Site icon ETHIO12.COM

“ለኢትዮጵያ የተዘረጋው ወጥመድ ከወዲሁ እየተበጣጠሰ ነው”

ይህ ምን ዜና ይሆናል ብለህ ነው? የምትደብቀው እውነት እንጂ አሸነፍኩ ብለህ የምታቅራራበት ድል አይደለም። የሰው ልጅ እልቂት፡ የአስክሬን ክምር እያየህ፡ አንድ ፍሬ ህጻናት፡ ያነገቱት ጠመንጃ ከብዷቸው እየተንገታገቱ ማርከሃቸው ይህን ምን ድል ብለህ ታበስራለህ? እነሱ ቢሆኑ ሊያደርጉት ይችላሉ። ለእኛ ግን ከባድ ነው። የሀገርን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ ግን ምርጫ በሌለው ጦርነት ውስጥ ገብተናልያለኝ ከእነድምጸቱ አሁን ድረስ ከጆሮዬ ያቃጭልብኛል።

ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን


ለኢትዮጵያ የተዘረጋው ወጥመድ ከወዲሁ እየተበጣጠሰ ነው። ነጮቹ አይናቸውን ጨፍነው የገቡበትና ኢትዮጵያ ላይ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት በሚል ከጀርባ በፋይናንስና በሀሳብ እየደገፉት ያለው ሴራ በኢትዮጵያ ውድ ልጆች መስዋዕትነት ፍርክስክሱ እየወጣ መሆኑን እያየን ነው። ለወጥመዱ ማሳኪያ፡ ለሴራው ግብ መምቺያ ተደርጎ የታሰበው ትልቁ ተስፋቸው የህወሀት ቡድን በጦር ግንባር ወደፊት በመገስገስ መሬቶችን፡ ከተሞችን ከተቆጣጠረና የኢትዮጵያን ሰራዊት ማዳከም ከቻለ ነው። አፋርና ራያ ላይ የህወሀት ቡድን ለዚህ ወጥመድና ሴራ የሚሆን ድል ይዞ እንዲመጣ ከዋሽንግተን ዲስ እስከለንደን ድጋፉ በዓይነት ሲጎርፍ እንደነበር የአደባባይ እውነት ነው።

የህወሀት መጠናከር የአዲስ አበባውን መንግስት እጅ እንዲሰጥ ያደርጋል፡ በኋላም የመዋጮው መንግስት ይመሰረታል የሚለው ተስፋቸው ግን እንደጠዋት ጤዛ ብን ብሎ መጥፋቱን የሚያረጋግጡት የሰሞኑ የአውደ ውጊያ ዜናዎች በምዕራቡ ዓለም መንደር ግራ መጋባትን መፍጠሩን እየሰማንም ነው። አፋርና ራያ ላይ አከርካሪው እየተመታ ቀድሞ የያዛቸውን ቦታዎች ሁሉ ጥሎ የፈረጠጠው የህወሀት ታጣቂ ሃይል ለቀለብ ሰፋሪዎቹ አለቆች የሚሆን የድል ብስራት ማሰማት አልቻለም። ኢትዮጵያን የነካ ከሽንፈት በቀር መች በለስ ቀንቶት ያውቅና?!

ሰሞኑንም ለዜና የሚሆኑ መረጃዎች ፍለጋ የመንግስትን ባለስልጣናትና ወታደራዊ መኮንኖች ስልክ ላይ በመደወል ተጠምጄ ነበር የሰነበትኩት። የምሰማቸው ነገሮች በሁለት ተቃራኒ ስሜቶች ከወዲህና ወዲያ የሚያላጉኝ ሆነዋል። የህወሀት የቀረች ቅንጣቢ አቅም አፈር ከድሜ እንዲግጥ መደረጉ የሚፈጥረውን እፎይታ አጣጥሜ ሳልጨርስ የሚገደሉት፡ የእሳት እራት እንዲሆኑ የተፈረደባቸው እነማን እንደሆኑ ስሰማ ደግሞ የሀዘን ጽልመት ልቤን ይሞላዋል።

ከጦሩ መሀንዲስ መኮንኖች አንደኛው ” ይህ ምን ዜና ይሆናል ብለህ ነው? የምትደብቀው እውነት እንጂ አሸነፍኩ ብለህ የምታቅራራበት ድል አይደለም። የሰው ልጅ እልቂት፡ የአስክሬን ክምር እያየህ፡ አንድ ፍሬ ህጻናት፡ ያነገቱት ጠመንጃ ከብዷቸው እየተንገታገቱ ማርከሃቸው ይህን ምን ድል ብለህ ታበስራለህ? እነሱ ቢሆኑ ሊያደርጉት ይችላሉ። ለእኛ ግን ከባድ ነው። የሀገርን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ ግን ምርጫ በሌለው ጦርነት ውስጥ ገብተናል” ያለኝ ከእነድምጸቱ አሁን ድረስ ከጆሮዬ ያቃጭልብኛል።

