Site icon ETHIO12.COM

“ለሠማዕታት ቤተሰቦች – ቤት ፣ ለልጆቻቸው የትምህርት ዕድል እንሰጣለን !” – የአዲስ አበባ ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ ።

ሐምሌ 5 ቀን 2013

የሐምሌ 4 ቀን 2013 እሁድ በመገናኛ አካባቢ የወትሮ አልነበረም።በሺዎች የሚቆጠሩ ከሁሉም የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ወጣቶች በየካ ክፍለ ከተማ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እየገቡ ታድመዋል ።

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል ሀላፊ መለስ ዓለም ከፍተኛ የመስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ሐላፊዎችና የካቢኔ አባላት ወደ አዳራሽ ዘለቁ።ቀደም ብለው ሥፍራ ይዘው በነበሩ የአርበኞች ማህበር አባላት የተለያዩ ፣ የህብረተሰብ ክፍሎችና ወጣቶች ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው።አደራሹ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችንን በሚያወድሱ መፈክሮች ደምቋል።

በዚህ መሃል የኢፌዴሪ መከላከያ የግንባታ ሥራዎች ዋና አስተባባሪ ሌ/ጄኔራል ባጫ ደበሌ ፣ የኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ ብ/ጄኔራል አስፋው ማመጫ ፣ የመከላከያ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮ/ል ጌትነት አዳነ ሌሎች ከፍተኛ መኮንኖችን አስከትለው ወደ አደራሹ ገቡ።

ሠማይና ምድርን የሚያደባላልቅ ጭብጫባና ፉጨት የሠራዊቱ አመራሮች ከተቀመጡም በኋላ ለደቂቃዎች ቀጠለ። የኘሮግራሙ ዓላማ “ክብር ለሀገር አንድነትና አብሮነት ለተሰው የመከላከያ ሠራዊት አባለት” በሚል መሪ ቃል ከአዲስ አበበ ወጣቶች ጋር በየካ ክፍለ ከተማ ውይይት ለማካሄድ ነበር።

ምክትል ከንቲባ አደነች አቤቤ የኘሮግራሙን አላማ አብራሩ ።ሀገራችን በቅርብ ለተጎናፀፈቻቸው ሦስት ወሣኝ ድሎች የከተማዋ ወጣቶች ላበረከቱት አስተዋፅኦ ለተጫወቱት ሚና አመሠገኑ።የመከላከያ ሠራዊታችንን ሀገራዊ ውለታ በሚገርም ሁኔታ ተነተኑ።

ዕለቱ የምስጋና ብቻ ሳይሆን የአዲስ አበባ ወጣት ከሞራልና ገንዘብ ድጋፍ ባለፈ ከሠራዊቱ ጎን ተሰልፎ ሀገራዊ ሐላፊነቱን መወጣት እንዳለበት በታላቅ የሀገር ፍቅር ስሜት አስገነዘቡ።ከፍተኛ ጭብጨባ ፉጨት አቋርጧቸው ቀጠሉ።

ከሃዲው ሐይል ትርጉም ባለው ደረጃ ስጋት በማይሆንበት ሁኔታ በመከላከያ ሠራዊታችን መመታቱም ሌላው ድል መሆኑን አብራሩ።ዓመቱ ህብረትና አንድነት ያለውን ጉልበት፣ የሚያመጣውን የማይታጠፍ ስኬት ተናገሩ።ለድሉ መገኘት የከተማው አስተዳደር ወጣቱን ጨምሮ ያደረገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አበሰሩ።ድጋፉ በሰብአዊ ሐይል ጭምር መሆን ይኖርበታል አሉ።

ቀጣዩ ተናጋሪ የመከላከያ ግንባታ ሥራዎች ዋና አስተባባሪ ሌ/ጄኔራል ባጫ ደበሌ ነበሩ።የወጣቱ አቀባበል ሞራልና ስሜት ለዚህ ወገን ደግሜ ደጋግሜ በሞትኩ የሚያሰኝ ነበር።ስሜትን ሰቅዞ ይይዛል።

