Site icon ETHIO12.COM

« ይህ የጥፋት ሃይል ከኢትዮጵያ ምድር ተጠራርጎ እስከሚጠፋ ዳግም አፈር ልሶ እንዳይነሳ በሚደረገው አገር የማዳን ዘመቻ ዝግጁ መሆኑን በድጋሚ ያረጋግጣል» ጋምቤላ

የጋምቤላ ክልል መንግስትና ህዝብ ለሃገር ሉዓላዊነት በግንባር ያለውን ሰራዊት በስንቅ፣ በገንዘብ፣ በሞራል እና በሰው ኃይል እንደሚደግፍ አስታወቀ

የጋምቤላ ክልል መንግስትና ህዝብ በሃገሪቱ ህልውና ላይ የተቃጣውን አገር የማፈራረስ ዓላማ ያለው ዘመቻ የሚያወግዝ ብቻ ሳይሆን ለሃገር ሉዓላዊነት በግንባር ያለውን ጀግና ሰራዊት በስንቅ፣ በገንዘብ፣ በሞራል እና በሰው ኃይል ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋገጠ።

የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ የሀገሪቱ ጉዳይ የሰጠው መግለጫ ሙሉ ቃል

አገራችን ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት ሆና የኖረችው ለአገራቸው መስዋዕትነት የሚከፍሉ ጀግና ልጆች ስላሏት ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ለአገራቸው ሉዓላዊነት የሚዋደቁ፤ ኢትዮጵያን በልባቸው ተክለው ለክብሯ ራሳቸውን አሳልፈው የሚሰጡ ዜጎች መኖራቸውን ያህል እንደ ህወሓት ጁንታ ያሉ የእናት ጡት ነካሾች፣ የአገርንና የሕዝብን ጥቅምና ሉዓላዊነት አሳልፈው ለውጭ ጠላት የሚሸጡ ከሀዲ ባንዳዎች በኢትዮጵያ ማህፀን ተፈጥረዋል።

የኢትዮጵያ ህዳሴ እውን እንዲሆን መላው የአገራችን ሕዝብ በራሱ አቅም እየገነባ ያለው የህዳሴ ግድብ እንዲጠናቀቅ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድነትና ወንድማማችነት በሚያስፈልግበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ለሃያ ዓመታት ያህል የአገርን ሉዓላዊነት ከመጠበቅ ጎን ለጎን የትግራይን ክልል ሕዝብ ሰብል በመሰብሰብ፣ ቤት በመጠገን፤ አቅመ-ደካማ እናቶችንና አባቶችን በመርዳት በቤተሰባዊ ስሜት በትግራይ ክልል በቆየው የመከላከያ ሠራዊታችን ላይ ጥቅምት 24/2013 ዓ/ም የፈፀመው ጥቃት በቂ ምስክር ነው።

ከዚህ አንጻር በአሸባሪው የህወሓት ጁንታ ድብቅና ከሠው ልጅ ከማይጠበቅ ፍፁም ሰይጣናዊ ሴራ ሌላ ክልሎች ብቻ ሳይሆኑ እወክለዋለሁ የሚለው የትግራይ ክልል ሕዝብም የጥቃቱ ሰለባ ሆኗል።
ከዚህ አንጻር በመከላከያ ሠራዊታችን ላይ ጁንታው ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ መንግሥት ባከናወነው ሕግ የማስከበር ሥራ አሸባሪው የህወሓት ጁንታ አገር ለማፈራረስ ካዘጋጀው ማኒፌስቶው ጋር አብሮ የተቀበረ ሲሆን፤ መንግስታችን ህግ የማስከበር ሥራ ካከናወነ በኋላ ጁንታው ያወደማቸውን በርካታ ውድ የሆኑ መሰረተ ልማቶች በቢሊዮን ብር በጀት በማፍሰስ በፍጥነት በመጠገንና ወደ ስራ በመመለስ የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆነውን የትግራይ ህዝብ ችግር ለመቅረፍ ፈርጀ ብዙ ተግባራት አከናውኗል።

ከዚህ አኳያ የሃገራችንን ሉአላዊነት ከውጪ ሃይሎች ከሚሰነዘሩ ትንኮሳዎች ለመከላከልና ሁለተኛውን ዙር የሕዳሴ ግድብ ለመሙላት ትኩረት መስጠት የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት እና የተበተነው የሕወሃት የጥፋት ሃይል በሚሽሎኮሎኩባቸው አካባቢዎች አርሶ አደሩ ተረጋግቶ ወደ እርሻ ሥራ እንዲገባ በማሰብ መንግስት አርሶ አደሩ ተረጋግቶ የእርሻ ሥራውን እንዲያከናውን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የመከላከያ ሠራዊት ከክልሉ ለቆ እንዲወጣ ወስኗል።

