አሸባሪው ሕወሓት በወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት ሕዝብ ላይ ላለፉት አርባ ዓመታት በፈፀመው ስልታዊና የተቀናጀ የዘር ማፅዳት ወንጀል ከእያንዳንዱ ቤተሰብ 29 ከመቶ ለህልፈት፣ 26 ነጥብ 5 ከመቶ ለስደት መብቃቱንና 19ነጥብ 5 ከመቶ ደግሞ የት እንደገባ እስካሁን እንደማይታወቅ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጥናት አመላክቷል። 12 የጅምላ መቃብር ቀጠናዎች መገኘታቸውንም አስታውቋል። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም ይህን መነሻ በማድረግ ጉዳዩን ከምንጩ ለማጣራት የጋዜጠኛ ቡድን ወደስፍራው ልኳል።
የጋዜጠኞቹ ቡድን ጅምላ ጭፍጨፋ ተፈፅሞባቸዋል ከተባሉ ስፍራዎች ውስጥ በወልቃይት ወረዳ ደጀና የተባለ ስፍራ በመገኘትም የአካባቢውን ማኅበረሰብ፣ የአስተዳደር አካላት፣ የዓይን ምስክሮች እንዲሁም የተጎጂ ቤተሰቦችን አነጋግሯል። አሸባሪው ሕወሓት በግፍ ከጨፈጨፋቸው የአካባቢው ተወላጆች መካከል ማሳያ የሚሆነውን በአባ ልጃለምና ቤተሰባቸው ላይ የደረሰውን ግፍና የዘር ማጥፋት ተግባር አንዱ ነው።
አባ ልጃለም ታዬ ማናቸው?

አባ ልጃለም ታዬ ትውልዳቸውም ሆነ እድገታቸው በወልቃይት ወረዳ ደጀና አካባቢ ነው። አባ ልጃለም በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ የሚከበሩ እና የሚወደዱ ሰው ሲሆኑ የታሪክ አዋቂም ናቸው። ስለእውነት ከመናገር የማያቅማሙ የመርህ ሰውም ናቸው። በዚህ የተነሳ የአካባቢው ነዋሪ ሁሉ ለቃላቸው ይገዛል፤ ተምሳሌትነታቸውንም ይከተላል።
እንደ አካባቢው ነዋሪዎች ገለጻ ታታሪ አርሶ አደርነታቸው ከአካባቢው ለምነት ጋር ተዳምሮ ጥሩ ሀብትና ንብረት እንዲያፈሩም አስችሏቸዋል። የተከሏቸው ዛፎች ጭምር «የነአባ ልጃለም ሰፈር» የሚል ስያሜን አሰጥቷቸዋል። ግቢአቸውና ደጃፋቸው በእንክብካቤ የተያዘ በመሆኑም ወደ መኖሪያ ቀዬአቸው ሲደረስ የምድር ገነትን የጎበኙ እስኪመስል ድረስ ሀሴትን ያጎናጽፋል። ልጆቻቸውም ቢሆኑ ገና ከለጋ ዕድሜአቸው ጀምሮ በሥራ ትጋትና በመልካም ሥነምግባር ያደጉ በመሆኑ ቤተሰቡ ሁሉ ደስተኛ ኑሮ ይኖራል።
የአካባቢው ማኅበረሰብ በችግሩም ሆነ በደስታው ጊዜ የአባ ልጃለምን ሃሳብ መፈለጉ የተለመደ ነው። በአካባቢው ግጭቶች ሲከሰቱ በማስታረቁ ረገድ ትልቅ ሚና ያላቸው እሳቸው ናቸው። ትዳር የሚፈልጉ የአካባቢው ነዋሪዎችም ቢሆኑ አባ ልጃለም የሌሉበት ሽምግልና አይደምቅም ይላሉ። ከዚህም ባሻገር እሳቸው ያሉበት ስብሰባም ሆነ የምክክር መድረግ በስምምነት መካሄዱ የተለመደ ነው። ምክንያቱም በሳልና የአካባቢው ራስ ናቸውና። በዚህ የተነሳ ደጀና ሲነሳ የአባ ልጃለም ስም በጉልህ መነሳቱ አይቀሬ ነው።
የሕወሓት እና የወልቃይት ጠገዴ ትውውቅ

