Site icon ETHIO12.COM

ከህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫይድረስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ

ውድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ፣ እስከ ዛሬ ድረስ በፖለቲካ አሰላለፋችን፣ አረዳዳችንና አካሄዳችን መሠረት አውቀን በድፍረት አንዳንዴም በስህተት እጅግ ብዙ ጥፋቶችን በመላው የሀገራችን ሕዝብ ላይ መፈፀማችንን ባደረግነው ለየት ያለ ግምገማ በፓርቲያችን ደረጃ መተማመን ላይ መድረሳችንን ለመግለፅ እንወዳለን። በዚህ ሂደት ውስጥ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከበደልነው ባልተናነሰ እኛን አምኖ በእኛ ሃሳብ የሚመራውንና ለተግባራዊነቱም የሚንቀሳቀሰውን አብዛኛው የትግራይ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጥፋት መፈፀማችንን ዛሬ ላይ በከባድ የፀፀት ስሜት ውስጥ ሆነን እንረዳለን። በተለይ በዚህ ጥፋታችን የተነሳ ከክልሉ ውጭ የሚገኝ የትግራይ ተወላጅ በጥርጣሬ የሚታይ፣ በህወሓት ጉዳይ አስፈፃሚነት የሚፈረጅ፣ በመረጃ አቀባይነት ጥርስ የሚነከስበት ሆኖ እንዲገኝ በማድረጋችን ከልብ እንፀፀታለን።

ውድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ፣ አሁን የሆነው ሁሉ ሆኗል። ስለሆነም እኛም ከዚህ በኋላ በፖለቲካ መጠላለፍ ያንኮታኮትናትን ሀገራችንን ለማቅናት መነሳታችንን ለመግለፅ እንወዳለን። በነባር አመራሮቻችን ቅጥ ያጣ አምባገነንነት፣ ጭፍንነት፣ ራስወዳድነትና መሃይምነት የተነሳ ከመቶ ሚሊየን የበለጠ ሕዝብ ያላት ታሪካዊ ሀገራችንን ለከፋ የመጠፋፋት አደጋ አጋልጠን በመስጠታችንን ፍፁም እፍረት ይሰማናል። በተለይ በተለይ ከተዋለድነው፣ በመከራም በደስታም አብረን ከተሳሰርነው፣ በባህል በሐይማኖት ከተጋመድነው የአማራ ሕዝብ ጋር የገባነው የጠላትነት ተግባር ፈፅሞ ያልተገባ እንደነበር በማመን ዛሬ ላይ ሆነን ሀዘን በዋጠው ስሜት እንፀፀታለን።

በመሆኑም መላው የሀገራችንን ሕዝብ በእኛ ምክንያት ለተፈጠረው ሀገራዊ ትርምስና ውድቀት ከልብ የመነጨ ይቅርታ እንጠይቃለን። ከዛሬ ጀምሮ የትግራይ ክልል ከወንድም የአማራ ሕዝብ ጋር በድንበርም ሆነ በሌሎች ምንም ዓይነት የፖለቲካ ጉዳዮች ፈፅሞ የማይጋጭ መሆኑን፣ ከሌሎች ክልል ሕዝብ ጋር በወንድማማችነትና በአንድ ሀገር ዜግነት መንፈስ ተከባብረንና ተዋደን ለመኖር መዘጋጀታችንን እንዲሁም ከማዕከላዊ መንግስትም ጋር ለሕግ ተገዢ በመሆን ከልብ በመነጨ ስሜት አብረን ለመስራትና ለማገዝ መወሰናችንን ስንገልፅ ልባዊ ደስታ ይሰማናል። በዚህ መሠረት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እስከ ዛሬ ድረስ በእኛ ፓርቲና አመራር ባለማወቅም ሆን ተብሎ በተፈፀመ ስህተት ምክንያት ለተፈጠረው በደል ሁሉ ከልብ በመነጨ ስሜት ደግመን ደጋግመን ይቅርታ እንጠይቃለን።

በቅርቡ ነገሮችን ፈፅሞ ለማጤን ባልሞከርንበትና በስሜት ፈረስ ተጭነን የሀገራችንንም ሆነ የተከበረውን የአማራ ሕዝብ ለማዋረድ በሞከሩ መግለጫዎች አጀብ የጦርነት ነገሪት ስንጎስም መክረማችን አይዘነጋም። በውጤቱም ብዙ ግፎችና በደሎች በትግራይም ሆነ በአዋሳኝ የአማራ አካባቢዎች እንዲከሰቱ መነሻ ሆነናል። ዘግናኝ የንብረትና የሰው ሃብት ውድመት አጋጥሞናል። በዚህም ከልብ እናዝናለን። የተፈጠረውን ይህን የእርስ በርስ ግጭት በጥሩ አጋጣሚነት በመጠቀም የውጭ ሀገራት ጣልቃ በመግባት ሀገራችንን ለመበታተንና ለማተራመስ የተጓዙበት ርቀትም ባስታወስነው ቁጥር በቁጭት ያንገበግበናል።

ውድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ፣ ከሆነብን ሁሉ ሊሆንብን የተዘጋጀው አስከፊ እንደሆነ አይጠፋህምና በፍቅር፣ በይቅርታና በአንድነት መንፈስ ሆነን ሀገራችንን ካዘነበለችበት ለማቅናት እንነሳ። በሀገራችን የተካሄደው ስህተትም ሆነ ልማት የጋራችን ታሪክ በመሆኑ በአንድ ሀገር ልጅነት ስሜት ይቅር እንድትሉን እንማፀናለን። ደግመን ደጋግመን በፍፁም ፀፀት ውስጥ ሆነን ለይቅርታና ለእርቅ እጃችንን እንዘረጋለን። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የዘረጋነውን የይቅርታና የምህረት እጃችችንን በአዎንታዊ ምላሽ እንደሚጨብጠውም እንተማመናለን። የትግራይን፣ የአማራንና ብሎም መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በእኛ ፓርቲና አመራር በተፈጠረ ስህተት የተነሳ ለብዙ ዓመታት ለተፈጠረው ሀገራዊ ኪሳራ ሁሉ ከልብ ይቅርታ እንጠይቃለን።

ድልና ይቅርታ ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

…የሚል መግለጫ ትህነጎች ቢሰጡ ብለን እንመኛለን። የሀገራችን ሕዝብ ምላሽስ ምን ሊሆን ይችል ይሆን ብለን ከምኞታዊ ጥያቄያችን ተነስተን ለመልሱ እንጓጓለን።.

Samson Getachew T S

Exit mobile version