Site icon ETHIO12.COM

“ጥብቅ ዕቅድ አለን፣ውጤቱን በቅርብ ቀን ወዳጅም ጠላትም ያየዋል” አብይ አህመድ

“ምንን፣ ለምን፣ እንዴት፣ የትና መቼ ማድረግ እንዳለብን ጥብቅ ዕቅድ አለን። ውጤቱን በጥቂት ጊዜ ውስጥ ወዳጅም ጠላትም ያየዋል። ሠራዊታችን አስፈላጊ ሲሆን እጅን በአፍ ላይ ለሚያስጭን ተልዕኮ ተዘጋጅቷል” ሲሉ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ለሚመሩት ሕዝብ መልዕክት አስተላለፉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አረም የሚነቀለው በደቦ ነው” ሲሉ አሁን የተጀመረውን የአንድነት እንቅስቃሴ ገልጸውታል። አያይዘውም አረምን በደቦ የመንቀሉ የኖረ ባህል የኢትዮጵያ ልጆች በተግባር እያስዩት መሆንን አመላክተዋል።

ምንም እንኳን እዛም እዚህም የሃሳብ መለያየት ቢኖርም አሸባሪውን ቡድን ከመጋፈጥና ከማስወገድ አንጻር ልዩነት እንደሌለ የተቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ” የኢትዮጵያ ልጆች ከአራቱም ማዕዘን የጁንታውን ዕቅድ ለመቀልበስ ተነሥተዋል። ይህ በራሱ ድል ነው። የኢትዮጵያ ልጆች ጠላታቸው ማን እንደሆነ ለይተውታል። እርሱንም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ዐውቀዋል። ያንንም ያደርጉታል” ብለዋል። አክለውም ” አረሙ እንዲነቀል አድርገን እንሠራለን። አረሙን ስንነቅል ግን ስንዴውን እንዳንጎዳው የሚቻለውን ሁሉ ጥንቃቄ እናደርጋለን ”

ሙሉ መልዕታቸው እንደሚከተለው ነው

የገጠምነው ጠላት የኢትዮጵያ ነቀርሳ የሆነውን ጠላት ነው። ጁንታው ያገኘውን የፖለቲካ ሥልጣን የገዛ ሀገሩን ለማፍረስ የተጠቀመ ምናልባት በታሪክ ብቸኛው ቡድን ነው። አብሮ የኖረ ሰይጣን በቶሎ አይነቀልም እንደሚባለው በግራ በቀኝ መፍጨርጨሩ አይቀርም።

በርግጠኝነት ግን ጁንታው መልሶ እንዳይበቅል ሆኖ ይነቀላል።

ይህ የሚሆነው ሁላችንም እንቦጩን ለመንቀል ከተረባረብን ነው። በሂደቱ ውስጥ እዚህና እዚያ ግለሰቦች ሊሳሳቱ ይችላሉ። ሐሳብ የሚከፋፍሉ መረጃዎች ሊሰሙ ይችላሉ። በግብ አንድ ሆነን የአካሄድ ክርክር ይፈጠር ይሆናል።

ያም ሆነ ይህ ከግባችን አያናጥበንም። የኢትዮጵያ ልጆች ከአራቱም ማዕዘን የጁንታውን ዕቅድ ለመቀልበስ ተነሥተዋል። ይህ በራሱ ድል ነው። የኢትዮጵያ ልጆች ጠላታቸው ማን እንደሆነ ለይተውታል። እርሱንም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ዐውቀዋል። ያንንም ያደርጉታል።

ይህ አንድነታችን ያስፈራቸው ኃይሎች የሚከፋፍል የመሰላቸውን ነገር ሁሉ ያደርጋሉ። ዓይነ መዓታችንን ከእነርሱ ላይ አንሥተን በገዛ ወገኖቻችን ላይ እንድንተክል ያሤራሉ። ፈጽሞ አናደርገውም።

አሁን የፈጠርነው አንድነት የጁንታውን የጥንት ሤራ ያፈረሰ፤ ቀጥሎም የሤራውን ባለቤት የሚያፈርስ፤ በመጨረሻም የተሤረባትን ሀገር በአንድነት የሚያድስ ነው።

መከላከያ ኃይላችንና የክልል ኃይሎቻችን ተገቢውን ቦታ እየያዙ ነው። ያንን ለማወክ ትንኮሳ ይኖራል። ለዚያ ለራሳችን ቃል የገባነውን የተኩስ አቁም እያከበርን ተገቢውን ምላሽ ይሰጠዋል።

ምንን፣ ለምን፣ እንዴት፣ የትና መቼ ማድረግ እንዳለብን ጥብቅ ዕቅድ አለን። ውጤቱን በጥቂት ጊዜ ውስጥ ወዳጅም ጠላትም ያየዋል። ሠራዊታችን አስፈላጊ ሲሆን እጅን በአፍ ላይ ለሚያስጭን ተልዕኮ ተዘጋጅቷል። አረሙ እንዲነቀል አድርገን እንሠራለን። አረሙን ስንነቅል ግን ስንዴውን እንዳንጎዳው የሚቻለውን ሁሉ ጥንቃቄ እናደርጋለን።

በሀገራችን አረም በደቦ ነው የሚነቀለው። የኢትዮጵያ ልጆችም እርሱን እያደረጉት ነው።


Exit mobile version