የወልቃይትና የትግራይ ሕዝብ ግንኙነት ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ እንደሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፤ መረጃዎችም ይጠቁማሉ። በተለይ ቀደም ባለው ዘመን በርካታ የትግራይ ተወላጆች ወደ ወልቃይት በመሄድ የተለያዩ የጉልበት ሥራዎችን ሠርተው ተከዜ ሳይሞላ ወደ አካባቢያቸው ይመለሱ እንደነበር ይገልጻል።
ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም የሕይወት ታሪካቸውን በተመለከተ ባሳተሙት መጽሐፍ ላይ፣ ሁመራን ጭምር በስሩ የሚያቅፈውን የወገራ አውራጃን ይገዙ የነበሩት ቢትወደድ አዳነ መኮንን አስመራ ላይ በተካሄደ ኤክስፖ ላይ ባቀረቡት መነሻ ሃሳብ በየዓመቱ 40 ሺህ የሚሆን የትግራይ ሕዝብ ወደ ሁመራ እየሄደ ሲሠራ ከርሞ ወደ ትግራይ ሲመለስ ይፈጅበት የነበረውን ረጅም ጉዞ ለማሳጠር ይቻል ዘንድ መንገድ እንዲሠራላቸው ጠይቀው እንደነበር ጠቅሰዋል።
በ1972ዓ.ም የወልቃይት ወረዳ አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ተስፉ የሺወንድም እንደሚገልጹት የወልቃይት፣ ጠገዴና ሁመራ አካባቢ የለም መሬት ባለሀብት በመሆኑ አርሶ አደሩ በርካታ እርሻ ነበረው። በዚህ የተነሳ የአካባቢው አርሶ አደር ገንዘብ እየከፈለ ከትግራይ የሚመጡ የጉልበት ሠራተኞችን ያሠራ ነበር። እነሱም እህል ከተሰበሰብ በኋላ ተከዜ ሳይሞላ ተሻግረው ይሄዳሉ።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በወልቃይት፤ ጠገዴና ጠለምት ሕዝብ ላይ የተፈፀመውን ጅምላ ጭፍጨፋ በተመለከተ ያካሄደውን ጥናት የመሩት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ አስራደ እንደገለፁት፣ አካባቢው በርካታ እንስሳት የሚረቡበት እና ሰሊጥና ጥጥን ጨምሮ በርካታ ሰብሎች የሚመረቱበት ለም አካባቢ ነው። በመሆኑም ሕወሓት ታላቋን ትግራይ ለመመስረት ሲያስብ ይህን አካባቢ መቆጣጠር እንደሚገባ በማመን ለዚህ ሲሠራ ኖሯል ይላሉ።
በሌላ በኩል አካባቢው ከኤርትራና ከሱዳን ጋር የሚዋሰን በመሆኑ ሕወሓት ላለመው ታላቋ ትግራይን የመመስረት ዓላማ ኮሪደር ለማግኘት ይህ አካባቢ ወሳኝ ነው። በዚህ የተነሳ ገና ወደስልጣን ሳይወጣ ጀምሮ ኮሪደር ማግኘት አንዱ ግቡ አድርጎ ሲንቀሳቀስ መቆየቱንና ይህ አካባቢ ከሱዳን ጋር የሚያገናኘው በመሆኑ የትኩረቱ መነሻ እንደሆነም ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ አመላክተዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ በአንድ ወቅት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የማንነት ጥያቄ ይመለስልን በሚል ከወልቃይት ሕዝብ ለቀረበላቸው ጥያቄ «እኛ በጉልበት ነው የያዝነው፤ እናንተም ከቻላችሁ በጉልበት መያዝ ትችላላችሁ» የሚል ምላሽ እንደሰጧቸውም ጠቁመዋል። ይህም የሕዝቡን ጥያቄ በሕጋዊ መንገድ መመለስ አዳጋች በመሆኑ በጉልበት ወደ ማስፈራራት መሄዳቸውን ያሳያል ብለዋል።
