Site icon ETHIO12.COM

“እያለቀስኩ ነው … ባሌን በብርሃን ፍጥነት ነው የገደሉት”

በቅርቡ የተገደሉት የሃይቲ ፕሬዝደንት ባለቤት ገዳዮች ወደቤታቸው መጥተው ባላቸውን በእኩለ ለሊት ሲገድሉባቸው የነበረውን ሁኔታ ተናግረዋል።

ማርቲን ሞይዝ እንዳሉት ጥቃቱ በጣም በፍጥነት የተፈፀመ ከመሆኑ የተነሳ ባላቸው ጆቨኔል “አንድም ቃል መተንፈስ” አልቻሉም። ፕሬዝደንት ሞይዝ ባፈለው ረቡዕ ነው የተገደሉት። ገዳዮች ተብለው የተጠረጠሩት ደግሞ 28 የውጭ ሃገር ዜጎች ናቸው።

ሚስታቸው ማርቲን ሞይዝ ተጎድተው በአሜሪካዋ ከተማ ማያሚ ሕክምና ሲያገኙ ቆይተው አሁን አገግመዋል። ቅዳሜ ዕለት በትዊተር ገፃቸው ባስተላለፉት የድምፅ መልዕክት የባላቸውን ሥራ ለመጨረስ ቃል ገብተዋል።

“ከብርሃን በፈጠነ ጊዜ ሰርጎ ገቦች ወደ ቤታቸውን ዘልቀው ባሌን በጥይት ገድለውታል” ብለዋል በድምፅ መልዕክታቸው። “ይህ ድርጊት ስም የለውም። ምክንያቱም ጆቨኔል ሞይዝን የመሰለ ፕሬዝደንትን አንድም ቃል ሳይተነፍስ ለመግደል አጥር አልባ ወንጀለኛ መሆን አለብህ።”

ማርቲን ባላቸው የተገደለው በፓለቲካዊ ምክንያት እንደሆነ ይገምታሉ። በተለይ ደግሞ ለፕሬዝደንቱ የተሻለ ሥልጣን የሚሰጣቸው የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ለማድረግ ማሰባቸውን ተከትሎ ነው። እኒህ ስም የሌላቸው ገዳዮች “የፕሬዝደንቱን ሕልም መግደል ነው የሻቱት” ይላሉ።

“አዎ እያለቀስኩ ነው። ነገር ግን ሃገራችን መንገዷን እንድትስት መፍቀድ የለብንም። የፕሬዝደንት ጆቨኔል ሞይዝ፣ ባሌ፣ የምንወደው ፕሬዝደንታችን ደም በከንቱ እንዲፈስ መፍቀድ የለብንም።”

የ53 ዓመቱ ሞይዝ በደቡብ፣ ሰሜንና መካከለኛው አሜሪካ ካሉ ሃገራት ድህንት አቆራምዷታል የምትባለውን ሃይቲን ለአራት ዓመታት መርተዋል። የሥልጣን ዘመናቸው ወጣ ገባ ነበር። በሙስናና ብልሹ አስተዳደር ምክንያት በርካታ ተቃውሞ ተነስቶባቸው ያውቃል። ከሁለት ዓመት በፊት የሕዝብ ተወካዮች ምርጫ ማከናወን የነበረባት ሃይቲ ባለመግባባት ምክንያት አራዝማዋለች።

በሚቀጥለው መስከረም የሕገ መንግሥት ማሻሻያ እንዲደረግ ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ አቅደው ነበር የተገደሉት ፕሬዝደንት። ባለፈው የካቲት ፕሬዝደንቱ እሳቸውን ሊገሏቸው ያሰቡ ሰዎች ሐሳብ መክሸፉን ተናግረው ነበር። የገዳዮቹ ዓላማ ምንድነው? እንዴትስ የፕሬዝደንቱን ጥበቃዎች ዘልቀው ገቡ የሚሉት ጥያቄዎች እስካሁን አልተመለሱም።

የሃይቲ ፖሊስ አብዛኛዎቹ የገዳዩ ቡድን አባላት ኮሎምቢያዊያን ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ አሜሪካዊያን ናቸው ብሏል። 17 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ፤ ሶስት ሰዎች ከፖሊስ ጋር በነበረ የተኩስ ልውውጥ ተገድለዋል፤ ስምንት ተጠርጣሪዎች ደግሞ እየታሰሱ ነው። ዘገባው የቢቢሲ ነው


Exit mobile version