Site icon ETHIO12.COM

ʺእንዲህ ጨሶ ጨሶ የነደደ እንደሆንያመዱ ማፈሻ ቦታው ወዴት ይሆን”

የማይነካውን ሀገር ነክተው፣ ያልገባቸውን የኢትዮጵያን ስም ጠርተው፣ ክብሯን ለመድፈር ተመኝተው የሚያቃጥለውን ኢትዮጵያዊነት አቀጣጠሉት፣ ጠላትን ጠራርጎ የሚወስደውን ማዕበል ቀሰቀሱት፣ ተበታትኗል ያሉትን ሕዝብ ሰበሰቡት፣ አርፎ የተቀመጠውን ንብ ነካኩት፤ አሁን ማዕበሉ ሊወስዳቸው፣ ንቡ ሊነድፋቸው፣ እሳቱ ሊያቃጥላቸው፣ የጫሩት ጉድጓድ እስከ ዘላለም ሊወጣቸው መጣን ወደ አሉበት ሥፍራ ቀድሞ ሄደባቸው፡፡

ኢትዮጵያዊነት የሚፋጅ እሳት፣ የማይናወጥ አለት፣ የአሸናፊነት ምልክት፣ የድል ብሥራት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ሲያብር ማዕበል ኾኖ ይወስዳል፣ ውቅያኖስ ኾኖ ይውጣል፣ ነደድ እሳት ኾኖ ያቃጥላል፣ ይፋጃል፣ የተከመረውን የጠላት ተራራ ይደረምሳል፣ የክፉዎችን ምሽግ ያፈርሳል፡፡

ኢትዮጵያዊያን ሲነሱ ጠላቶች ሁሉ ዝም ይላሉ፣ የክፋት እጆች ይመለሳሉ፣ የክፋት እግሮች ይቆማሉ፣ የጥል መንገዶች ይዘጋሉ፣ የጠላት አንደበቶች ሁሉ ዲዳ ይሆናሉ፣ ኢትዮጵያዊያንም እንደ ለመዱት ያሸንፋሉ፣ ልካቸው ከፍታ ነውና ከፍ ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያን የነኩ ሁሉ ምድር ክዳቸዋለች፣ ሰማይ ተቆጥታባቸዋለች፣ ነብሳቸው ከስጋቸው አልቆዬችም፣ እየተቅበዘበዘች ታልፋለች እንጂ፤ ኢትዮጵያዊነት ምስጢር፣ ኢትዮጵያ ደግሞ የምስጢር ሀገር ናትና ጠላቶች ሁሉ ከሚስጥሩ በታች ናቸው፡፡

ክብር ለኢትዮጵያዊ ከምንም በላይ ነው፡፡ ሀገር ተነካች ሲባል ነጋዴው ንግዱን፣ ገበሬውን በሬውን፣ ሞፈርና ቀንበሩን፣ እናቶች ስፌትና ፈትሉን አቁመው ተነካች ወደ ተባለበት አቅጣጫ እንደ አስፈሪ ደመና ይጓዛሉ፡፡ ያንዣበቡትን የቁጣ ደመና ያዘንባሉ፣ በማዕበል ጠራርገው ከሀገራቸው ያስወጣሉ፡፡ ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀሩ ከአፈር ጋር ያዋህዳሉ፡፡ ለክብር የሚሳሱት ነብስ የለምና፡፡ አቅመ ደካሞች በጸሎትና በስግደት ዘመቻውን የድል አድርገው፣ ኢትዮጵያ ሀገራችን ዳሯን እሳት መሃሏን ገነት አድርግልን እያሉ ለፈጣሪያቸው ምልጃ ያቀርባሉ፡፡ ዘመቻቾቹም ምልጃ አቅራቢዎቹም ዓላማቸው አንድ ነውና በጋራ አድርገውት ያልተሳካላቸው የለም፡፡

በየዘመናቱ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን የተጠመዱ ወጥመዶች ሁሉ ተቆራርጠዋል፣ የቀሩት ደግሞ አጥማጆቹን ይዘዋል፡፡ ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚመከሩ የጠላት ምክሮች ሁሉ ኢትዮጵያን ያጠነክራሉ፡፡ ኢትዮጵያን ለመምታት የሚላኩ ክንዶች ሁሉ እንዳልነበር ይኾናሉ፡፡ የኢትዮጵያ ምስጢር አልገለጥላቸው ብሏል፡፡ ላይችሏት ይገፏታል፣ እንደምተቃጥላቸው እያወቁ ይነካኳታል፡፡

