Site icon ETHIO12.COM

አብን ሰዓቱን አይቶ “ትህነግን እንጠንቀቅ፤ ኢትዮጵያም እናስቀድም” አለ

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በሀገራችን ላይ የተደቀነውን ፅኑ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ለመመከትና ከምንም በላይ የቆመለትን የሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት ፣ የህዝብ ጥቅምና ክብር እንዲሁም የሀገረ መንግሥቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚጠበቅበትን ሁሉ ድርጅታዊ አስተዋፅኦ ለማድረግ ቁርጠኝነቱን በአፅንኦት ለመግለፅ ይወዳል፡፡

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን ) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ፣

ለሁሉም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሉች ፤

የኢትዮጵያ ጉዳይ ለሚያሳስባችሁ አፍሪካውያን ወንድሞቻችንና ዓለም አቀፍ አጋሮቻችን ፤

በመላው ዓለም ለምትገኙ ሰላም ወዳድ ኃይሎች በሙሉ !

—————–

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በሰኔ 26 እና 27 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅና ዙሪያ መለስ ውይይት በማድረግና ፤

• የሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ መሰረት ለመጣልና በህዝብ ይሁንታ ብቻ ሥልጣን የሚይዝ ሥርዓት ለመፍጠር የተደረገውን 6ኛውን ሀገራዊ የምርጫ ሂደት በመገምገም ፤

• የታላቁን የአባይ ግድብን በማጠናቀቅና እንደ ሀገር የተፈጥሮ ፀጋችንን ተጠቅመን የመልማት መብታችንን ለማረጋገጥ በተያያዝነው ጥረት ረገድ የተጋረጡብንን ተግዳሮቶች በመገንዘብ፤

• ህዝባችን በሰላምና ደህንነት እጦት ፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝና መረን በለቀቀ የኑሮ ውድነት እየደረሰበት ያለውን ምጣኔ ሀብታዊ ድቀት ግምት ውስጥ በማስገባት ፤

• ከሁሉም በላይ ሀገራችን ከውስጥ በከሃዲያንና እኩያን ኃይሎች ቅንጅት ፣ ከውጭ በታሪካዊ ጠላቶቻችንና ዓለም አቀፍ አጋሮቻቸው አይዞህ ባይነትና ድጋፍ የተደቀነባትን የህልውና ስጋት ተቀዳሚ ትኩረት በመስጠት ፤

የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ የደረሰባቸውን አቋሞች ለተከበረው ህዝባችን ፣ ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችንና በአጠቃላይም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ ይወዳል፡፡

1. 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ በተመለከተ

አብን እንደ ድርጅት የመጀመሪያው አብይ የፖለቲካ ተመክሮው በሆነው በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ውስጥ ለመሳተፍ ሲያቅድ ፣ ገና ከመነሻው ሀገራችን የምትገኝበትን የፖለቲካ አውድ በመገምገም በምርጫው የመሳተፉን ውሳኔ ያደረገው በዋነኝነት ከድርጅታዊ ፋይዳዎች ይልቅ ለሀገራዊ ፖለቲካው መረጋጋትና ለዴሞክራሲያዊ ተመክሮ ግንባታ ከሚኖረው ፋይዳ አንፃር እንደሆነ በይፋ አሳውቋል፡፡

አብን ሀገራዊ ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን የምርጫ ዘመቻውን ስትራቴጂክ ግቦችና ማስፈፀሚያ ስልቶችን በዝርዝር በመንደፍ ፣ አማራጭ ፖሊሲዎቹን በማኒፌስቶ በመሰነድና ሙሉ ድርጅታዊ ኃይሉን በማንቀሳቀስ በምርጫ በሚሳተፍባቸው በአማራና ሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች 510 እጩዎችን በማቅረብ ሰፊውን መራጭ ህዝብ ለመድረስ ያልተቆጠበ ጥረት አድርጓል፡፡

በዚህም መሰረት የምርጫ ዘመቻው ከነተግዳሮቶቹ ተጠናቅቆ ፣ በሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ፓርቲያችን በሚወዳደርባቸው ክልሎች ድምፅ ተሰጥቶና በከፊል ጊዜያዊ ውጤት ተገልጾ በድህረ ምርጫ ሂደት ላይ እንገኛለን፡፡