ሕወሓት እና ወልቃይት

ሕወሓት የወልቃይት አካባቢን መውረር የጀመረው በ1972ዓ.ም እንደሆነ በወቅቱ የወልቃይት ወረዳ አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ተስፉ የሺወንድም ይገልጻሉ። ሆኖም ሕዝቡ ሕወሓትን ባለመቀበሉ በአጭር ጊዜ ተባሮ ሊወጣ ችሏል። በዚህ ቂም የያዘው ሕወሓት ዳግም አቅሙን በማጠናከር በ1974 ዓ.ም አካባቢውን ተቆጣጠረ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ላለፉት አርባ ዓመታት የሕዝቡን ማንነትና ሀብቱን ቀምቶ ኖሯል።
በተለይ በ1983 ዓ.ም የመንግሥትነት ስልጣን ሲያገኝ የመጀመሪያ አጀንዳው በማድረግ በካርታ ጭምር አስደግፎና ራሱ በቀረጸውና ራሱ ባፀደቀው ሕገመንግሥት ወልቃይትና ጠለምትን በትግራይ ክልል አካቶ እንደጠቀለለው አቶ ተስፉ ጠቅሰዋል።
ነገር ግን የወልቃይት ሕዝብ የሕወሓትን ድርጊት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይቃወም ነበር። «ወልቃይት የአማራ እንጂ የትግራይ አካል ሆኖ አያውቅም» «ወልቃይት፣ ሁመራም ሆነ ጠለምት አማራ ነው፤ ማንነታችን ይመለስ» የሚለው ጥያቄ በሕዝቡ ዘንድ በየጊዜው ይነሳ ነበር።
«ዳገት ያበረታው የአማራ ፍኖት» በሚል የወልቃይትን ጉዳይ በተመለከተ ታሪክ ነክ መጽሐፍ ለንባብ ያበቁት አቶ ቹቹ አለባቸው ከአንድ ዓመት በፊት ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለፁት፣ የወልቃይት ሕዝብ ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ ሕወሓትን ሲታገል ነው የኖረው።
ሕወሓት አማራን በስነልቦናና በኢኮኖሚ የመጉዳት እና ባህሉን የማዳከም ኢላማ ይዞ ሲሠራ ኖሯል ያሉት አቶ ቹቹ ለዚህም ማሸማቀቅ እና አንገቱን ማስደፋት ዋነኛ ስልቱ ነበር ብለዋል። ባለፉት አርባ ዓመታትም ከ500 ሺህ እስከ 700 ሺህ የሚሆን የወልቃይት ሕዝብ በሕወሓት የተነሳ ከቀየው ተፈናቅሏል ብለዋል።
«ወልቃይት ለአማራ ታሪኩ፤ የባህር በሩና የኢኮኖሚ መሠረቱ ነው» ያሉት አቶ ቹቹ፣ ሕወሓት ይህንን ማንነቱን ለመቀማት ከፍተኛ ሥራ ሲሠራ መኖሩንም አብራርተዋል።
ሕወሓት የሕዝብ ጥያቄን ለመቀልበስና ወልቃይት የትግራይ አካል መሆኑን ለማሳመን ታዋቂ የአገር ሽማግሌዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችና ታሪክ አዋቂዎችን ሁሉ እየፈለገ ሕዝቡን እንዲያሳምኑ ጠየቀ፣ ከፊሎቹንም በማስፈራራት ለማሳመን ሞከረ። ነገር ግን አንዳቸውም ይህን ያፈጠጠ የውሽት ትርክት ሊቀበሉ እንዳልቻሉ አቶ ተስፉ ይናገራሉ። እሳቸውም በዚህ የተነሳ አገራቸውን ጥለው ከተሰደዱ የአካባቢው ነዋሪዎች አንዱ ሆነዋል።
