤስ.ኤ.አይ.ዲ እና ሌሎች በዓለም አቀፍ ድህነት ሰበብ የሚቆምሩ ቡድኖች ከረሃብ ጋር የተገናኙ የተራቆቱ ስሞችን ማለትም “እጅግ በጣም የተመጣጠነ ምግብ እጥረት” ፣ “ከባድ የምግብ እጥረት” ፣ “ከፍተኛ የምግብ እጥረት” ፣ “አስከፊ የምግብ እጥረት” “ምግብ ጉድለቶች ”“ አጣዳፊ የምግብ ዋስትና ”፣“ እጅግ በጣም ከፍተኛ የምግብ ፍጆታ ክፍተቶች ”እና ሌሎች ብዙዎች አታላይ አባባሎች እና ቃላትን በመደርደር ኢትዮጵያን እንደፈለጉ ሲመዘብሩ ኖረዋል። ህወሓት ደግሞ ለኢትዮጵያ ጥቅም አንድም ቀን ተጨንቆ የማያውቅ የማፍያዎች ስብስብ ስለነበር ምዕራባውያን የፈለጉትን የተንኮል ድር ኢትዮጵያ ላይ ቢያደሩ ማንም ከልካይ አልነበራቸውም ። አሁን ግን ይህን ማድረግ ህልም ነው።

ምዕራባውያን እነኝህን የማታለያ ቃላቶችን ለመተግበር በሚጋጋጡበት ወቅት ብዙ ጊዜ የሚጣ ረሱ ቃላትን ሲናገሩ ይሰማ ነበር ። ለምሳሌ እ.ኤ.አ. ነሐሴ 15 ቀን 2014 ዩ..ኤስ.ኤ.አይዲ ባወጣው ሪፖርት በኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ ያለ ኢኮኖሚ ቢኖርም በተለይም በገጠሩ ህዝብ እና በአነስተኛ አርሶ አደሮች መካከል በከፍተኛ ሁኔታ “ሥር የሰደደ እና አጣዳፊ የምግብ እጦትና ከፍተኛ ችግር” ማጋጠሙን ይተርካል ። ይህንን ያሉትን ችግር ለማባባስ በኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ከ 5 ዓመት በታች ከሆኑ ሕፃናት ውስጥ በግምት 44% የሚሆኑት በከፍተኛ ሁኔታ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ወይም በችግር የተጋለጡ ብሎ ያክልበታል ። በትግራይ ክልልም ከዚህ “ሥር የሰደደ እና አጣዳፊ የምግብ ዋስትና ችግር መኖሩን ይተነትናል። ለምን ሌሎች ክልሎች አልታይ አሏቸው የሚለው አሁንም እንቆቅልሽ ነው።

ሌላው የህወሓት ሎሌ አሌክስ ዲዋል የተባለ ሰው በዘመነ ህወሓት በአገሪቱ ተፈጥሮ የነበረውን ረሃብ እና ድርቅ ለመሸፈን እ.ኤ.አ. በግንቦት 2016 “በኢትዮጵያ ውስጥ ረሃብ የለም… ኢትዮጵያውያን በረሃብ አይሞቱም… ሰዎች አይሞቱም… እንስሳት ግን በውሃ ጥማት እየሞቱ ነው” ሲል የተጣረሰ ሃሳብ ይናገራል ። “ረሃብ የለም ግን እንስሳት በውሃ ጥም ይሞታሉ ። ” ምን የሚሉት አስተያየት ነው?