ከዚህም በተጨማሪ የአሸባሪውን ቡድን የጥፋት ዓላማ የተከተሉ እንደገና ማሰቢያ ጊዜ አግኝተው ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመምጣት ዕድል እንዲኖረው ያለ ቅድመ ሁኔታ በሰብዓዊነት ላይ የተመሰረተ የተናጠል የተኩስ አቁም መንግስት ማወጁ የሚታወስ ሲሆን፤ ይህም ውሳኔ መንግሥት በትግራይ ክልል የሚገኙ ዜጎች ይበልጥ እንዳይጎዱ በማሰብ የወሰደው ታላቅ ኃላፊነት የተሞላበት ውሳኔ በመሆኑ የጋምቤላ ክልል ሕዝብና መንግሥት የሚደግፈው ውሳኔ ነው።

መንግስት ወትሮውም ቢሆን ጠላት ብሎ የፈረጀው ጁንታውን እንጂ የአብራካችን ክፋይ የሆነውን ጭቁኑን የትግራይ ህዝብ ባለመሆኑ ችግሩ ዕልባት ያገኝ ዘንድ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ባለፉት ጊዜያት በተከታታይ ሲያቀርብ የነበረውን ጥያቄ እና ከዚህ በፊት በተለያየ ጊዜ ከክልሉ ተወላጆች፣ የሃገር ሽማግሌዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር ሲደረግ የነበረውን ውይይት ከግምት ውስጥ በማስገባት ለሰላም ልዩ ትኩረት በመስጠት ይህንን ሰላም የኢትዮጵያ አንዱ አካል የሆነውን የትግራይ ህዝብ ተቋዳሽ ሊሆን ይገባል ተብሎ በመታመኑ መንግሥት ለተናጠል ተኩስ አቁም አወጀ እንጂ ለ27 ዓመታት ሲዘጋጅ ቆይቶ በ2 ሳምንት ውስጥ ለፈራረሰው ጁንታ ቡድን በመፍራት ወይም በጁንታው በመሸነፍ እንዳልሆነ በትክክለኛ አእምሮ የሚያስብ ዜጋ የሚያውቀው ሀቅ ነው።

በሌላ በኩል ኑሮውን ዋሻ ያደረገው የጁንታው ቀሪ ሃይል ወደተላላኪነት ሥራው ለመመለስ የህዝብ ጠላት የሆነውን ጁንታውን ሃሳብ በሰብዓዊ ርዳታ ስም በገንዘብ በመሳሪያ ጭምር ሁለገብ ድጋፍ በማድረግ ጥቂት የምዕራባዊያን መንግስታትና ሚዲያዎቻቸው በኢትዮጵያ ላይ ኢ-ፍትሃዊ የሆነ ጫናና ማዕቀብ በማድረስ ላይ ይገኛሉ።
የጁንታው ርዝራዥም ይህንን የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ኢትዮጵያ ሃገራችን በታሪካችን ነፃ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ምርጫ በማካሄድ ዓለምን አስደምማለች።

በሌላ በኩል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት የተጀመረበትን ድርድሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጉዳዩ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር እንዲቀጥልና ዕልባት እንዲያገኝ ኢትዮጵያ ያቀረበችው ምክረ ሃሳብ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ም/ቤት ተቀባይነት አግኝቷል።
ነገር ግን በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያ እውነት በዲፕሎማሲው ባሽነፈበት ወቅት ላይ የሃገር መከላከያ ሰራዊታችን ለቆ የወጣባቸውን ቦታዎች በወረራ እንደያዘ እና በቀጣይ ኢትዮጵያን የማፈራረስ ጦርነት በተለያዩ ግንባሮች በሃገራችን ላይ ግልፅ ጥቃት ከፍቶብናል።

በመሆኑም የጋምቤላ ክልል መንግስትና ህዝብ ይህንን በሃገራችን ህልውና ላይ የተቃጣውን አገር የማፈራረስ ዓላማ ያለው ዘመቻ የሚያወግዝ ብቻ ሳይሆን ለሃገር ሉዓላዊነት በግንባር ያለውን ጀግና ሰራዊታችንን በስንቅ፣ በገንዘብ፣ በሞራል እና በሰው ኃይል ያልተቆጠበ ድጋፍ መሆኑን ያረጋግጣል።


ይህ የጥፋት ሃይል ከኢትዮጵያ ምድር ተጠራርጎ እስከሚጠፋ ዳግም አፈር ልሶ እንዳይነሳ በሚደረገው አገር የማዳን ዘመቻ ከዚህ በፊት ሲያደርግ እንደነበረው በማንኛውም ያልተቆጠበ ድጋፍ ለማድረግ የጋምቤላ ክልል ሕዝብና መንግሥት ዝግጁ መሆኑን በድጋሚ ያረጋግጣል።


ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር፤ ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ፤

Exit mobile version