ፓርቲያችን በመላ ሀገሪቱ በተወዳደረባቸው አካባቢዎች በምርጫው ሂደት የተፈፀሙትን አበይት ጥሰቶች በማሰባሰብና በዝርዝር ቅሬታዎችን በመሰነድ በህግ አግባብ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አቅርቧል፡፡ የምርጫ ቦርድ ከተጣለበት ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት አኳያ ከሰው ፣ ከፋይናንስ ፣ ከተመክሮና ከሎጂስቲክ አቅም ውሱንነት ቢታይበትም በአጠቃላይ ከቅድመ ምርጫው ጀምሮ አንፃራዊ አዎንታዊነት እንዳሳየ እናምናለን፡፡ በቦርዱ የበላይ አመራር የታየው ገለልተኝነት ፣ ግልፅነትና ፍትሃዊነት መንፈስ እንደ ተቋም የሚፈተንበት ወቅት እንደሆነም እንገነዘባለን፡፡

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ህዝባችን ይህንን ሁሉ ጫና ተቋቁሞ በምርጫው ሂደት ውስጥ በመሳተፍ ላሳየው ፅናት ልባዊ አድናቆቱን በመግለፅ፣ የመራጩ ድምፅ እንዲከበር ተገቢውን ሰላማዊና ህጋዊ ጥረት እንደሚያደርግና የህዝባችንንም ሀቀኛ ውሳኔ ያለማወላወል እንደሚቀበል ለማሳወቅ ይወዳል፡፡

በሌላ በኩል 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሥርዓቱን እውነተኛ ባህሪ በተግባር መፈተንና ማጋለጥ መቻሉን ትልቁ ውጤት አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡ በምርጫው ሂደት የታየው ጎዶሎነትና ክፍተት ከምርጫ ውጤት አኳያ የምንመዝነው ከሆነ የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታና የሃሳብ ብዝሃነት የማያመለክት መሆኑን መናገር ይቻላል፡፡

አብን እንደ ድርጅት በምርጫ በመሳተፉ ምን አገኘ ፣ አሳካ የሚለውን ስንገመግም አንዳንድ ተስፋ ሰጭ ነገሮች እንዳሉ መካድ አይቻልም፡፡ ከሁሉም በላይ የህዝባችን እውነተኛ ወኪል ስለመሆናችን ህዝባችን የነበሩትን ጫናዎች ተቋቁሞ በሰጠን የመተማመኛ ድምፅ በቂ ማረጋገጫ አግኝተናል፡፡ ይህም የመጪው ዘመን ፓርቲ መሆናችንን ይመሰክራል፡፡ በሐገር አቀፍ ድረጃ በተሻለ ህዝብን የማስተባበር አቅም እንዳለንና ጠንካራ ተገዳዳሪ የፖለቲካ ኃይል መሆናችንን በማያሻማ ሁኔታ አረጋግጠናል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የምርጫው ሂደት አጠቃላይ ድርጅታዊ ቁመናውን የሚፈትሽበት መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ይገነዘባል፡፡ በቀጣይም ከሂደቱ ያገኛቸውን ተመክሮዎችና ትምህርቶች በማካተትና ሁለገብ የማሻሻያ እርምጃዎች በመውሰድ ለብሔራዊ ፖለቲካችን ሁነኛ ሚና መጫወቱን እንደሚቀጥል አያጠራጥርም፡፡

2. ብሔራዊ ደህንነትን በተመለከተ

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በተለይ በሀገር ሉዓላዊነትና አንድነት ፣ በህዝብ ጥቅምና ክብር ፣ በሀገረ መንግሥቱ ቀጣይነት ረገድ ግልፅና የማያሻማ አቋም ያራምዳል፡፡ በገዥው ፓርቲ ግልፅ ፍረጃ ፣ ወከባና ጥቃት እየደረሰበትም ቢሆን የፖለቲካ ማዕከሉ እንዲረጋጋና በአፍሪካ ረዥሙንና ደም አፋሳሹን የእርስ በርስ ጦርነት ያደረገች ሀገር ተመልሳ ወደ ቀውስ እንዳትገባ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

አብን ወቅታዊው የሀገራችን ብሔራዊ ደህንነት ከጊዜ ጊዜ እየከፋና እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ይገነዘባል፡፡ የውጭ ወራሪዎችና የውስጥ ቦርቧሪዎች ከተቻለ ኢትዮጵያን ለየዘውጉ አምበሎች በታትኖ ከዓለም ካርታ ለማጥፋት ፤ ካልሆነ ደግሞ ውስጣዊ አንድነት የሌላት ፣ ደካማና ፍላጎታቸውን ያለማንገራገር የምትቀበል አድርገው ለማሽመድመድ እየተረባረቡ ይገኛሉ፡፡