ኢትዮጵያዊያን ችግር የሚያለያያቸው ሳይሆን የሚያገናኛቸው፣ የሚያቃቅራቸው ሳይሆን የሚያፋቅራቸው፣ የሚያዝላቸው ሳይሆን የሚያጠነክራቸው፣ የሚያጎድላቸው ሳይሆን የሚሞላቸው፣ ከፍ ከፍ የሚያደርጋቸው ልዩዎች ናቸው፡፡ ሀገር ተነካ ወገን ተደፈረ ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት በተባለ ቁጥር ሁሉም እንደ ንብ ፈርሶ፣ የጠመንጃውን አፈሙዝ አባብሶ ለሰርግ እንደተጠራ ሁሉ በደስታ ይዘምታል፡፡ እየፎከረ ወደ ጦር ሜዳ ይገባዋል፣ ጠላትን በባሩድ ያንገበግባል፣ የሚተኮሰው ጥይትና የሚወጠው ባሩድ ሽታ ይጠረዋል፣ ʺእሰይ ባሩዱ ሸተተኝ” እያለ ይቀርባል፡፡ ሽቶ የረጩለት እንጂ ጥይት የተኮሱበት አይመስለውም፡፡

ʺሀብት ንበረቱን በቤቱ ጥሎ
ሄደ ዘመቸ ለሀገር ብሎ” እንደተባለ ለኢትዮጵያዊ ከሀገር በላይ ምንም የለም፡፡ ከእርሷ በፊት እኔን ያድርገኝ እያለ ይሄዳል እንጂ፡፡ የግል ሥራዬ ይቀርብኛል፣ ልጆቼ ይናፍቁኛል፣ ቤቴ ይጎድልብኛል ብሎ ነገር የለም ኢትዮጵያ ከተነሳች የጋለው ስሜቱ ይነሳል፣ ነፍጡን አንግቦ ወደ ዘመቻ ይገሰግሳል፣ በየደረሰበት አልሞ ይተኩሳል፣ ጠላትን እጅ ያስነሳል፣ ምሽግ ያፈርሳል፣ አፈር ያለብሳል፡፡

የአሸባሪው ትህነግ እብሪት፣ ከዘመን ዘመን እየጨመረ የሚሄድ ክፋት ኢትዮጵያዊያንን አስቆጥቷቸዋል፣ አንድ አድርጎ አስነስቷቸዋል፣ ለአንድ ዓለማ የጋራ ጠላትን ለማጥፋት እንዲነሱ ገፋፍቷቸዋል፡፡ አሁን በየአቅጣጫው መጣንብህ እያሉት ነው፣ በተባበረ ክንዳችን እንቀብርሃለን፣ በኃያሉ ክንዳችን ክብራችን እናስቀጥላለን፣ ዓለምን ዳግም እናስደምማለን፣ ሠንደቋን ከፍ እናደርጋለን እያሉ ነው፡፡ ደግሞም ያደርጉታል፤ ላያደርጉ አይነሱም፣ ሳያደርጉት አይመለሱም፡፡

ʺአወይ አተኳኮስ ወይ ደፋር መኾን
ሲሄድ መቀነቻ ሲዞር ግንባሩን” አሁን ሲዞርም ሲሄድም ከእርሳስ አያመልጥም፡፡ ለክፉ ቀን የተቀመጠው ነፍጥ ተነስቷል፣ የዘመኑ አርበኞች እንደ አንበሳ አግስተው፣ እንደ ነበር ተቆጥተው ገስግሰዋልና፡፡ ማንስ ያቆማቸዋል፣ ማንስ ይመክታቸዋል፣ እውነትና ጀግንነት ይዘው ተነስተዋልና፡፡ የሚቆሙት ድል ሲያደርጉና ጠላት ከተቀደሰችው ምድር ላይ ሲጠራርጉ ብቻ ነው፡፡ የተዳነፈነን እሳት መነካከት ትርፉ መለብለብ ብቻ ነውና፡፡

