Site icon ETHIO12.COM

“ አሸባሪው የህውሃት ቡድን በትግራይ ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመ ነው -“


አሸባሪው የህወሓት ቡድን በትግራይ ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመ በመሆኑ በዓለምአቀፍ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሊጠየቅ እንደሚገባ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) አስታወቀ።

ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪ ቡድኑ በትግራይ ክልል እያደረሰ ያለውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ በአግባቡ እንዲረዳ ማድረግ ተገቢ መሆኑም ተጠቁሟል።

የትዴፓ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሙሉብርሃን ሃይሌ፤ አሸባሪው ህወሃት የትግራይን ህዝብ መሸሸጊያ በማድረግ ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለው መሆኑን ገልጸዋል።

ቡድኑ እታገልለታለሁ እያለ ለሚያወራለት ለትግራይ ህዝብም ሆነ ለመላው ኢትዮጵያውያን ምንም ዓይነት ሃላፊነት እንዳማይሰማው ጠቁመው፤ ይህንንም በተደጋጋሚ በፈጸማቸው እኩይ ተግባራት በግልጽ ያሳየ መሆኑን አብራርተዋል።

ቡድኑ ከስልጣን ከወረደ በኋላ የሚፈጽመው ግፍና በደል ደግሞ እየከፋ መምጣቱን አቶ ሙሉብርሃን ተናግረዋል።

ቡድኑ “ለህዝብ እታገላለሁ ቢልም ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይደርስ ከማድረግ ባለፈ ህጻናትና አቅመ ደካሞችን ጭምር በጦርነት በማሳተፍ ጸረ-ህዝብነቱን በተግባር እያስመሰከረ ነው” ብለዋል።

ይህም ቡድኑን በዓለምአቀፍ ህግ በዘር ማጥፋት ወንጀል የሚያስጠይቀው መሆኑን ጠቁመዋል።
የፌዴራል መንግስት ለህዝቡ በማሰብ የሰጠውን የጥሞና ጊዜ የትግራይ አርሶአደር በአግባቡ እንዳይጠቀም እንቅፋት የሆነው አሸባሪው ህወሓት መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈ አሸባሪ ቡድኑ መላ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ህዝቡ እንዲደግፈው የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

“የትግራይ ህዝብ አሸባሪው ህወሓት በድጋሚ ስልጣን ላይ ይመጣል በሚል በቀቢጸ-ተስፋ ሊጠብቅ አይገባም” ያሉት ሃላፊው፤ ቡድኑ እስኪከስም ድረስ ከሽብር ድርጊቱ እንደማይቆጠብ ተናግረዋል።

መንግስት የሽብር ቡድኑን እኩይ ተግባር በጥንቃቄ መመከትና የትግራይን ህዝብ ነጻ ማውጣት እንዳለበትም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያውያን ተጋሩ ሲቪክ ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዮሃንስ ጎይቶም በበኩላቸው፤ መንግስት ለትግራይ ህዝብና ለአርሶአደሩ የእፎይታ ጊዜ ለመስጠት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች በክልሉ ከፍተኛ ስርዓት አልበኝነት እንዲንሰራፋ አድርገዋል።

ለአብነትም ህጻናትና አቅመ ደካማ አረጋውያንን ለጦርነት ከማሰለፍ ጀምሮ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወንጀለኞችን በመልቀቅ ዝርፊያና ህገ-ወጥ ተግባር እንዲበራከት ማድረጉን አንስተዋል።

በትግራይ ህዝብ ላይ የሚከሰቱ ግፍና መከራዎች መነሻ አሸባሪው የህወሓት ቡድን መሆኑን ጠቅሰው፤ ቡድኑ ከዓለምአቀፍ የጦር ወንጀለኝነት ባለፈ በዘር ማጥፋት ወንጀል ሊጠየቅ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የትግራይ ህዝብም ቡድኑ ለረጅም ዓመታት ሲያደርስበት የነበረውንና አሁንም እያስከፈለው ያለውን ዋጋ በአግባቡ በመረዳት ይህን ሃይል ታግሎ ነጻ መውጣት እንዳለበት አመልክተዋል።

ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ የአሸባሪው ህወሓት ቡድን በትግራይ ክልል እየፈፀመው ያለውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት አይቶ እንዳላየ ማለፉ ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

ቡድኑ በተሳሳተ ፕሮፓጋንዳ የውጭውን ማህበረሰብ ለማሳሳት የሚያደርገው ሙከራም በእውነተኛ መረጃ ሊከሽፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አቶ ሙሉብርሃን በበኩላቸው ቡድኑን በእውነተኛ መረጃ ለማጋለጥ ተባብሮ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል። EBC

Exit mobile version