ከዚህ የምንረዳው እና በዘመናዊ ዓለም የተፈጠረው የምዕራባውያን የፖለቲካ አካሄድ የቱንም ያህል በአንድ አገር ችግር ቢፈጠር የምዕራባውያንን ጥቅም እስከጠበቀ ድረስ የተፈጠረውን ችግር እንደ ችግር ካለመቁጠርም በዘለለ ጉዳዩን ለመደበቅ በሚፈበርኳቸው የማታለያ ቃላቶቻቸው ሲያደናግሩ እንደሚኖሩ የሚያሳዩ ናቸው ።

የምዕራባውያን ተንኮል አሁንም አልቆመም ። ይህን ተንኮላቸውን ለመደበቅ አድኖ መግደል ዘይቤ ሲጠቀሙ በግልፅ ይታያሉ ። ለምሳሌ አሁን ላይ ማለትም እ.ኤ.አ. በ 2021 በኢትዮጵያ ውስጥ ረሃብ የለም። ነገር ግን በተወሰኑ የትግራይ አካባቢዎች እርሻ እና ሰብአዊ እርዳታን ለማድረስ አስቸጋሪ ሁኔታ እንደገጠማቸው በመግለጽ ችግሩን ለመቅረፍ የእነሱን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እድል ለመጠቀም ይሞክራሉ። በዚያም በሉት በዚያ ምዕውራባውያን የተለያዩ የማታለያ ቃላትን በመጠቀም እና ወታደራዊ ጣልቃ በመፈጸም ትርፋቸውን ለማጋበስ ይጋጋጣሉ።

አሁን ምዕራባውያን ሊገነዘቡት የሚገባው ነገር ቢኖር ለረጅም ዓመታት የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ ሲሰጣቸው የነበረው አሸባሪው ህወሓት ወደ መቃብር ወርዷል። ህወሓት የሚባል ቡድን የለም። ነገር ግን ህወሓት አሁን ላይ ወደተራ ሽፍታነትና አሸባሪነት የተቀየረ እና የምዕራባውያንን ጥቅም ሊያስጠብቅ የሚችልበት የፈዋሽነት አቅሙ የተመናመነ ሙቶ የሞተ ቡድን ነው። ጊዜው ያለፈበት መድኃኒት ሆኗል።

በእርግጥ አሸባሪው ህወሓት አቅም ቢያገኝ ኢትዮጵያን መሸጡ የማይቀር ነው። አሸባሪውና ከሃዲው ህወሓት አገር አፍራሽ እና ወገኖቹን ጠል መሆኑን አሁን የጀመረው አይደለም ። ይልቁንም ሲወለድ ጀምሮ የተጣባው ክፉ ልክፍት እንጂ። ለዚህም ማስረጃ እ.ኤ.አ. ከ1981-1984 የህወሓት መሪዎች መለስ ዜናዊን ጨምሮ “የሰብአዊ ዕርዳታ” የተሰኘውን “ትግራዋይ መረዳጃ ማህበር” (REST) የተባለ ድርጅትን በመጠቀም ለሰብአዊ ዕርዳታ የመጣን ዕርዳታ ለግል ጥቅማቸው ሲያውሉ ቆይተዋል።

የህወሓት መሪዎች ለሰብአዊ ዕርዳታ የመጣን ገንዘብን ሲከፋፈሉ እንደነበሩ ከህወሓት መስራቾች የነበሩ የተለያዩ ግለሰቦች በተለያየ አጋጣሚ ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ከሰጡት ቃለ ምልልስ ተመልከተናል። ለምሳሌ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በትግራይ የተከሰተውን ረሃብ ለማቃለል በወያኔ እጅ ከገባው 100 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 95 ሚሊዮን ዶላር ለጦር መሳሪያ ግዥዎች እና ከረሀብ ማስታገሻነት ጋር ተያያዥነት ለሌላቸው ሌሎች ዓላማዎች መጠቀማቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል ። አቶ ገብረ መድህን አርያ የተባሉ ሌላው የህወሓት ነባር ታጋይ በበኩላቸው ለትግራይ ሰዎች ዕርዳታ የመጣውን ማሽላ በመሸጥ ለጦር መሳሪያ መግዣ እና ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን ከኢሳት ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አረጋግጠዋል።

