Site icon ETHIO12.COM

ጨፌ ኦሮሚያ ለባህላዊ ፍርድ ቤቶች እውቅና የሚሰጥ አዋጅ አጸደቀ

ሀምሌ 10/2013 (ኢዜአ) ጨፌ ኦሮሚያ በክልሉ የፍትህ ተደራሽነትና ትክክለኝነትን ለማረጋገጥ ያግዛል ላለው የባህላዊ ፍርድ ቤቶች ምስረታ እውቅና የሚሰጥ አዋጅ አጸደቀ።

ጨፌው የ2014 የክልሉ በጀት 124 ቢሊዮን ብር እንዲሆን አጽድቋል።

ጨፌ ኦሮሚያ እያካሄደው የሚገኘው 14ኛ መደበኛ ጉባኤ በሁለተኛ ቀኑ የባህላዊ ፍርድ ቤቶች ምስረታ እውቅና የሚሰጥ አዋጅን ማጽደቅን ጨምሮ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል። ባህላዊ ፍርድ ቤቶቹ ከቀበሌ ጀምሮ የሚመሰረትና የክልሉ ሕዝብ በቀደመው ባህሉና ወጉ መሰረት ፍትህ እንዲያገኝ ያግዛል ነው ተብሏል።

ፍርድ ቤቶቹ በተለይ በመደበኛ ፍርድ ቤቶች በፍትህ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ ፈተና የሆነውን ሀሰተኛ ምስክርነት ለመቀነስ እንደሚረዳም ተገልጿል። በዋናነት የክልሉ ሕዝብ የቀደመ ባህላዊ የፍትህ አሰጣጥ ሂደትን ተከትሎ የሚያጋጥሙ አለመግባባቶችን ለመፍታት ያስችላልም ተብሏል።

ረቂቅ አዋጁን ያቀረቡት የህግ ተመራማሪው አቶ ሚልኪ መኩሪያ እንደሚሉት ፍርድ ቤቶቹ የፍትህ ተዳራሽነትን የበለጠ ያጠናክራሉ። ከዚህ በፊት በአብዛኛው የክልሉ ነዋሪዎች ፍትህ ለማግኘት ረጅም ጉዞ በማድረግ ለአላስፈላጊ ወጪ ይዳረጉ ነበር ነው ያሉት።

በአዋጁ መሰረት የሚቋቋሙ ፍርድ ቤቶች የክልሉ ሕዝብ ፍትህን በቅርበትና በእውነት ላይ ተመስርቶ እንዲያገኝ ይረዳዋል ብለዋል። ፍርድ ቤቶቹ የመጀመሪያና በፍርድ ሂደቱ ያልረካው አካል አቤት የሚለበት ሁለተኛ እርከን ፍርድ ቤት እንዲኖረው ሆኖ እንደሚደራጅም ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈ ባህላዊ ፍርድ ቤቶቹ አምስት አባላት ያሉትና አባላቱም ለስምንት አመታት የሚያገለግሉ እንደሚሆኑ ተናግረዋል። እነዚህ ፍርድ ቤቶች ከመደበኛና ከማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ጎን ለጎን የሚሰሩ ሲሆን ለክልሉ ህዝብ ትልቅ ጥቅም የሚሰጡ እንደሆነም ገልጸዋል።

በዚሁ መሰረት አዋጁ በጨፌው አባላት በሙሉ ድምጽ ጸድቋል። በተመሳሳይ ጨፌው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጦ ከተወያየበት በኋላ ሪፖርቱን በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ የኦሮሚያ ክልል የአስር ዓመት እቅድ ላይ ሰፊ ውይይት አድርጎ እቅዱን አጽድቆታል። በመጨረሻም የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት የክልሉን ኦዲተር ጀነራል እቅድ አፈጻጸም፣ የ2013 ዓ.ም ተጨማሪ በጀት እንዲሁም የ2014 ዓ.ም በጀት ላይ ውይይት በማድረግ አጽድቆታል።

በዚህም የክልሉ የ2014 በጀት 124 ቢሊዮን ብር ለካፒታልና ለተለያዩ ወጪዎች እንዲውል አጽድቋል። በጀቱ 19 ቢሊዮን ብር ለተለያዩ ወጪዎች፣ 29 ቢሊዮን ለካፒታል በጀትና 73 ቢሊዮን ብር ለወረዳዎችና ለከተማ አስተዳደሮች ድጋፍ እንዲሁም 600 ሚሊዮን ብር ለተጠባባቂ በጀት ተይዟል።


Exit mobile version