ከዚህ አንፃር የብልጽግና አገዛዝ የሀገሪቱን ፣ የዜጎችና የመንግሥቱን ሰላምና ደህንነት ፣ ጥቅምና ክብር በማስጠበቅ ረገድ ጉልህ ክፍተቶች እየተስተዋለበት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ባደረገው ከፍተኛ ተጋድሎ ከአፈናና ጭቆና መንበሩ የተባረረውና በሀገር መከላከያ ሠራዊት ፣ በአማራ እና አፋር ልዩ ኃይልና ህዝባዊ ሚሊሺያ ድባቅ የተመታው የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ግንባር (ትህነግ) ተመልሶ በማንሰራራት በብሔራዊ ደህንነታችን ላይ ተቀዳሚ አደጋ ሊሆን በቅቷል፡፡

አብን ማዕከላዊ መንግሥትና በየደረጃው ያሉ መንግሥታዊ አካላት ሀገሪቱ ከተደቀነባት የህልውና አደጋ ለመታደግ በሚደረገው ርብርብ የራሳቸውን ሚና በግልፅ ከመወሰን አንስቶ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተተ የብሔራዊ ደህንነት እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ ያቀርባል፡፡

መንግሥት ልዩ የደህንነት ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ፤ በተለይም አሸባሪው የትህነግ ቡድን መልሶ በተቆጣጠረው በትግራይ የተማሪዎችንና የሲቪል ዜጎችን፤ በአጠቃላይም የትግራይን ህዝብ ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ይጠይቃል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ሁኔታ አብንን በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡ የትግራይ ህዝብ በመካከሉ ለሚገኙ ተማሪ ልጆቹ አስፈላጊውን ጥበቃና ክብካቤ እንዲያደርግ ጥሪ እናደርጋለን፡፡

አብን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ፣ ሀገር ወዳድ ዜጎችና በተለይም ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ሀገራችን ስለገጠማት የብሔራዊ ደህንነት አደጋ ግልፅ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ኢትዮጵያን ለመታደግ በአንድነት እንዲሰለፉ ጥሪ ያደርጋል፡፡

በወታደራዊ ኃይል የሚገኘው ድል ዳግም በዲፕሎማሲው አውድማ እንዳይነጠቅ መላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸው አምባሳደር በመሆን በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ትግል እንዲሳተፉ ጥሪ ያቀርባል፡፡

በተለይም ደግሞ በፀረ – ኢትዮጵያው ጎራ በጠላትነት ተፈርጆ ዘርፈ ብዙ ጥቃት የተሰነዘረበት የአማራ ህዝብ የሚገኝበትን ወቅታዊ የስጋት ደረጃ በውል ተገንዝቦ የበኩሉን ጥንቃቄና ዝግጅት እንዲያደርግ፣ የአማራ ዲያስፖራ በህዝባችንና በሀገራችን ላይ የተቃጣውን አደጋ ለመቀልበስ ሁለገብ የሃሳብ ፣ የፋይናንስ ፣ የዲፕሎማሲ ተሳትፎውን አጠንክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ያቀርባል፡፡

አብን አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ፣ መላው የኢትዮጵያ ወዳጆችና አጋሮች የጥንታዊ ሥልጣኔ ፣ አኩሪ የነፃነት ታሪክ ያላት ሀገር በእኩያን ኃይሎች የተከፈተባትን ወታደራዊ ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥቃት ለመመከት ከጎናችን እንዲሰለፉ ጥሪ ያደርጋል፡፡ በዚህ ረገድ በአካባቢው ጉዳይ ትኩረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት በአፍራሽ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እንዳይደለሉና የችግሩን ዙሪያ ገብ በፍትሃዊነት በመገምገም እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ያቀርባል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በሀገራችን ላይ የተደቀነውን ፅኑ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ለመመከትና ከምንም በላይ የቆመለትን የሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት ፣ የህዝብ ጥቅምና ክብር እንዲሁም የሀገረ መንግሥቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚጠበቅበትን ሁሉ ድርጅታዊ አስተዋፅኦ ለማድረግ ቁርጠኝነቱን በአፅንኦት ለመግለፅ ይወዳል፡፡

አዲስ አበባ ፣ ሸዋ ፣ ኢትዮጵያ

ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም

Exit mobile version