Site icon ETHIO12.COM

በበጀት ዓመቱ ከ7 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ በሰነድ አልተወራረደም

በበጀት ዓመቱ በዘጠና መስሪያ ቤቶችና በአስራ ሁለት የቅርንጫፍ ተቋማት ከ 7.4 ቢሊዮን ብር በላይ በሰነድ ያልተወራረደ መሆኑን የፌደራል ዋና ኦዲተር ይፋ አደረገ። ሪፖርቱ የቀረበለት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተደጋጋሚ የኦዲት ግኝት ችግር በሚከሰትባቸው ተቋማት ላይ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ አሳስቧል።

የፌደራል ዋና ኦዲተር የ2012/13 በጀት ዓመት የኦዲት ሪፓርቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል።ኦዲተር መስሪያ ቤቱ ሪፖርቱን ባቀረበበት ወቅት እንዳንድ ተቋማት በተደጋጋሚ ተመሳሳይ የሃብት አጠቃቀም ችግር እየታየባቸው መሆኑን ገልጿል።

ለአብነትም የ2011 በጀት ዓመት በ68 ተቋማት በተደረገ ኦዲት ተመላሽ መሆን ከነበረበት ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ውስጥ እስካሁን የተመለሰው 261 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑ ተጠቅሷል።ይህም በኦዲት ግኝቱ መመለስ ከነበረበት ገንዘብ ወስጥ 14 ነጥብ 6 በመቶ ብቻ ተመላሽ መሆኑን ያመላክታል።

በ2012 በጀት ዓመት ደግሞ በ90 መስሪያ ቤቶችና በ12 የተለያዩ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች በተደረገ ኦዲት ከ7 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ የሰነድ ሂሳብ ሳይወራረድ መገኘቱም በሪፖርቱ ተገልጿል።

በገቢዎች ሚኒስቴርና በጉምሩክ ኮሚሽን በእያንዳንዳቸው ስር ባሉ ስድስት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች 7 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በወቅቱ ያልተሰበሰበ ውዝፍ ገቢ መገኘቱም እንዲሁ።

የምክር ቤቱ አባላትም ተደጋጋሚ የኦዲት ግኝት የሚከሰትባቸው ተቋማትና የሚታዩት ችግሮች ተመሳሳይነት እንዳላቸው አንስተዋል።ችግሩን ለመቅረፍ ከሪፖርት ባለፈ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ገልጸው፤ ምክር ቤቱ በዚህ ረገድ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንደሚወጣ አስገንዝበዋል።ዝርዝር ዜናውን ለማንበብ ሊንኩን ይጠቀሙ፡-

Exit mobile version