Site icon ETHIO12.COM

የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮ-ጅቡቲ የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት መስመር ዝርጋታ የ83.6 ሚሊዮን ዶላር ብድር አጸደቀ

የአፍሪካ ልማት ባንክ ለሁለተኛው የኢትዮ-ጅቡቲ የኤሌክትሪክ ሀይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት የ83.6 ሚሊዮን ዶላር ብድር ማጽደቁን አስታወቀ።

የአፍሪካ ልማት ባንክ በኢትዮ-ጅቡቲ ድንበር አካባቢ ለሚገነባው የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት መስመር ዝርጋታ የሚውሉ በረጅም ጊዜ የሚከፈሉ ሁለት ብድሮችን ማጽደቁን ይፋ አድርጓል።

ባንኩ ካጸደቃቸው ሁለት ብድሮች መካከል 69.65 ሚሊዮን ዶላሩ ለኢትዮጵያ እንዲሁም 13.93 ሚሊዮን ዶላሩ ለጅቡቲ የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል።

ይህ የአፍሪካ ልማት ባንክ ብድር የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናን በሀይል በማስተሳሰር የአካባቢውን መሰረተ-ልማት በማስተሳሰር ኢኮኖሚያዊ ሽግግር እንደሚያመጣ እንደሆነም ነው የተገለፀው።

ባንኩ ይህን ሁለተኛ ዙር የብድር ድጋፍ ማድረግ የቻለው እኤአ በ2004 ለመጀመሪያው ዙር የሀይል መስመር ዝርጋታ የሰጠው በረዥም ጊዜ የሚከፈል ብድር አጥጋቢ ውጤት በማስገኘቱ እንደሆነ ገልጿል።

ይህ ሁለተኛው ዙር የሀይል አቅርቦት መስመር ዝርጋታ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ ከኤሌክትሪክ ሀይል ሽያጭ የምታገኘው ገቢ የሚያሳድግ ሲሆን ጅቡቲም አንድ ኪሎ ዋት በሰዓት ከ10 የአሜሪካ ዶላር በታች በሆነ ዋጋ እንድታገኝ የሚያስችላት ነው ተብሏል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

Exit mobile version