ʺ አጥቢት ሲወጣ ሲነጋ ሌሊት
ጠላት ጎሳሚ እንደ ነጋሪት” ጠላትን እንደ ነጋሪት እየጎሰመ፣ ቢሻው ደረቱን፣ ቢሻውም ባቱን እየመታ ወደፊት ይገሰግሳል፡፡ አንተ ፍርሃት በልቡ ያልፈጠረበት፣ ጠላት የሚበረግግለት፣ ጀግንነቱ ከዓለም እስከ ዓለም የሚነገርለት፣ በቅርብ ያሉት የተገዙለት፣ በሩቅ ያሉት እጅ የነሱለት፣ በዝናው የተሸበሩለት ጀግና ሕዝብ ልጅ ነህ፡፡ ጠላትን በእሳት ጅራፍ የሚገርፍ፣ ከወሰኑ ወዲህ የማያሳልፍ፣ አመጸኛን በጥይት የሚቀስፍ፣ ወዳጅን በፍቅር የሚያቅፍ ሕዝብ ልጅ ነህ፡፡

በጀግንነቱ የእኩል ዘመን አምጥቷል፣ በግዞት የነበሩትን ነጻ አውጥቷል፣ ኃያላኑን አንኮታኩቷል፣ ሀገሩን አኩርቶ ራሱም ኮርቷል፣ በምድር የሰው ልጅ እኩልነት እንጂ የአንደኛው የበላይነት እንዳይኖር አሳይቷል፣ ለጨለማው ዘመን ብርሃን አብርቷል፣ መንገድ ለጠፋባቸው መንገድ አሳይቷል፤ የዚህ ሕዝብ ልጅ ነህና አንተ በክብርህና በእናት ሀገርህ የሚመጣውን ሁሉ እንደ አባታህ በአሻገር መልስ፣ በደረሰበት ደምሰስ፡፡ የአንተ ጀግንነት፣ የአንተ ጽናት፣ የአንተ ታሪክ ሠሪነት፣ የአንተ አሸናፊነት ሁሉ ከጠላትህ ይበልጣልና ወደፊት ገስግስ፡፡

ʺ እንዲህ ጨሶ ጨሶ የነደደ እንደሆን
ያመዱ ማፈሻ ቦታው ወዴት ይሆን” አሁን በአሸባሪው እብሪት ሁሉም ጨሷል፡፡ በእጁ ያለውን ሁሉ አንስቷል፡፡ እናት ሀገሩን ሊያስከብር ምሎ ተነስቷል፡፡ ʺለኢትጵያ ነብሴን ብሰስት የሠራዊት ጌታ ነብሴን አይቀበላት፣ ኢትዮጵያን ለስጋዬ መቀበሪያ ስንዝር ሥፍራ ትንፈጋት” እያለ ውድ ሕይወቱን ሊሰጣት፣ ሞቶ ሊያኖራት፣ ተዋድቆ ሊያስከብራት፣ በደምና በአጥንቱ ሊያፀናት እየተመመ ነው፡፡ በውስጡ የጨሰው እልህና ወኔ ሲነድ ደግሞ የአመድ ማፈሻም ኾነ ማፍሰሻ አይገኝም፡፡ የነደደው ጀግና ያገኘውን አመድ እያደረገ ይሄዳል እንጂ፡፡ ክተት ብሏልና ወደ ሥፍራው እየተመመ ነው፡፡ በነደደው ልቡ፣ በሚነደው አፈሙዙ ጠላትን ሊያነደው፣ አመድ አድርጎ ሊያቦነው ነው፡፡ ሲነድ የሚለበለበው ብዙ ነው፣ ሲነድ የሚጠፋው ጣለት እልፍ ነው፣ የዛን ጊዜ በነደደው የጀግና እሳት የማይቃጠል ጠላት የለም፡፡

በአለህበት ሁሉ ወኔህን ታጠቅ፣ አካባቢህን ጠብቅ፣ ከአሉባልታ ራቅ፣ የምትችለውን ሁሉ ለሀገርህ ስጣት፣ ኮርተህ አኩራት፤ እርሷም ልጄ ብላ ትኮራብሃለች፣ ክበር ብላ ታከብርሃለች፣ የአሸናፊ ልጅ ነህና አሸናፊነትህን የሚወስድብህ የለም፡፡

በታርቆ ክንዴ – ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 21/2013 ዓ.ም (አሚኮ)

Exit mobile version