በዚህ መልኩ የሕወሓትን ድርጊት ከተቃወሙ የአካባቢው ታዋቂ ሰዎች ውስጥ አንዱ ደግሞ አባ ልጃለም ታዬ ናቸው። አባ ልጃለም ወልቃይት አማራ እንጂ ትግራይ ሆኖ አያውቅም የሚለውን አስተሳሰብ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ያንፀባርቁ ነበር። ይህ ታዲያ በሕወሓት ጥርስ ውስጥ እንዲገቡ አደረጋቸው። ሊበቀሏቸውም ተነሱ።
በእነ አባ ልጃለም ላይ የተፈፀመው ግፍ

የአባ ልጃለም የልጅ ልጅ የሆነው አቶ ተመስገን በራ እንደሚለው አባ ልጃለም ለዘመናት የኖሩበትን የወልቃይት አካባቢ ማንነት ለመለወጥ የተጀመረው ነገር ፈጽሞ የማይሆን መሆኑን በመግለጽ ሕወሓት ከዚህ ተግባር እንዲታቀብ አሳሰቧቸው። ወልቃይት የአማራ እንጂ የትግራይ አካል ሆኖ እንደማያውቅም ታሪክ ጠቅሰው ሞገቷቸው።

ይህ ግን ለሕወሓት ትልቅ የራስ ምታት ነበር። በዚህ የተነሳ ይህንን ሃሳባቸውን ለማስቀየር አንዴ በሰላማዊ መንገድ፤ ሌላ ጊዜ በማስፈራራት በርካታ ጥረቶችን አደረጉ። ከዚያ በኋላ የእሳቸውን አለመቀበል ሲመለከቱ በ1978 ዓ.ም ባዶ ስድስት ወደሚባል እስር ቤት አስገቧቸው። በዚያ ለስድስት ዓመታት ቆይተዋል። በእስር ቤት ቆይታቸውም በርካታ ግፎች ተፈፅሞባቸዋል። በእስር ቤት ውስጥ ሁሉንም ዓይነት የግፍ መንገዶች በመጠቀም አሰቃይተዋቸዋል።
ግፉ በዚህ ብቻ አላበቃም። ከዚያ በኋላ ስቃዩ እንደውርስ ወደ ልጆቻቸውና ሌሎች ቤተዘመዶቻቸው ዞረ። የቤተሰቡን ንብረት በመውረስ ወደድህነት እንዲገቡ አደረጉ። ሌላው ቀርቶ ዛፎቻቸው እንኳን ከግፉ አላመለጡም። እኒያ እንደልጆቻቸው የሚወዷቸውና ተንከባክበው ያሳደጓቸው ዛፎች የጥፋ ምሳር አረፈባቸው። የእነዚህ ዛፎች ቅሪት ዛሬም ህያው ምስክር ሆኖ ለታሪክ ተቀምጧል።
አቶ ተመስገን እንደሚለው በወቅቱ አልጋ ላይ መተኛት የለባችሁም በማለት አልጋቸውን እና የሚተኙበትን መኝታ ጭምር ጭነው ወስደዋል። ጥረው ግረው ንብረት ሲያፈሩም በየዓመቱ እየጠበቁ ለአራት ዓመታት ዝርፊያ ፈጽመውባቸዋል።
ልጃቸው አቶ አዲሰይም የአባቱ መንገላታት ከአቅሙ በላይ ሲሆንበት ወደጫካ በመግባቱ እሱን ካላመጣችሁ አንዳችሁም በሕይወት አትኖሩም በሚል በዛቻና በማስፈራራት እንዲሁም ከፍተኛ ስቃይ በመፈፀም እንዳሰቃዩአቸው አቶ ተመስገን ይናገራል። ከዚህ በኋላ አባ ልጃለም እስከእለተ ሞታቸውም ድረስ በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ኖረው በመጨረሻ ማለፋቸውን ይናገራል።