አልማሪያም ሰሞኑን ጭምር እንደተናገረው እ.ኤ.አ ሰኔ 2 ቀን 2021 ጋርዲያን እንደፃፈው “በሰሜናዊው የትግራይ ግዛት የተባበሩት መንግሥታት የተኩስ አቁም ለማወጅ በኢትዮጵያ ላይ ግፊት እያደረገ ነው። ተናበው ኢትዮጵያን ለማዳከም እየሰሩ የሚገኙት ምዕራባውያን እ.ኤ.አ. ሰኔ 2 ቀን 2021 የዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ አለቃ ሳማንታ ፓወር በትዊተር ገፃቸው ላይ “ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት አስከፊ የሆነ ረሃብ ተመልክታለች እናም በወራት ውስጥ እንደገና ልታዩ ትችላላችሁ“ በማለት ክፉ ምኞታቸውን አንጻባርቀዋል። አደጋዎች (ችግሮች) ከፍ ሳይሉ እና ሳይባባሱ መንግሥት በትግራይ ውስጥ ግጭትን በማስቆም እና ያልተገደበ የእርዳታ ተደራሽነት መፍቀድ እንዳለበትም ይተርካሉ። ተጎዱ ለሚሉት ወገኖች ግን ጠብ የሚል ነገር ሲያደርጉ አይታዩም።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እና ሰብዓዊ ዕርዳታን ያለገደብ ማድረስ በሚል እ.ኤ.አ. ሰኔ 2 ቀን 2021 “ፈረንሳይ እና ጀርመን የዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ ደግፈዋል። ይህንን አጋጣሚ እንደጥሩ እድል በመጠቀም ኢትዮጵያ ውስጥ እጃቸውን በማስገባት ለማተራመስ እየሰሩ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል ።

ይህን ሃሳባቸውን ለማስፈጸም እንዲችሉ የአሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ከ G-7 በፊት በኢትዮጵያ ላይ ትኩረት እንዲሰጥ ለማድረግ ያቀደ ስብሰባ አድርገዋል። ሆኖም ግን የያዙት ሃሳብ ውሃ የሚቋጥር ባለመሆኑ ኢትዮጵያን ከመውቀስ ባለፈ ይህ ነው የሚባል ነገር ሊያደርጉ አልቻሉም።

አንዳንድ ተዋንያን የሰብዓዊ ዕርዳታን ሽፋን በማድረግ የሽብርተኛ ክፍሉን በድብቅ ለማስታጠቅ እና መሣሪያዎችን ለማስገባት መሞከራቸውን የሚያመለክቱ ተዓማኒ ማስረጃዎች መኖራቸውን የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል። እንደትላንትናው ሁሉ ዛሬም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመዳፈር ሙከራ ቢያደርጉም ለነጻነቱ ቀናኢ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ሴራቸውን እያከሸፈባቸው ይገኛል።

ጣሊያን እ.ኤ.አ. በ 1935 ወደ 400 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮችን ይዛ ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ እና ኢትዮጵያን የሌጎፍ ኔሽን ማህበርን ተጠቅማ ለማህበሩ አባላት አቤት ባለችበት ዘመን የአውሮፓ ኃያላን በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመውን ግፍ እያዩ እና ባለዩ እና የሰሙትን እንዳልሰሙ ፊታቸውን በኢትዮጵያ ላይ አዙረውባት ነበር ። በዚህም የአውሮፓ ኃይሎች እ.ኤ.አ. በ 1936 በሊግ ኦፍ ኔሽንስ የተንሸዋረረ ፍርድ በማሳለፍ ኢትዮጵያን ለጠላት አሳልፈው ሰጧት ።

ዛሬም እ.ኤ.አ. በህዳር 3 ቀን 2020 በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ ለመናገር በሚዘገንን አኳን አረመኔያዊ ጥቃት የፈጸመውን የሽብር ቡድን የአሜሪካ እና የአውሮፓ ኃይሎች “በተኩስ አቁም” ወደ ስልጣን ለመመለስ ያልቆፈሩት ድንጋይ የለም። ሆኖም ግን በአውሮፓውያን ድጋፍ ኢትዮጵያን በግፍ የወረረችው ጣሊያን በአባቶቻችን ክፉኛ ተቀጥ ቅጠው ምኞቷ እንደተኮላሸው ሁሉ የአሁኑ ትውልድም አሸባረውን ትህነግ አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወደ ፍርስራሽነት መቀየር ችሏል።