እናም ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ ሠራዊቱ በትግራይ ክልል የተሰጠውን ተልዕኮ በሚያኮራ መልኩ መፈፀሙን፣ በመንግስት ውሳኔ ለቆ የወጣው ለቀጣይ ዝግጁነት እንዲያመቸው መሆኑንና ጁንታው ከአሁን በኋላ የሀገር ስጋት መሆን እንደማይችል አስረዱ።

ሌላው አቅሙን አሟጦ ወደ ሽምቅ ተዋጊነት የተሸጋገረው ርዝራዥ ህዝቡን እያደናገረ አሊያም እያስገደደ ከሠራዊቱ ጋር ለማጋጨት በመሞከሩ ህዝብ ላይ ላለመተኮስ ጭምር እንደሆነ አስከተሉ።ለህዝብ መሞት እንጂ መግደል ባህሉ ባለመሆኑ ውሳኔው ተጨማሪ ድል ነው አሉ።

ማብራሪያዎቻቸው በርካታ ብዥታን የሚያጠሩ ፣ግልፀኝነትን የሚፈጥሩ የጁንታውን የሐሰት ኘሮፓጋንዳ የሚያጋልጡና የሚቀብሩ ነበሩ።ሠራዊቱን ከጀርባ ወግቶ፣ ጦር አደራጅቶ፣ ለምስራቅ አፍሪካ ጭምር እበቃለሁ ሲል የነበረ ሐይል ሁሉን አጥቶ ተበታትኖ ሲያበቃ እንዴት ሊያሸንፍ ይችላል? ሲሉ ጠየቁ።

በማህበራዊ ሚዲያ ጁንታው የሚያናፍሰው የሐሰት ኘሮፓጋንዳ ከባህሪው የሚመነጭ መሆኑን አስረገጡ።ይሄን ሐሳብ በሐሰት ተፀንሶ በውሸት ጎልምሶ መቃብሩ ውስጥም ሆኖ እየዋሸ የሚገኝ በሚል ገለፁ።

እሳቸው እንዳረጋገጡት ጁንታው ከአሁን ወዲያ የሀገራችን የደህንነት ሥጋት አይደለም።መቀሌም ከሌሎቹ የትግራይ ከተሞች የተሻለ ወታደራዊ ጠቀሜታ የላትም።ለረጅም ጊዜ ቀን ለሊት ለስምንት ወራት በግዳጅ ሲንከራተት የነበረው ሠራዊት ይደራጃል።አጋጣሚውን ወደ ላቀ ብቃት ለመስፈንጠር ይጠቀምበታል።

ወጣቱ ፣ ሌ/ጄኔራል ባጫ ላነሱት የተቋሙ ፍላጎት በከፍተኛ ጭብጨባ ድጋፉንና ዝግጁነቱን ገለፀ።ሐሳብ የኢትዮጵያዊነት ማሳያ አብነት ፣ የመላው ሀገራችን ህዝቦች መልክና ስነልቦና ባለቤት የሆነው የአዲስ አበባ ወጣትን በተቋሙ ውስጥ በብዛት የማየትን ፍላጎት የተገለፀበት ነበር።

ቀጣዩ የወጣቶቹ ተራ ነው።አስተያየት እና ጥያቄ ።ከተነሱት ሐሳቦች ውስጥ ጥቂቱን ማንሳት ወደናል።ከሠራዊታችን ጎን ተሰልፈን ሀገራችንን ለማገልገል ዝግጁ ነን።ዕድሉን በማግኘታችን ኩራት ይሰማናል።

