Site icon ETHIO12.COM

ከሳውዲ አረቢያ ከተመለሱ ስደተኞች ውስጥ የትግራይ ክልል ተወላጆች ቁጥር ከፍተኛ ነው

በበእምነት ወንድወሰን 

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ከሳውዲ አረቢያ ከተመለሱ 42 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መካከል አንድ ሶስተኛ ገደማ የሚሆኑት የትግራይ ክልል ተወላጆች መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። ከስደት ተመላሾች ውስጥ በቁጥራቸው ብዛት በሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ የተቀመጡት የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች መሆናቸውንም ሚኒስቴሩ ገልጿል። 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመሆን ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተነገረው፤ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ  41, 878 ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው መመለስ ተችሏል። በሰላም ሚኒስቴር የህግ ማስከበር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አምባዬ ወልዴ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ መንግስት በቀን ከ1,500 እስከ 3,000 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ከሳዑዲ አረቢያ ሲመልስ ቆይቷል። 

ፎቶ፦ ከፋና ቴሌቪዥን የተወሰደ 

ከተመላሽ ስደተኞች መካከል 13,895ቱ የትግራይ ክልል ተወላጆች መሆናቸውን የተናገሩት አቶ አምባዬ፤ ይህም ከሌሎች ክልሎች ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። በትግራይ ያለው ከፍተኛ የሆነ ድህነት እና ስራ አጥነት፣ የተደራጁ እና ህጋዊ የሚመስሉ ህገ-ወጥ ደላሎች መበራከት እንዲሁም ወላጆች ከድህነነት ለመውጣት ያላቸው ፍላጎት በልጆቻቸው ላይ ያሳደረው ጫና፤ ከክልሉ ለሚሰደዱ ዜጎች ቁጥር ከፍ ለማለቱ ምክንያቶች እንደሆኑ አቶ አምባዬ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ከስደት ተመላሽ ከሆኑት የትግራይ ተወላጅ ዜጎች ውስጥ በአሁኑ ሰዓት በጊዜያዊ ማቆያ ያሉት ቁጥራቸው ሁለት ሺህ ገደማ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ ዲና ሙፍቲ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጠቁመዋል። ስደተኞቹ እስካሁን በማቆያ ውስጥ የቆዩበት ምክንያት ወደ ትግራይ ክልል ለመሄድ የትራንስፖርት ችግር በመኖሩ መሆኑንም አስረድተዋል። የትራንስፖርት ችግር እስኪፈታ እና ወደ ቤታቸው መሄድ እስከሚችሉ ድረስም “ዘመዶቻቸቸው ፈርመው ማስወጣት ይችላሉ” ብለዋል ቃል አቃባዩ። 

ፎቶ፦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ ጽህፈት ቤት

ከሳዑዲ አረቢያ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከተመለሱ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ውስጥ፤ ከትግራይ ክልል ከተሰደዱት ጋር በብዛታቸው ተቀራራቢ የሆኑት የአማራ ክልል ተወላጆች ናቸው። ከተመላሾቹ ውስጥ የአማራ ክልል ተወላጆች ቁጥር 13,813 መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር የህግ ማስከበር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ቁጥራቸው 11, 362 መሆኑ የተገለጸው የኦሮሚያ ክልል ተመላሽ ስደተኞች በብዛታቸው ሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸውም ተገልጿል። የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ባሰባሰበው መረጃ መሰረት፤ ከስደት ተመላሾች ውስጥ የመጨረሻው እና ዝቅተኛው ቁጥር የተመዘገበው ከሶማሌ ክልል ነው። ከሳዑዲ አረቢያ የተመለሱ የሶማሌ ክልል ተወላጆች ቁጥር 19 ብቻ መሆኑን አቶ አምባዬ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ የስደተኞችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን እና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት በመንግስት በኩል እየተደረጉ ስላሉ እንቅስቃሴዎች ለሁለቱ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። ተመላሽ ስደተኞች “በፊት በር እየገቡ፤ በጀርባ ተመልሰው እየሄዱ በመሆናቸው መንግስት የሚያደርገው ሁሉ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ እየሆነበት” የሚል ጥያቄም ተነስቷል። 

ፎቶ፦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ ጽህፈት ቤት

“መንግስት ስደት እና ስደተኞችን በተመለከተ እስከ አሁን የሰራው ስራ በቂ አይደደለም” ያሉት የሰላም ሚኒስቴሩ አቶ አምባዬ፤ መንግስት “ወደፊትም ትልልቅ ስራዎችን መስራት ይጠበቅበታል። ለዚህም እየሰራ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ለስደተኞች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠትም በመንግስት በኩል በስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የስደተኞችን መረጃ ከማጠናከር ባሻገር እና በጉዳዩ ላይ ከክልል ጽህፈት ቤቶች ጋር ስራ እየሰራ እንደሆነ በመግለጫው ላይ ተነስቷል። የስደት ተመላሽ ዜጎች ቀጣይ ዕጣ ፈንታን በተመለከተ የሰላም ሚኒስቴር ከክልሎች ጋር በመሆን በቅርቡ በይዘቱ ሰፋ ያለ የውይይት መድረክ እንደሚያዘጋጅም ተገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Exit mobile version