ከዚያ በኋላ በ1984 ዓ.ም አለምሸት ልጃለም ታዬ፣ በ1988 ዓ.ም ደግሞ አዲሰይ ልጃለም ታዬ የተባሉ ልጆቻቸው የሕወሓት ካድሬዎች የግፍ ጭካኔ ሰለባ ሆኑ። ሌላኛው ልጃቸው ወጣት ተክሌ ልጃለም ደግሞ በዳንሻ እስር ቤት ከታሰረ በኋላ የት እንደገባ እስከመጨረሻው ድረስ ሳይታወቅ ኖሯል፤ ዛሬም ቢሆን ይኑር ይሙት የሚያውቅ የለም።
አቶ ተስፉ እንደሚሉት ሕወሓት በዚያን ጊዜ በተለይ የአካባቢውን ተወላጆች ከአካባቢው በማፈናቀል እና የሕወሓት ታጋዮችን በቦታው ላይ በማስፈር የሕዝብ አሰፋፈር ሥርዓቱን ለመቀየር ከፍተኛ ሥራ መሥራቱን ተናግረዋል።
ከዚህም አልፎ በተለይ ታሪክን የሚያውቁ የአካባቢው ነዋሪዎችን እየፈለገ ያጠፋቸው እንደነበር የገለፁት አቶ ተስፉ በዚህ የተነሳ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ተገድለዋል፤ ከፊሎቹም ተፈናቅለዋል፤ ብዙዎች ደግሞ ከሀገር ተሰደዋል ብለዋል።
አቶ ስብሃት ነጋ በወልቃይት
አባ ልጃለም በባዶ ስድስት ውስጥ በታሰሩበት ወቅት በሕወሓት ካድሬዎች ብዙ መከራና ግፍ ቢፈጸምባቸውም ወልቃይት የትግራይ አካል ነው የሚለውን ሃሳብ ሊቀበሉ አልፈለጉም። የዱላ መብዛትም ሆነ የዘመዶቻቸው ስቃይ ከዚህ ሃሳባቸው ፍንክች አላደረጋቸውም። ለመጨረሻ ጊዜ ሃሳባቸውን ለማስቀየር የሕወሓት የነፍስ አባት የሆኑት አቦይ ስብሃት ነጋ ወደ ስፍራው ተልከው እንደነበር የልጅ ልጃቸው አቶ ተመስገን በራ ይናገራል።
አቶ ተመስገን እንደሚለው በ1984 ዓ.ም ክረምት ላይ አቶ ስብሃት ነጋ በደጀና ባዶ ስድስት ተገኙ። ዋነኛ ዓላማቸውም አባ ልጃለምን በማስፈራራት አልያም በማግባባት ማሳመን ነበር። ነገር ግን አባ ልጃለም ማንነታቸውን እንደማይክዱ ለአቦይ ስብሃት እቅጩን ነገሯቸው። ይህ አቦይ ስብሃትንም ሆነ የሕወሓት ካድሬዎችን ተስፋ ያስቆረጠ የመጨረሻ ሙከራ ነበር።
በዚህም መነሻነት አቦይ ስብሃት ተስፋ ቆርጠውና ጭካኔ ጨምረው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፤ ከዚያ አባ ልጃለምም ከእስር እንዲወጡ ተደረገ። ነገር ግን ከእስር ቤቱ የወጡት በሰላም አልነበረም። በመርፌ በተሰጣቸው መድኃኒት አንደበታቸው ተዘግቶ እና ግማሽ አካላቸው መንቀሳቀስ እንዳይችል ተደርጎ ነው። በዚህ መልኩ ለብዙ ጊዜ ሲሰቃዩ ቆይተውም በ1986ዓ.ም ሕይወታቸው ሲያልፍ ግፉ ግን በልጆቻቸውና በዘመዶቸው እንዲሁም በዛፎቻቸው ላይ ጭምር ቀጠለ።
ዛፎችን መረሸን ከትናንት እስከዛሬ

አሸባሪው ሕወሓት በቅርቡ የአማራ ክልልን በወረረበት ወቅት በርካታ ግፎችን መፈፀሙ የሚታወስ ነው። በዚህም በርካታ ጅምላ ጭፍጨፋዎችን ፈጽሟል፤ አዛውንቶችን ሳይቀር ደፍሯል፤ ንብረት አውድሟል፤ እንስሳትንም ዘርፏል፤ መዝረፍ ያልቻለውን ደግሞ ገድሎ ጥሏል።
በዚህ መልኩ የሕወሓት የግፍ ሰለባ ከሆኑት ውስጥ ደግሞ ዛፎችም ይገኙበታል። ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በአንድ ወቅት እንደገለፁት፣ ሕወሓት ከአሸባሪም በላይ ነው።
