የአዲስ አበባ አስተዳደር አቋሙን ይፋ አደረገ

  • የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለአማራ ክልል መንግስትና ህዝብ ያለውን አጋርነት ገለጸ፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ÷የከተማ አስተዳደሩ እና የከተማዋ ነዋሪዎች እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ዛሬም ከክልሉ መንግስት እና ሕዝብ ጎን በመቆም ይሄንን ሀገር አፍራሽ እና የዘራፊ ስብስብ ኢሰብአዊ ድርጊቱን በፅኑ ይቃወማል! ብሏል፡፡

ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆም እንደ ወትሮው ሁሉ ደጀንነቱን ያረጋግጣል! የከተማውን ሰላም በማረጋገጥ የህገ-ወጦችን ተግባር በህግ ሥርአት ያስከብራል! ሲልም ገልጿል።

ክልል ከጦርነት ጉዳት ሳያገግም በስሙ ምለው በሚገዘቱ የጥፋት ኃይሎች ይህን አይነት አስከፊ ችግር ስላጋጠመው እያዘነ ፤ እንደ አስፈላጊነቱ የከተማ አስተዳደሩ በሁሉም ረገድ ከክልሉ ህዝብና መንግስት ጎን በመቆም ይህንን አጥፊ ቡድን ኢሰብአዊ ድርጊቶቹን እንደሚቃወምም አስታውቋል።

የዚህ የጥፋት ኃይል ከአማራ ክልል ቀጥሎ አዲስ አበባን የሽብር እና የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ በተለያየ መንገድ እየሞከረ እንደሚገኝም ተደርሶበታል ነው ያለው በመግለጫው።

እነዚህ አጥፊ ቡድኖች እራሳቸው በጠመቁት የፀብ አጀንዳ አዲስ አበባን እና የአዲስ አበባን ህዝብ የአላማቸው ማስፈፀሚያ ለማድረግ ከተማዋን ደግሞ የግጭት እና ብጥብጥ አውድ ለማድረግ በተግባር እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙም ገልጿል፡፡

ሆኖም ሰላም ወዳዱ እና ሚዛናዊው የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ግዜውን፣ እውቀቱን፣ ገንዘቡን እና ጉልበቱን ለሰላም እና ልማት የሚያውል ቢሆንም፣ በህልውናው ላይ በሰላሙ ላይ እና በልማቱ ላይ የሚቃጣን ማንኛውንም አደጋ እና ስጋት እንደ ወትሮው ሁሉ በግንባር ቀደምነት ይፋለማል። ልማቱንም ያስቀጥላል !! ብሏል የከተማ አስተዳደሩ በመግለጫው፡፡

ይህ የጥፋት ቡድን ለዚህ እኩይ ዓላማው ማስፈፀሚያነት የሚያገለግሉና ምንም አይነት ግጭት ከሌለበት አካባቢ የግጭት ሽሽት እና ተፈናቃይ በማስመሰል በርካታ ፀጉረ-ልውጦችን አስርገው በማስገባት በከተማው ውስጥ የጥላቻ፣ የመከፋፈል እና የአመፅ አላማቸውን ለማራመድ እና የጠመቁትን ሴራ ወደ ህዝቡ ለመርጨት ሲሞክሩ በእኩይ ተግባራቸው ሲንቀሳቀሱ መያዛቸውንም ገልጿል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ እንደ ሁል ጊዜው ሁሉ በቁርጠኝነት ህገ ወጦችን በህግ ስርዓት ያስይዛል!ሲልም በመግለጫው አስፍሯል፡፡

በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህንን መሰል እንቅስቃሴ በንቃት እየተከታተለ ለህዝቡ ይፋ የሚያደርግ ሲሆን ህዝቡን ያሳተፈ እርምጃዎችንም እንደሚወስድም አስታውቋል፡፡

See also  መከላከያ ሠራዊት በጥፋት ሃይሎች ታግቶ የቆየ 7250 ኩንታል እህል አሥለቀቀ

በተጨማሪም እንደ አገር የገጠመን ይህንን ችግር የጋራ ርብርብ የሚሻ በመሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የከተማችን ነዋሪዎች ከጀግናዉ የመከላከያ ስራዊታችን፤ ከአማራ ክልል መንግስት እና ህዝብ ጎን በመቆም እንደ ወትሮው ሁሉ አስፈላጊውን ቁርጠኛ ድጋፍ ያደርጋል!! ብሏል፡፡

ሰላም ወዳድነቱን በሥራ እና ደጀንነቱን በቁርጠኛ ትግል ያረጋግጣል! ሲል ገልጿል በመግለጫው፡፡

…………………………………………………………………..

Leave a Reply