Site icon ETHIO12.COM

40 ዕርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ አቀኑ፤ አውሮፕላን ቅድሚያ አዲስ አበባ ሳያርፍ ወደ መቀለ አይበርም

በትግራይ ክልል ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች አስፈላጊውን ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረግ መንግስት በሰጠው ትኩረት መሰረት ምግብና ምግብ ነክ ድጋፎችን የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ዛሬ ወደ ክልሉ መንቀሳቀስ ጀምረዋል። ለርዳታ ተግባር ወደ መቀለ መጓዝ የሚፈልጉም ሆነ ከመቀለ የሚወጥ ቀድመው አዲስ አበባ ማረፍ እንዳለባቸው መንግስት ደንብ አወጣ።

ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እርዳታ እንዲያቀርቡ መንግስት ባደረገው ጥሪ መሰረት ከአርባ የሚበልጡ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ከሰመራ ከተማ ሰብዓዊ እርዳታ ጭነው ወጥተዋል።በዓለም የምግብ ፕሮግራም አማካኝነት ወደ ትግራይ የተላከው የምግብ እህል፣ አልሚ ምግቦችና የተለያዩ የመገልገያ ቁሳቁሶች በክልሉ በተከሰተው ችግር ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚከፋፈል መሆኑም ታውቋል።

በሌላ የትግራይ ነክ ዜና የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ትግራይ፣ እንዲሁም ከትግራይ ወደ ውጭም ሆነ ወደ አገር ውስጥ አየር ማረፊያዎች የሚደረጉ ሁሉም በረራዎች አስቀድመው ቦሌ አየር ማረፊያ ማረፍ እንዳለባቸው ወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ ገልጿል፡፡በነዚህ አውሮፕላኖች ላይ አስፈላጊ ፍተሻ እንደሚደረግም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል ተኩስ ማቆም ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ ድጋፍ ሰጪ አካላት ጋር በቅርበት ለመስራት ፍላጎት እንዳለው በድጋሜ አስታውቋል፡፡

ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ከሰኔ 23 ቀን 2013 ጀምሮ የሰሜን የአየር ክልል ከ290 በታች የበረራ ደረጃ ዝግ ቢያደርግም ከሰኔ 25 ቀን 2013 ጀምሮ በትግራይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት ላላቸው አካላት ልዩ የበረራ ፍቃድ መስጠቱ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ ረገድ ምንም ዓይነት በረራ ያልከለከለ መሆኑንና ትናንት የዓለም የምግብ ፕሮግራም በሁለት አውሮፕላኖች ወደ ትግራይ በረራ ለማድረግ ጥያቄ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡የበረራውን ሁኔታ ለማቀላጠፍ ወደ ትግራይ በረራ ማድረግ የሚፈልጉ አካላት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው አካላት ፍቃድ ማግኘት እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡ ወደ ትግራይ የሚደረጉ በረራዎች ላይ መስተጓጎል መንግስት ችግር እንደፈጠረ ተደርጎ የሚቀርቡ ሪፖርቶች ትክክል አለመሆናቸውን ተገልጿል። via – ENA


Exit mobile version