ዲያቆን ዳንኤል እንደገለፁት፣ አሸባሪ የሚባሉ ሰዎች የሚረሽኑት ሰዎችን ነው፤ ሕወሓት ግን በመቄት እና በጭና ሦስት ነገሮችን ረሽኗል፤ ሰዎችን፣ እንስሳትን እና እፅዋትን። በሌላ አገር የአሸባሪ ታሪክ እንዲህ ዓይነት ተግባር ታይቶ አይታወቅም። ይህ ቡድን ዕድል ቢያገኝ በዓለም ላይ መልካም የተባሉ ነገሮችን ሁሉ ከማጥፋት ወደኋላ የሚል አይደለም።
ይህ ድርጊት ታዲያ አዲስ አለመሆኑንና ሕወሓት ከልጅነቱ ጀምሮ የኖረበት ባህርዪው እንደሆነ በነልጃለም ዛፎች ላይ የፈፀመው ጭፍጨፋ አመላካች ነው። በወቅቱ እነልጃለምን ለማዋረድና ወደ ድህነት ለመመለስ ሕወሓት ከተጠቀማቸው ስልቶች አንዱ ንብረታቸውን ማጥፋት ነበር። በዚህም የሚችለውን ሁሉ ዘርፎ ወስዷል። አቶ ተመስገን እንደሚለው አራት ዓመታት ያህል በየጊዜው እየተመላለሰ ንብረታቸውን ዘርፏል።
ይህም አልበቃ ብሎት ዛሬም ድረስ አሻራቸው የሚታየውንና የአባ ልጃለምን ደጅ ያደመቁት ትላልቅ ዛፎችም ላይ የጥፋት ምሳር አሳርፎባቸዋል። በሌላ ቋንቋ ረሽኗቸዋል።
በወቅቱ ዛፎቹ የተጨፈጨፉበት መንገድ ደግሞ መልሰው እንዳያድጉ ጭምር ከሥራቸው ጭምር በማጥፋት እንደነበር አቶ ተመስገን ይናገራል። ዛፎቹንም ቆርጠው እዚያው የጣሉአቸው በመሆኑ ዛሬም የዛፎቹ «ቅሪተ አፅም» ተጋድሞ ይታያል።
ሰማዕታቱን የማስታወስ ተግባር

ለወልቃይትና ጠገዴ ሕዝብ ማንነት ሲሉ ሕይወታቸውን የገበሩት የአባ ልጃለም ልጆች አፅም በክብር የማሳረፍ ሥነሥርዓት ሚያዝያ 7 ቀን 2014 ዓ.ም በወልቃይት ወረዳ ደጀና ቂርቆስ ቤተክርስቲያን ተካሂዷል። በዚህ ሥነሥርዓት ላይም በብዙ ሺህ የሚቆጠር የወልቃይት እና ጠገዴ ሕዝብ የተገኘ ሲሆን የአማራን ባህል መሠረት ያደረገ የቀብር ሥነሥርዓት በደማቅ ሁኔታ ተካሂዷል።
በዚህ ወቅትም በግፍ ለተገደሉና እንደ አልባሌ ዕቃ በየቦታው ተጥለው የነበሩት የአለምሸት ልጃለም እና አዲሰይ ልጃለም አፅም ከወደቀበት ተነስቶ በክብር እንዲያርፍ ተደርጓል።
በአጠቃላይ ያነጋርናቸው የአካባቢው ተወላጆችም ሆኑ ልዩ ልዩ ሰነዶች እንደሚያሳዩት ሕወሓት በወልቃይት ሕዝብ ላይ የፈፀመው ጅምላ ጭፍጨፋ ዋነኛ ዓላማ የአማራን ሕዝብ ከአካባቢው በማጥፋት የሥነሕዝብ አሰፋፈር ሥርዓቱን ለመቀየር ነው።
ይህ ደግሞ በአንድ በኩል አካባቢው ለም በመሆኑ ይህንን ሀብት በመዝረፍ «ታላቋ ትግራይ» የሚላትን የራሱ አገር ለመመስረት ሲሆን ከዚህ ባሻገር ወደሱዳን መውጫ ኮሪደር ለማግኘት ነው።

ይህንን እውን ለማድረግም የወልቃይትን ሕዝብ በመግፋት በምትኩ አብረዋቸው ሲታገሉ የነበሩ የትግራይ ተወላጆችን አስፍረዋል፤ የአካባቢውን ሕዝብ ማንነት በቋንቋና በሥነልቦና ለመቀየር ብዙ ጥረት አድርገዋል።
ይሁን እንጂ ማንነት በኃይል የሚቀየር ጉዳይ ላለመሆኑ የወልቃይት ሕዝብ ከአርባ ዓመት በኋላ ማንነቱን ይዞ በመቆየት እና ሕወሓትን በመፋለም ነፃ መውጣት መቻሉ ማሳያ ነው።
በወርቁ ማሩ