እንደ ወጣት ሰሞኑን በተገኙ ሀገራዊ ድሎችና መከላከያ ለሀገር በዋለው ውለታ ኩራት ተሰምቶናል።እኛ ወጣቶች ለሀገራችን ሠላም ግንባር ቀደም ሆነን መሰለፍ ይጠበቅብናል። ትላንት ከመከላከያ ጎን ነበርን ።ነገም ከጎኑ መሆናችንን እንቀጥላለን።ነገር ግን ደሙን የለገሰንን፣ ህይወት የከፈልንን ፣አካሉን ያጎደለልንን ሁለንተናውን የሰጠንን ወታደር ውለታ መመለስ እንደማይችል እናውቃለን።

እኛ በሀገሩ ቀርቶ በባዕዳን ምድር ለጠላት ያልተንበረከከው የአብዲሣ፣ የአሉላ አባነጋ፣ የበላይ ዘለቀ ፣የዑመር ሰመተር እና እልፍ አእላፍ ጀግኖች ልጆች ነን።ነፃነት ኩራታችን ሽንፈት እንደ አባቶቻችን እርማችን ነው።ታሪክ ለማስቀጠል ሀገራችንን ከየትኛውም ጠላት ለመከላከል በማንኛውም መንገድ ዝግጁዎች ነን።

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ለከተማችን ዕድገት ሌት ተቀን በመልፋትዎ ፣ተጨባጭ ውጤት በማምጣትዎ እንዲሁም ለመከላከያ ሠራዊታችን ላደረጉት ድጋፍ ይሄንንም መድረክ እንዲፈጠር ስላደረጉ በመላው የአዲስ አበባ ወጣት ስም እናመሠግናለን የሚሉ እና የመሣሠሉት ነበሩ።

አባት አርበኞችም ወጣቶች ሀገር ተረክበው ነፃነቱን እንዲያስቀጥሉ፤ በዕድገትና በሠላም መሠረት እንዲጥሉ አሳሰቡ።በፉከራ፣ ቀረርቶና ሽለላ የወጣቱን ስሜት አነቃቁ።

ከተነሱት ጥያቄዎች ውስጥ ለመከላከያ ሠራዊት አባላት ቤትና ቦታ ለምን አይሰጥም? ጁንታው ተመልሶ የሀገር ስጋት የሚሆንበት ዕድል አለ ወይ?የሚሉት ዋንኞቹ ነበሩ።

ሌተና ጄኔራል ባጫ ሠራዊታችን አሁንም በሙሉ ጥንካሬው ላይ ይገኛል።ጁንታውን ሥጋት በማይሆንበት ሁኔታ ድል ነስተን ለሌላ ሥጋት እየተዘጋጀን እንገኛለን።ምንም ዓይነት መሣሪያ በማያገኝበት ሁኔታ ቦታ ይዘን ህዝቡ እኩይነቱን ተረድቶ እስኪተፋው እየጠበቅን ነው።በማለት ምላሽ ሰጡ።

ቀጥሎ ምክትል ከንቲባዋ የተናገሩት አንዳንድ የሠራዊቱ አመራሮችን ያስነባ ፣ ወጣቶችን ያስፈነደቀ ጉዳይ ነበር።በህግ ማስከበር ዘመቻው ለሀገራቸው ህልውና ህይወታቸውን ላጡ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ቤት ይሰጣል።ልጆቻቸውም ያለምንም ችግር ይማራሉ አሉ።

ጀግናዬ መስዋዕትህ ፍሬ አፍርቷል።ሀገርህን ከውድቀት ታድጓል።አዲስ አበባ ደግሞ ለአዛዦችህ ባህላዊውን ጦር እና ጋሻ ሸልማለች ፤ ውለታህን ቆጥራ ለቤተሰቦችህ ቤተሰብ ሆናለች ፤ ወጣቶቿም ፈለግህን ተከትለው ዓርማህን ለማንሳት ወስናለችና አፈሩ ይቅለልህ በመንፈስ ደስ ይበልህ እንላለን።

ፈይሳ ናኔቻ
ፎቶግራፍ Addis Ababa City Press Secretary Office

Exit mobile version