Site icon ETHIO12.COM

በማይካድራ ከ1ሺህ 644 በላይ ሰዎች በግፍ መጨፍጨፋቸው ይፋ ሆነ፤

ዩኒቨርሲቲው በማይካድራው ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ላይ ስድስት ወራት የፈጀ ጥናት ሠርቷል። የጥናቱ ዓላማ ድርጊቱን ለዓለም አቀፍ ማኀበረሰብ ማሳወቅ፣ ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡና የተጎዱ ወገኖች እንዲካሱ ማድረግ ነው። በጥናቱ አሸባሪው የትህነግ ቡድን ለዓመታት በወልቃይት ጠገዴና በጠለምት አካባቢ በአማራዎች ላይ የፈጸመው ግፍ ተዳስሷል።

በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኀላፊና መምሕር ባምላክ ይደግ (ዶ.ር) ጅምላ ጭፍጨፋው በ1968 ዓ.ም አሸባሪው የትህነግ ቡድን ያዘጋጀው ፍኖተ መርህ አካል እንደሆነ ገልጸዋል።

ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጀምሮ በድምጽ አልባ መሳሪያ ጅምላ ጭፍጨፋ ለሚፈጽሙ ወጣቶችና ለፖሊስ አባላት ስልጠና ተሰጥቷል፤ የባለሀብቶችን አስከሬን ለማመላለስ ዝግጅት ሲያደርጉ እንደነበርም በጥናቱ ተረጋግጧል።

ከድምጽ አልባ መሳሪያ የሚያመልጡትን በመሳሪያ የሚገድል ቡድንም ተዘጋጅቶ ነበር። ከዚያም በማይካድራ ከተማ የሚኖሩ አማራዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ ማሳሰቢያ ተሰጠ፤ መታወቂያና ሲም ካርዳቸውን በመሰብሰብም ማንነታቸውን የመለየት ሥራ ተከናወነ፤ ለቀናት በቂ ዝግጅት ከተደረገ በኋላም ጥቅም 30 እስከ ለሊቱ 9:00 ድረስ በአሰቃቂ ሁኔታ ጭፍጨፋው ተፈጽሟል።

ሰነዶችን ዋቢ በማድረግ፣ የአካባቢውን ነዋሪዎች በመጠየቅና የመስክ ምልከታ በማድረግ በተሠራው ጥናት በወልቃይት ጠገዴና በጠለምት አካባቢዎች በርካታ ጅምላ መቃብሮች ተገኝተዋል። የጥናት ቡድኑ አባል ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ አስራደ እንዳሉት በርካታ ወጣቶችና ታሪክ አዋቂዎች ተገድለው በጅምላ ተቀብረዋል።

ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም በማይካድራ በተፈጸመ የዘር ጭፍጨፋ ብቻ ከ 1 ሺህ 644 በላይ ሰዎች ሰለባ ሆነዋል። 1 ሺህ 563 ሰዎች በጅምላ መገደላቸው በጥናቱ ተረጋግጧል። 81 ሰዎች ደግሞ አካል ጉዳተኛ ሆነዋል። ከ50 በላይ ሕጻናትም ያለ ወላጅ ቀርተዋል። ከዚህ ውስጥ ዘጠኙ ሴቶች ናቸው።

መረጃ ከተጠናቀረ በኋላ ተጨማሪ 31 ሰዎች ተገድለው መገኘታቸውን የገለጹት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ ይህም የሟችና የተጎጂዎች ቁጥር ከዚያ በላይ እንደሚሆን ማሳያ ነው ብለዋል። የተጨፈጨፉ ሰዎች አማካይ ዕድሜም 31 ነው።

ሌላኛው የሕግ መምህርና የጥናት ቡድኑ አባል ደመወዝ ካሴ (ዶ.ር) የኢትዮጵያን የወንጀል ሕግ፣ ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ለማቋቋም የወጣውን ስምምነት እና የዘር ፍጅትን ለመከላከልና ለመቅጣት የወጣውን የሕግ ማዕቀፍ ዋቢ አድርገው በሰጡት ማብራሪያ መሠረት ጅምላ ጭፍጨፋው ማንነትን መሠረት ያደረገ ነው።

ድርጊቱ ፍረጃን፣ የጥፋት ዝግጅትን እና የተፈጸመውን ወንጀል መካድን ጨምሮ የተቀመጡ 11 ዓለም አቀፍ ዝርዝር መስፈርቶችንም አሟልቷልም ነው ያሉት። ድርጊቱ በአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ የሥነልቦና ጉዳት አድርሷል። ዘረፋ ስለተፈጸመባቸውም ማኅበራዊ ሕይወታቸው ለአደጋ ተጋልጧል።

የወንጀሉን ክብደት ያህል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት አልሰጠውም። ፍትሕ እንዲሰፍን ለበደለኞች አልወገነም። የጉዳቱ ሰለባዎች ለከፋ ማኅበራዊ፣ ስነልቦናዊና ምጣኔ ሀብታዊ ችግር ቢጋለጡም አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ትኩረታቸውን ወደ ሌላ አዙረዋል። ይህም በመረጃ እጥረት ሳይሆን የራሳቸው አጀንዳ ስላላቸው መሆኑን ነው ምሁራኑ ያነሱት። ይህም ተገቢነት የለውም ብለዋል።

ምሁራኑ እንዳሉት ወንጀለኞችን ለሕግ ማቅረብ እንደሚገባ መክረዋል። ሀገር ውስጥ የሚገኙትን መንግሥት ኀይሉን ተጠቅሞ በቁጥጥር ስር ማዋል አለበት፤ በውጪ ሀገራት ያሉትን ደግሞ ከሀገራት ጋር በመተባበርና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር ለፍርድ ማቅረብ ይጠበቅበታል። በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት ዘር ተኮር ጅምላ ጭፍጨፋ ይርጋ ስለማያግደው ወንጀለኞቹ በማንኛውም ጊዜ ተጠያቂ ናቸው።

ተጎጂዎችን ማቋቋምና የሕክምና ድጋፍ መስጠት ይገባል ብለዋል።

የጥናቱ ግኝት የመጀመሪያው ዙር የአማርኛ ጽሑፍ እየተጠናቀቀ ነው ብለዋል። መረጃው በተለያዩ ዘዴዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቀው ይደረጋል። ወደ እንግሊዘኛ ቋንቋ በመተርጎምም ለዓለም አቀፍ ተቋማት፣ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የውጪ ሀገራት ኢምባሲዎች እንዲሁም ለልዩ ልዩ ሀገራት እንዲደርስ ይደረጋል ብለዋል። የ41 ዓመታት ችግር በአንድ ጥናት ብቻ ስለማይመለስ ሌሎች ተቋማት ተጨማሪ ጥናት እንዲያደርጉም መምህራኑ ጠይቀዋል ሲል አሚኮ ዘግቧል።


Exit mobile version