ከልብሳቸው እና ሸሚዛቸው በታች የአውሮፓ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለመግደል ሁሌም ረጅም ቢላ ይዘው ኢትዮጵያን ለመቆራረጥ እየቋመጡ ነው ። ለዚህ ሁሉ ዋነው መነሻ ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያ ቅኝ ገዥ ወራሪዎችን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣቷ የተፈጠረ የበቀል ስሜት ነው ። ኢትዮጵያውያኑ ኃያላን የጣሊያን ጦርን በ 1896 ከ 24 ሰዓታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በአድዋ ጦርነት ድል አደረጉ ። ሁለተኛው የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት ለ 5 ዓመታት የዘለቀ ቢሆንም ጣሊያን እንደገና ተሸነፈች ።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የቀድሞ የአዲስ አበባ ባህል እና ቱሪዘም ቢሮ ኃላፊ አቶ ነብዩ ባዩ በቅርቡ ከአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አውሮፓዊያን ኢትዮጵያውያንን እና ሌሎች አፍሪካውያንን ቅኝ ለመግዛት የተጠቀሙት ዘዴ የተለያየ መሆኑን ይናገራሉ ። ከኢትዮጵያ በስተቀር ያሉ ወንድም አፍሪካውያንን ቅኝ ገዥዎች የቅኝ ገዥዎች ቋንቋ በመጠቀም በአፍሪካ የነበሩ የተለያዩ ጎሳዎችን በመጨፍለቅ እና ማንነታቸውን በማጥፋት የቅኝ ገዥዎችን ቋንቋ በመጠቀም ወደ አንድ ቋንቋ ተናጋሪነት ለውጠዋቸዋል። በኢትዮጵያን ግን የዚህ ተቃራኒ ነው ። በኢትዮጵያ የተለያዩ ጎሳዎች ቢኖሩም በአድዋ ጦርነት ላይ በአንድነት ቆመው ቅኝ ገዥውን ጣሊያን ስላሸነፉ እና የማሻነፋቸው ምክንያት ደግሞ የኢትዮጵያውያን አንድነታቸው ጠንካራ ስለነበር ይህን አንድነት ለመስበር አውሮፓውያን በዩኒቨርሲቲዎቻቸው ሳቀር ኢትዮጵያን ለመበታተን ብቸኛው አማራጭ በብሄር መከፋፈል እንደሆነ አስጠንተዋል።

አልማሪም በትንታኔው እንደገለጸው፣ አስገራሚው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ ር) ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካም አዲስ “የመደመር” ፍልስፍናን ትምህርት እየሰጠ ነው ። ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ነፃ እና ፍትሃዊ የሆነ ምርጫ ይኖራቸዋል ። በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ያለምንም ጥርጥር የአፍሪካ ኮከብ ትሆናለች ። ኢትዮጵያ የምትሄድበት መንገድ ፣ የተቀረው አፍሪካም እንዲሁ! እምቢተኛ ፣ የማይታዘዝ እና ደፋር ስለሚያደርግ እና ኢትዮጵያ በአፍሪካ ለምዕራባውያን ኒኦ ቅኝ አገዛዝ ሥጋት በመሆኗ የምዕራቡ ሴራ- ኢትዮጵያን በፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ አድርገው መቀጠላቸው የማይቀር ነው ። ስለዚህም ከምዕራባውያን ጋር የሚደረገው ግብግብ በኢትዮጵያ ታዛዥና ደካማ መንግሥት ለመፍጠር የሚደረግ የምራባውያን ቅዥት እንደሆነ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊያውቅ ይገባል።

 ሙሉቀን ታደገ

አዲስ ዘመን ሰኔ  11/2013

Exit mobile version