ስሜት ይቆነጥጣል። የህወሀቷ ትግራይ እየተጋተች ያለችውን መከራ የዓለም ህዝብ እንዳይሰማው የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎች ከህወሀቶች ጋር በውሸት የድል ዜና ዳንኪራ እየጨፈሩ ናቸው። የትግራይን ህጻናት ህወሀት ከተባለ ክፉ አውሬ መንጋጋ ፈልቅቆ የሚታደጋቸው ማን ይሆን? እድሜ ዘመኗን ልጆቿን ለህወሀት የማይድን እብደት እየገበረች፡ በመጦሪያ ጊዜዋ ነፍጥ ተሸክማ በረሃ ለበረሃ የምትንከራተትን የትግራይ እናት በቃሽ የሚላት፡ የሚደርስላት አዳኝዋ ከየት ይገኝ ይሆን? ለህወሀቶች ይሄ ጀግንነት ነው። ዲያስፖራ በየመሽታ ቤቱና አውራጎዳናዎች ላይ ለሚፈነጥዙት ተጋሩዎች ይህ ትራጄዲ የአይበገሬነት መገለጫ ነው። ዘረኝነት ልቦናን ሲጋርድ፡ ድንቁርና ማሰቢያን ሲደፍን በእርግጥ ከዚህ ቡድንና ደጋፊዎቹ ርህራሄንና ሀዘኔታን፡ እንደሰው እንዲያስቡ መጠበቅ ጅልነት ነው።

ከወዲያ ማዶ ከትግራይ ምድር የሰው ልጅ መከራና ስቃይ ነግሷል። የምድር ሲዖል ከተባለ በዚህን ዘመን የትግራይ ምድር እንጂ ሌላ ሊገኝ አይችልም። እናት ልጇን ወደ ጦር ሜዳ ካላከች በረሃብ እንድትቀጣ እነጌታቸው ረዳ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ተሰምቷል። በትግራይ መንደሮች እድሜአቸው ከ8ዓመት በላይ የሆኑ ህጻናትን በቀን በባትሪ ቢፈልጉ ማግኘት የማይቻልበት ዘመን ላይ ተደርሷል።

አርሶአደሮች ሞፈርና ቀንበር ጥለው ክላሽ እንዲያዙ ተደርገዋል። ማሳዎች ጦማቸውን ካደሩ ከርመዋል። መብራት የለም። ውሃ የለም። ግንኙነት የለም። ደምወዝ የለም። ንግድ እንቅስቃሴ የለም። ትምህርት የለም። ህወሀት የትግራይን ምድር ወደድንጋይ ዳቦ ዘመን በፍጥነት እንድትቀየር አድርጓታል። ጨለማ ምድር። የጥይት ጩኸት የሚያስካካባት፡ የባሩድ ጢስ ሰማይዋን ያጠቆረባት፡ የሰው ልጅ አስክሬን እንደውሻ በካሚዮኖች እየተጫነ የሚጓጓዝባት አኬልዳማ ምድር። ህወሀትን የፈጠረ ማህጸን ምነው መሀን በነበረ?! ለትግራይ ህዝብ መቅሰፍት ይዞ የተነሳ ክፉ ቡድን!!

በእርግጥም የትግራይ ህጻናት እልቂትን ለሚዲያ ዜና ማድመቂያ መጠቀም የሞራል ክስረት ነው። የእናቶችን ሞትና ስቃይ እያነሱ የድል ብስራት ለመንገር የሚከፈቱ አፎች ሊኖሩ አይገባም። ጀነራል መኮንኑ እንዳሉኝ ይህ ትራጄዲ ለአደባባይ ወሬ የሚበቃ አይደለም።

አሁን ላይ የሚያስጨንቀው ይህን እንዴት ማስቆም ይቻላል የሚለው ነው። ምዕራባውያን ለኢትዮጵያ መዳከምና ለመንግስቷ መንበርከክ እስከጠቀመ ድረስ የህጻናቱ እልቂት ጉዳያቸውም እንዳልሆነ ጭው ካለው ዝምታቸው ተረድተናል።

የእነዚህ ህጻናትና እናቶች እልቂት የኢትዮጵያ ጦር ትግራይ በነበረ ጊዜ የተፈጸመ ቢሆን ኖሮ ከኋይት ሀውስ እሰከ ለንደኑ ዶዊንግ ጎዳና ድረስ የሚሰማው ጩኸት የጆሮን ታንቡር ይበጥስ ነበር። እነሮይተርስ፡ አልጀዚራ፡ ቢቢሲ፡ ኒውዮርክ ታይምስ ሌሎችም ታላላቅ ሚዲያዎች ትንፋሽ የሚያሳጣ የዘገባ ናዳ ይለቁብን ነበር። ምን ያደርጋል? እነዚህ ህጻናት ወንዝ ተሻግረው፡ ከሌላው መንደር ለትንኮሳ ተልከው መገደላቸው እነአሜሪካንን አፍ አሳጣቸው።

ዋናው ነገር ኢትዮጵያ ላይ የተደቀነው የስጋት ዳመና ቀስ እያለም ቢሆን እየተገፈፈ መሄዱ ነው። በህጻናቱ እልቂት የተደገሰው የኢትዮጵያ ጥፋት ሊሳካ እንደማይችል የሰሞኑ የጦር ሜዳ ውሎዎች ለጠላትም ለወዳጅም አረጋግጠዋል። ኢትዮጵያ ላይ የተዘረጋው ወጥመድ በውድ ልጆቿ መስዋዕትነት፡ በአምላኳ ቸርነት፡ በህዝቧ ጸሎት ፍርክስክሱ መውጣቱ የማይቀር ነው። ከወዲሁ ጀምሮታል። ኢትዮጵያውያን ቀና ብለው በክብር የሚታዩበት፡ ጠላት በበኩሉ አንገቱ ተሰብሮ የሚሸማቀቅበት ጊዜ ሩቅ አይደለም።

Exit mobile version