Site icon ETHIO12.COM

በጣና ሀይቅ በተሰወረችው ጀልባ ህይወታቸው ያለፈ የሰባት ሰዎች አስከሬን ተገኘ


በማእከላዊ ጎንደር ዞን ምስራቅ ደንቢያ ወረዳ በጣና ሀይቅ 13 ሰዎችን አሳፍራ በጉዞ ላይ እንዳለች በተሰወረችው አነስተኛ ጀልባ ህይወታቸው ያለፈ የሰባት ሰዎች አስከሬን መገኘቱን ፖሊስ አስታወቀ።

የወረዳው ፖሊስ ፅህፈት ቤት ሃላፊ ምክትል ኮማንደር ቸርነት አስማረ ለኢዜአ እንደገለጹት አስከሬኑ የተገኘው በሃይቁ ላይ ላለፉት ሁለት ቀናት በጀልባና በዋናተኞች በተካሄደ አድካሚ ፍለጋ ነው፡፡

እንደ ኢዜአ ዘገባ፤ አስከሬኑ የጣና ሀይቅ በሚያዋስናቸው በጎርጎራና አዲስጌ ድንጌ በተባለ የገጠር ቀበሌ መካከል በሀይቁ ላይ በማእበል ተገፍተው ዛሬ ንጋት ላይ ተንሳፈው መገኘቱን አስረድተዋል፡፡

የቀሪውን የስድስት ሰዎች አስከሬን ለማግኘት ፍለጋው ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመው የጀልባዋን መስመጥ የሚያጣራ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ምርመራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

ጀልባዋ ሐምሌ 9 ቀን 2013 ዓም ሌሊት ድንች የጫኑ 13 ሰዎችን አሳፍራ በወረዳው አዲሰጌ ድንጌ ተብሎ ከሚጠራ ቀበሌ አባን ላይ ጎጥ መነሻዋን በማድረግ ወደ ጎርጎራ ወደብ በጉዞ ላይ እንዳለች መሰወሯ ይታወሳል።

Exit mobile version